አዲስ አበባ፦ በ2011ዓ.ም ክረምት በሀገር አቀፍ በአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር መሬት ላይ ከተተከሉት ችግኞች የጸደቁት በ13ሺ656 ሄክታር ላይ ብቻ መሆኑ የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን ገለጸ::
በኮሚሽኑ የአነስተኛና ሰፋፊ ደን ልማት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር ወይዘሮ ሐረገወይን ተክሉ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በአንድ ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ሄክታር ላይ አራት ነጥብ አምስት ቢሊዮን ችግኝ ቢተከለም በእንክብካቤ የፀደቀው በ138ሺ656 ሄክታር ላይ የተተከለው ብቻ ነው::
በ2011 ዓ.ም በክረምት በንቅናቄ በሀገርአቀፍ የተካሄደው የችግኝ ተከላ እንክብካቤና የጽድቀት መጠንን ለማወቅ የኮሚሽኑ የባለሙያዎች ቡድን ከሁለት ወር በፊት በዘጠኙም ክልሎች በአካሄደው የመስክ ምልከታ በ138ሺ656 ሄክታር መሬት ላይ የእንክብካቤ ሥራ መሰራቱ ተረጋግጧል::
እንደ ዳይሬክተሯ ማብራሪያ፤ የክረምቱ ወቅት ረጅም በመሆኑ ለችግኞቹ የጽድቀት መጠን አስተዋጽኦ አድርጓል::ይሁን እንጂ እንክብካቤውና የችግኝ የጽድቀት መጠን ግን የችግኝ ተከላ መርሃግብሩ በህዝብ ንቅናቄ ከእቅድ በላይ የተከናወነውን ያህል አለመሆኑን የመስክ ምልከታ መረጃ ያሳያል::
በመስክ ምልከታው ዓረም የበላቸው ችግኞች መኖራቸው እንዲሁም በውሃ መብዛት የተዋጡ እና ለችግኝ ማሸጊያ ውለው የነበሩ ላስቲኮች ከስፍራው ባለመወገዳቸው መልሰው ችግኞቹን በማፈናቸው በጽድቀቱ ላይ ተጽዕኖ መፍጠሩ በክፍተት ተለይቷል::
ቀደም ሲል በኮሚሽኑ ባለሙያዎች ብቻ የተከናወነው የመስክ ምልከታ በቂ አለመሆኑ እንደታመነበትና የእንብካቤ ሥራውም አስፈላጊነት ትኩረት እንደተሰጠው የጠቆሙት ወይዘሮ ሐረገወይን፤ በመስክ ምልከታው የታዩ ክፍተቶችን ለማረምና የእንክብካቤ ሥራ እንዲጠናከር ከኮሚሽኑ፣ከግብርና፣ ከውሃ፣ መስኖና ኤሌክትሪክ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቶች የተውጣጡ የባለሙያዎች ቡድን ተዋቅሮ በቅርቡ አማራ፣ኦሮሚያ፣ትግራይና ደቡብ ብሄሮች ብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልሎች ለመስክ ምልከታ መላካቸውን ገልጸዋል::
መረጃዎቹም ተጠናክረው በቅርቡ ለህዝብ ይፋ እንደሚሆንአስታውቀዋል::በእንክብካቤው ሁሉም ክልሎች ኃላፊነት እንዲወስዱ እንደሚደረግም ጠቁመዋል::
በክረምት የተከናወነው የችግኝ ተከላ መርሃግብር የሀገሪቱን የደን ሽፋን በምን ያህል መጠን እንደሚያሳድገው ከወዲሁ ለማወቅ እንደማይቻልና ወደፊት የሚሰራ መሆኑን የጠቆሙት ወይዘሮ ሐረገወይን፤ በሁለተኛው የዕድገትና ትራንስፎርሜሽን የዕቅድ ዘመን ማብቂያ ላይ የደን ሽፋኑን ከነበረበት 15 ነጥብ አምስት በመቶ 20 በመቶ ላይ ለማድረስ መታቀዱን አስረድተዋል::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012
ለምለም መንግሥቱ