‹‹ኢትዮጵያ በ2050›› በሚል ሀሳብ ትናንት በስካይ ላይት ሆቴል የተጀመረው ዓለምአቀፍ የውይይት መድረክ፤ በ32 ትውልደ ኢትዮጵያውያን ምሑራን (ፕሮፌሰሮችና ዶክተሮች) ተሰናድቶና በተግባር የተፈተሸ እውቀት ታግዞ 64 የጥናት ጽሁፎች የቀረቡበት ሲሆን በኢትዮጵያ የቀጣይ 30 ዓመታት ጉዞ ፈተናና መልካም እድሎች ላይ አተኩሮ እየተካሄደ ያለ ነው፡፡
በውይይት መድረኩ እንደተጠቆመው፤ ኢትዮጵያ ምንም እኳን በእድገት ጉዞ ላይ ብትሆንም በርካታ ችግሮች ያሉባት አገር ናት፡፡ በተለይም ለአንድ አገር ወሳኝ በሆኑ እንደ የትምህርት ጥራት፣ የሃይል አቅርቦት፣ የምግብ ዋስትና፣ በጤና ተደራሽነት እንዲሁም ትራንስፖርት በመሳሰሉ የእድገት መስኮች ወደኋላ ቀርታለች፡፡
ይሄን ችግር ከመፍታት አኳያ ደግሞ በርካታ ስራዎች መከናወን ያለባቸው ሲሆን፤ መድረኩ ሲዘጋጅም ቀደም ሲል በውጭ ያለው የኢትዮጵያ ማህበረሰብ ከሚታወቅበት የፖለቲካ ተሳትፎ ባለፈ በኢትዮጵያ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት ውስጥ የበኩሉን እንዲወጣ ማስቻል ነው፡፡ በመሆኑም መድረኩ ከ30 ዓመት በኋላ ከሚኖራት የህዝብ ቁጥር አኳያ እነዚህን ችግሮች በምን መልኩ ፈትታ መጓዝ አለባት የሚለውን የሚያመላክትና የፖሊሲ ግብዓት የሚያቀርብ ይሆናል፡፡
ከአሜሪካ የመጡት ዶክተር ደብረወርቅ ዘውዴ፣ በመድረኩ ጽሑፍ ካቀረቡ ምሑራን አንዷ ናቸው፡፡ እርሳቸው እንደሚሉት፤ ምንም እንኳን ኢትዮጵያ በርካታ እድሎች ያሏትና በእድገት ጎዳናም ላይ ያለች ብትሆንም ዛሬም 78 በመቶ ያክል ህዝቧ የቀን ገቢው ከ2 ዶላር በታች ነው፡፡
ከ52 ሴቶች አንዷ በወሊድ ምክንያት ትሞታለች፡፡ 70 በመቶ ህዝቧ በጨለማ ውስጥ ይኖራል፤ የኢንተርኔት ተደራሽነቱም ቢሆን ከ15 እስከ 18 በመቶ ነው፤ የንጹህ ውሃ አቅርቦቱም ከ50 በመቶ ያነሰ ነው፤ የዘመናዊ መጸዳጃ ቤትም ከ15 በመቶ አልዘለለም፤ የጎልማሶች የትምህርት ምጣኔም 35 በመቶ ላይ ነው፤ በከተሞች ያለው የህዝብ እድገት ግን በሶስት እጥፍ እያደገ ይገኛል፡፡
ከዚህ ባለፈም የህዝብ ቁጥሯ እያደገ ከመሆኑ ጋር ተያይዞ እአአ በ2050፣ 200 ሚሊዮን እንደሚደርስ ይገመታል፡፡ እነዚህና ሌሎች የሚታዩ ችግሮች ከህዝብ ቁጥሩ እድገት ጋር ተዳምሮ ቀጣይ ስራን የሚጠይቁና ትኩረት ተሰጥቷቸው ሊፈጸሙ የሚገባቸው ናቸው፡፡ ይህ ደግሞ ለወጣቱ የሚመች ነገን ከመስራት ባለፈ ነገር የሚሰሩ ወጣቶችን መፍጠር ይፈልጋል፡፡
በመሆኑም ኢትዮጵያ ጤናው ያልተጠበቀና ያልተማረ አምራች ሃይል ይዛ የትም መድረስ ስለማትችል፤ በወጣቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግና ወጣቱ ወደ አገር ግንባታ የሚገባበትን አቅም መፍጠር ይገባል፡፡ ለፈጣን እድገቷም በትምህርት እና ሴቶች ላይ ኢንቨስት ማድረግ ይጠበቅባታል፡፡ ለእነዚህና ሌሎች ስራዎች እውን መሆን ደግሞ የመልካም አስተዳደር መስፈን ትልቅ ድርሻ እንዳለው ተገንዝቦ መስራት ይገባል::
