አዲስ አበባ፡-ፋይናንሺያል ታይምስ (ኤፍ.ቲ.)ጋዜጣ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድን በፖለቲካው መስክ ከ50 ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦች መካከል አንዱ በማድረግ ስማቸውን አሰፈረ።
ጋዜጣው በያዝነው ሳምንት ባወጣው ዘገባ 50 ተጽእኖ ፈጣሪ ከሆኑ የዓለም እውቅ ሰዎች መካከል ብቸኛው አፍሪካዊ የኢትዮጵያ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ናቸው ሲል አስፍሯል። ጠቅላይ ሚኒስትሩ ባለፉት አሥርት ዓመታት ውስጥ ተጽእኖ መፍጠር ከቻሉት 50 ሰዎች ውስጥም ብቸኛው የአፍሪካ መሪ ሆነዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ ከተሸለሙበት ጊዜ ጀምሮ በዋናነት የመገናኛ ብዙኃንን ቀልብ መሳባቸውንና የለውጥ አራማጅ መሆናቸው፤ የኢትዮ-ኤርትራ ሰላም፣ በርካታ የፖለቲካ ሰዎች ከእስር ቤት መለቀቅ እና የፖለቲካ እና ዴሞክራሲ ምህዳር መስፋቱ የስኬት ታሪካቸው ሆኖ ለመመረጥ እንዳበቃቸው ገልጿል።
በፖለቲካ ፣ በኢኮኖሚ፣ በንግድ እና በቴክኖሎጂ እንዲሁም በባህል፣ በመገናኛ ብዙኃን፣ በሳይንስ እና በስፖርቶች ዙሪያ ያሉ ተጽእኖ ፈጣሪ ግለሰቦችን ዝርዝር ይፋ የሚያደርገው ጋዜጣው፤ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ በፖለቲካው መስክ ተጽእኖ የፈጠሩ መሆኑን አስፍሯል።
የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ዶናልድ ትራምፕ፣ የቻይናው ፕሬዚዳንት ጂንፒንግ ፣ የጀርመን ቻንስለር አንጌላ ሜርክል ፣ የቱርክ ፕሬዚዳንት ሬሴፕ ጣይብ ኤርዶጋንና የቀድሞው የአሜሪካ ፕሬዚዳንት ባራክ ኦባማ እንዲሁ በዝርዝሩ ውስጥ ይገኛሉ ።
ምንጭ፡- አፍሪካን ኒውስ
አዲስ ዘመን ታህሳስ 17/2012
አዲሱ ገረመው