አዲስ አበባ፡-የአማራና የትግራይ የአገር ሽማግሌዎች በሁለቱ ክልሎች ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች አማካኝነት የተፈጠረውን ችግር እውነት ላይ ተመስርተው እንዲፈቱ የኢትዮጵያ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ገለጸ።
“ህብረ-ብሄራዊነታችን አንድነታችንን ለማጠናከር ውስጣዊ ችግሮችን በምክክር እንፍታ” በሚል መሪ ሃሳብ በተካሄደው የምክክር መድረክ ላይ የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ኮሚቴ ሰብሳቢ ተወካይ አባ ገዳ በየነ ሰንበቶ እንዳሉት የአማራና የትግራይ የአገር ሽማግሌዎች በሁለቱ ክልሎች ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች አማካኝነት ከቅርብ ጊዜ የሚስተዋለውን ችግር እውነትን መሰረት አድርገው በውይይትና በዕርቅ መፍታት ይኖርባቸዋል።
አባ ገዳ በየነ እንደገለጹት፤ ሰላም ለአገር አንድነትና ለህዝቦች ትስስር መሰረት በመሆኑ ልንንከባከበው ልንጠብቀው የሚገባ ትልቅ ሀብት ነው። የተወሰኑ ወገኖች “የአማራና የትግራይ ህዝብ መቼ ተጣላ፤ የተጣሉት ፖለቲከኞች ናቸው” ቢሉም ይህንንም ችግር መፍታት ያለብን እኛ የአገር ሽማግሌዎች ነን። እናም የአማራና የትግራይ የአገር ሽማግሌዎች በሁለቱ ክልሎች ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች አማካኝነት የተፈጠረውን ችግር በጋራ እውነትን መሰረት አድርገው ሊፈቱት ይገባል ብለዋል።
“ለግል ጥቅም ሲባል ኢትዮጵያ እንደ የመን፣ ሊቢያ፣ ሶሪያና ሶማሊያ እንድትሆን መፍቀድ የለብንም” ያሉት የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ኮሚቴ አባል ሀጂ ኢሳ ሸክ ኡመር በበኩላቸው በአማራና በትግራይ ክልል ፖለቲከኖች መካከል የተፈጠረውን ጊዜያዊ ችግር በውይይት መፍታት ይገባል እንጂ የአገርን ሰላምና አንድነት የሚያናጋ ግጭት ውስጥ መግባት አያስፈልግም ሲሉ ገልጸዋል። የሁለቱ አገር ሽማግሌዎች በህዝብ መካከል ግጭት ለመፍጠር የሚጥሩ ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች ካሉም አደብ ግዙ ማለት ይገባል ብለዋል።
የአገር ሽማግሌዎች መማክርት ምክትል ሰብሳቢ ፓስተር ዳንኤል ገብረስላሴ በበኩላቸው የአማራና የትግራይ ህዝብ የውጭ ወራሪዎችን በመመከትና ዳር ድንበርን በማስጠበቅ ከሌላው የኢትዮጵያ ህዝብ ጋር አብረው የተዋደቁና የአገርን ሉአላዊነት ያስጠበቁ መሆናቸውን አውስተው በፖለቲከኞችና በአክቲቪስቶች አማካኝነት የተፈጠረውን ችግርም በዕርቅና በውይይት መፍታት እንዳለባቸው አስገንዝበዋል።
በተለይ የሁለቱ ክልሎች የአገር ሽማግሌዎች የሚነሳው የወሰን ችግርም ህገመንግስታዊና ህጋዊ መስመርን ተከትሎ መፍትሄ የሚሰጠው ስለሆነ ብዙ ዋጋ ተከፍሎበት የተገነባን ሰላምና አገር ባህላዊ እሴቶቻችን ተጠቅመን በውይይት በመፍታት አገርን በሰላም ማስቀጠል ይገባል ብለዋል።
ከትግራይ ክልል የአገር ሽማግሌ ተወክለው እንደመጡ የገለጹልን መላከ ጸሀይ ተሻለ ገብረሚካኤል የሁለቱ ክልል ህዝቦች የአገር ሽማግሌዎች ከዚህ ቀደም በግልጽ እንደተወያዩት ያጣሉን አክቲቪስቶችና ፖለቲከኞች እንጂ በሁለቱ ህዝቦች መካከል ችግርና ጠብ የለም ሲሉ ገልጸውልናል።
“ፖለቲከኞች በሁለቱ ህዝቦች መካከል ጠብ ያለ በማስመስል ሲገልጹ ይሰማል” ያሉት መላከ ጸሀይ ተሻለ የትግራይ ህዝብ በአማራ ህዝብ ፣የአማራም ህዝብ በትግራይ ህዝብ በክፉ ተነስቶ አያውቅም፤ህዝቡ አብሮ የኖረና የተሳሰረ፤ የአብሮነት ታሪክ ያለው፤ በጋራ እየሰራ በጋራ እየደገ የመጣ ነው ብለዋል።
ሰላም ለፖለቲከኛውም ሆነ ለህዝቡ እንደሚጠቅም የገለጹት የአገር ሽማግሌዎች በጋራ ቁጭ ብለን ስንወያይና ችግሮቹን ስናውቅ መፍትሄዎችንም ስለምናስቀምጥ በፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው ችግር ተፈትቶ ለአገር ሰላም በጋራ ዘብ ልንቆም ይገባል ሲሉ ተናግረዋል።
በአማራና በትግራይ ክልሎች ፖለቲከኞች መካከል የተፈጠረው የፖለቲካ አለመግባባት ከተፈታ ህዝቡ ጋር ችግር እንደሌለ የገለጹት ከአማራ ክልል የአገር ሽማግሌዎች እንደመጡ የገለጹልን አቶ መላኩ ባየልኝ፤ የሁለቱ ክልሎች የአገር ሽማግሌዎች የሁለቱ ህዝቦች ሰላም፣ ፍቅርና ጠንካራ ትስስር እንዲቀጥልና አገራችን ሰላሟ እንዲጠበቅ በፖለቲከኞቹ መካከል የተፈጠረውን መቃቃር ለመፍታት ጥረት እናደርጋለን ብለዋል።
በመድረኩ የአገር ሽማግሌዎቹ ከፖለቲካና ከማንነት ውግንና ነጻ ሁነው የሁለቱ ክልሎች ፖለቲከኞችና አክቲቪስቶች እውነትን መሰረት አድርገው ሊያስታርቋቸው እንደሚገባ የአገር ሽማግሌዎቹ መልዕክታቸውን አስተላልፈዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012
ጌትነት ምህረቴ