‹‹ኢትዮጵያውያን ጎበዝ ከተባልን ለምን ከዓለም ደሃ ህዝቦች መካከል ሆንን?›› የሚል ጥያቄን በማንሳት ሀሳባቸውን ያቀረቡት ሌላው የጽሑፍ አቅራቢ ኢንጂነር ታደሰ ሃይለስላሴ በበኩላቸው እንደሚሉት፤ ኢትዮጵያውያን ለእድገት ያላቸውን እድል ያክል ተግባብተውና ተጋግዘው መስራት ከቻሉ ከ30 ዓመት በኋላ የታሰበበት የብልጽግና ስፍራ የማይደርሱበት ምክንያት አይኖርም፡፡ ለዚህ ከሚያበቃቸው ዘርፍ አንዱ ግብርና ሲሆን፤ በተለይ ያላትን የውሃ ሃብት አጠቃቀም አዘምና በጤፍ ላይ አተኩራ መስራት አንዱ የብልጽግናዋ ጉዞ ማፋጠኛ መስክ መሆኑ እሙን ነው፡፡
ኢትዮጵያ ያሏት የልማት እድሎችና የመልሚያ መንገዶች ከቦታ ቦታ የተለያዩ መሆኑን የሚናገሩት ኢንጂነር ታደሰ፤ በምዕራብና ምስራቅ ኢትዮጵያ ያለውን የውሃ ሃብት ለአብነት ያነሳሉ፡፡ በዚህም ውሃን ከምዕራቡ ክፍል ወደ ምስራቁ መፍሰስ እንዲችል ማድረግ አንዱ መንገድ መሆኑን ይገልጻሉ፡፡
ለምሳሌ፣ ከእንጦጦ ጀርባ ካሉ አካባቢዎች ወደ ጀማ ወንዝ ገብተው ከአባይ ወንዝ የሚቀላቀሉ 13 ጅረቶች አሉ፡፡ እነዚህን ወደ አንድ ሰብስቦ በአዲስ አበባ በኩል ወደ ምስራቁ እንዲፈሱ ማድረግ ቢቻል እስከ 2 ቢሊዮን ሜትር ኪዩብ ውሃን ማመንጨትና በውሃውም እስከ 150 ሺህ ሄክታር መሬት ማልማት ይቻላል፡፡ ለዚህ ደግሞ መንግስት፣ ባለሀብቱ፣ ባለሙያዎችና ሌሎችም የልማት አጋሮች ተገቢውን ትኩረትና ድጋፍ ማድረግ ይጠበቅባቸዋል፡፡
ሌላው ጥናት አቅራቢ ፕሮፌሰር አስፋው በየነ እንደሚሉት፤ የአየር ንብረት ለውጥ አሁን ላይ ዓለምን ለበርካታ ውስብስብ ችግሮች እየዳረገ ያለ ጉዳይ ነው፡፡ ለዚህ ደግሞ ካርቦንዳይ ኦክሳይድ ትልቅ ሚና አለው፡፡ የካርቦን ዳይኦሳይድ ምንጭ ደግሞ በአመዛኙ ከመሬት ተቆፍረው የሚወጡ ነገሮች ናቸው፡፡ እነዚህ ተቆፍረው የሚወጡ ማዕድናትና ሌሎችም ለከባቢ አየር መበከል የጎላ ሚና አላቸው፡፡ አሁን ላይ የከባቢ አየር ሙቀት መጨመርም የዚህ አንድ ማሳያ ሲሆን፤ ኢትዮጵያም በዚህ መልኩ ለሚፈጠረው አየር ንብረት ለውጥ ተጠቂ አገራት መካከል አንዷ ናት፡፡
ኢትዮጵያ በማይገመት የዝናብ ሁኔታ ውስጥ ሆና በዝናብ ላይ የተንጠለጠለ ግብርናን ይዛ ከረሃብና ድህነት መውጣት አትችልም፡፡ በመሆኑም የግብርና ስልቷን መቀየር፤ በተለይም የመስኖ ልማት ስራ ላይ ማተኮር ይኖርባታል፡፡ ለዚህ ደግሞ ከወረቀት የዘለለ የሚተገበር ፖሊሲ ቀርጻ መስራት ይጠበቅባታል፡፡
በመድረኩ ላይ የተገኙት ዶክተር የውሃ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስትሩ ዶክተር ኢንጂነር ስለሺ በቀለ በበኩላቸው እንዳሉት፤ መሰረተ ልማትና ኢንቨስትመንት ለኢትዮጵያ ኦኮኖሚ ወሳኝ ጉዳዮች ናቸው፡፡ ለእነዚህ ውጤታማነት ደግሞ ውሃ ወሳኝ ድርሻ አለው፡፡ ይሁን እንጂ የውሃ ሀብታችን፣ አንደኛ በአመዛኙ ድንበር ተሻጋሪ በመሆኑ፤ ሁለተኛም በአካባቢ ጥበቃ ችግር ምክንያት እየተመናመነ በመሆኑ በአግባቡ ጥቅም ላይ እየዋለ አይደለም፡፡ ለምሳሌ፣ እንደ ህዳሴ ግድብ አይነቱን በድንበር ተሸጋሪ ወንዞች ላይ የሚከናወነውን የልማት ስራ ማየት ቢቻል ከሌሎች አገራት ጋር ተባብሮና ተግባብቶ መስራትን ይጠይቃል::
ለዚህም ኢትዮጵያ የድርሻዋን እየተወጣች ነው፡፡ በተመሳሳይ በደን መጨፍጨፍና በመሬት መሸርሸር ምክንያት የውሃ ሀብት እየተጎዳ ይገኛል፡፡ ይሄንንም ለመከላከል ሰፊ የአካባቢ ጥበቃ ስራ እያከናወነች ነው፡፡
እንደ ሚኒስትሩ ገለጻ፤ ኢትዮጵያ ካላት እምቅ ሀብትና የመልማት አቅም አኳያ አሁን ላይ ያለው ነገር በቂ የማይባል፤ ይልቁንም ብዙ መስራትን የሚጠይቅ ነው:: በዚህም የውሃ ሀብቱን ቀጣይነት ልማትና አስተዳደር ለማረጋገጥ በርካታ ስራዎች እየተከናወኑ ሲሆን፤ ባለፈው ክረምት የተከናወነው የአራት ቢሊዮን ችግኝ መርሃ ግብርም የዚሁ አንድ አካል ነው፡፡
ይህ ስራም ከሌሎች አጋዥ የአካባቢ ጥበቃ ስራዎች ጋር ተመጋግቦ የሚቀጥል ይሆናል፡፡ ይህ ሲሆን የውሃ ሀብቱን በማሳደግ የልማቱን ጉዞ ማፋጠን ይቻላል፡፡ በዚህም የመስኖ ልማት፣ የሃይል ማምረት፣ የንጹህ መጠጥ ውሃና ሌሎችንም ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ዘርፍ ልማቶችን ማፋጠን የሚቻልበት እድል ይፈጠራል፡፡
የትራንስፖርት ሚኒስትሯ ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው እንዳሉት፤ ኢትዮጵያ አሁን ላይ በአስገራሚ ለውጥ ላይ ናት፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እርምጃዎችም የዚሁ ማሳያዎች ሲሆኑ፤ የሰላም ኖቤል ሽልማቱ፣ የአገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያው እና ሌሎችም የዚሁ ጉዞ ማሳያዎች ናቸው፡፡ ከስራ እድል ፈጠራ፣ ከኢንቨስትመንት ማስፋፊያና የውጭ ባለሀብቶችን ለማበረታታት የሚደረገው ጥረትም የስራው አጋዥ ነው::
አሁን ባለው የኢትዮጵያ ሁለንተናዊ ለውጥና የመደመር እሳቤ ጉዞ የበርካታ አገራትን ወዳጅነትና የኢንቨስትመንት ተፈላጊነት እያሳደገላት ይገኛል፡፡ አገር በቀል የሆነው የመደመር እሳቤም የአገሪቱን ማህበራዊ፣ ኢኮኖሚያዊና ፖለቲካዊ ጉዳዮች በራሷ እውቀት ለመፍታት እድል የሚሰጣት ነው፡፡ መንግስትም በአገሪቱ ሁለንተናዊ እድገትና ልማት ብሎም የሳይንስና ቴክኖሎጂ ሽግግር እና የትራንስፖርትና ሎጀስቲክስ ዘርፉ ላይ የዳያስፖራው ተሳትፎ እንዲያድግ በፖሊሲና በተግባር እቅድ ይደግፋል ብለዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 10/2012
ወንድወሰን ሽመልስ