ህፃን መሠረት ዘርፉ እና ፎዚያ ኪሮስ ከክፍላቸው ወጥተው ወደ ምገባ እያመሩ ነበር ያገኘኋቸው:: ህፃናቱ እንደነገሩኝ ሁሌም ጠዋት በእረፍት ክፍለ ጊዜ ጢቢኛ (ዳቦ) በወተት ቁርሳቸውን ይመገባሉ:: የቅድመ መደበኛ ክፍል ተማሪዎችም በየቀኑ በመምህራኖቻቸው እየታገዙ በምገባ ክፍሉ ወተትና ጢቢኛ እንዲመገቡ ይስተናገዳሉ::
የምገባ ክፍሉን ተዘዋውሬ እንዳየሁት ተማሪዎቹ የሚመገቡበት መጠለያና መቀመጫ ምቹ ነው:: የመመገቢያ ክፍሉም ንጹህ ነው:: የማብሰያ ክፍሉም እንዲሁ:: የምግብ አቅራቢዎች ንጽህናም ጥንቃቄያቸውን ያሳያል:: ወተቱ በመመገቢያው ግቢ ካሉ ላሞች እየታለበ እንደሚቀርብላቸውም አረጋግጫለሁ:: ጢቢኛውም እዛው ነው የሚጋገረው:: ላሞቹን የሚያልቡና ዳቦውን የሚጋግሩ ሰራተኞች በመኖራቸው ተማሪዎቹ ተገቢውን ቁርስ ያገኛሉ::
በምገባ ክፍሉ ውስጥ ለስድስት ዓመታት ተቀጥረው የሰሩት ወይዘሮ ነነይ ግርማ እንደነገሩኝ በየቀኑ ከስድስት ላሞች 35 ሊትር ወተት ያልባሉ:: ሁሉንም አፍልተው ለተማሪዎቹ በቁርስ ሰዓት ላይ ያቀርቡላቸዋል:: ማታ የሚያልቡትን ደግሞ ለገበያ ያቀርባሉ:: ዳቦ የሚጋግሩ፣ ለላሞቹ ምግብ የሚያቀርቡና አትክልት የሚንከባከቡም አብረዋቸው ይሰራሉ::
እንዲህ ያለውን የትምህርት ቤት ምገባ የጎበኘሁት በአማራ ክልል ዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሰቆጣ ከተማ የሚገኘውን የአዝባ አጠቃላይ አንደኛ ደረጃ ትምህርት ቤት ነው::
የትምህርት ቤቱ ርዕሰ መምህር ገብረመስቀል አሰፋ እንደነገሩኝ በትምህርት ቤታቸው የምገባ ፕሮግራሙ የተጀመረው በ2007 ዓ.ም ወይዘሮ ፍሬዓለም ሽባባው የሚባሉ ግለሰብ በሚመሩት ‹የኢትዮጵያ ስኩል ሚል ኢኒሼቲቭ› ፕሮጀክት አማካኝነት ነው:: በወቅቱም ግለሰቧ ከአንድ ነጥብ አምስት ሚሊዮን ብር በላይ በሆነ ወጪ የምገባ ክፍሉን አደራጅተው፣ 10 የወተት ላሞችን ከማደሪያቸውና ከመኖአቸው ጋር እንዲሁም ሠራተኞችንም አሟልተው ነው ለትምህርት ቤቱ ያስረከቡት::
ምገባው ለአንድ ዓመት ተኩል በእርሳቸው ክትትል ሲከናወን መቆየቱን የገለጹት ርዕሰ መምህሩ፣ በስምምነቱ መሰረት ከሥራው ቢወጡም ለጢቢኛ የሚሆን የተመጣጠነ 16 ኩንታል ዱቄት በየወሩ በማቅረብ ያግዛሉ:: በትምህርት ቤቱ ምገባው ከመጀመሩ በፊት የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ቁጥር ከ90 አይበልጥም ነበር ፤ ከምገባ በኋላ ግን በየዓመቱ የተማሪዎች ቁጥር ጨምሯል:: በአሁኑ ጊዜም ቁጥሩ 312 ደርሷል ይላሉ::
ትምህርት ቤቱ ከ2009 ዓ.ም ጀምሮ ማታ ታልቦ ለገበያ ከሚያውለው የወተት ሽያጭ እና ከተለያዩ ገቢዎች የወተት አቅርቦቱን፣ የላሞቹን መኖ እና የሰራተኞችም የደመወዝ ክፍያ እየደጎመ መሆኑን የጠቆሙት ርዕሰ መምህሩ፣ ወጪና ገቢ ባለመመጣጠኑ አቅርቦቱን ማሳደግ እንዳልተቻለ ገልጸዋል:: የመኖ ወጪ ከፍተኛ እንደሆነና በተፈጥሮና በተለያየ ምክንያት ሁሉም ላሞች የማይታለቡበት ሁኔታ መኖሩንም ያመለክታሉ::
አጠቃላይ የምገባ ፕሮግራሙን በተመለከተ በዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ትምህርት መምሪያ የሥርዓተ ምግብ ተጠሪ አቶ ፈንታው ስዩም እንዳስረዱት፣ በዞኑ በሚገኙ 10 ትምህርት ቤቶች ውስጥ እየተተገበረ ይገኛል:: ከነዚህ ውስጥም ሰባቱ ወተትና ጢቢኛ የተቀሩት ደግሞ የወተት አቅርቦት ብቻ ነው ያላቸው:: በምገባ ፕሮግራሙ አንድ ትምህርት ቤት 211ሺ ብር በጀት አለው:: ለእያንዳንዱ ትምህርት ቤትም 16 ነጥብ 5 ኩንታል ዱቄት ይቀርብለታል:: በምገባ ፕሮግራሙ ሶስት ሺ 825 የቅድመ መደበኛ ተማሪዎች ተጠቃሚ ሆነዋል::
ዞኑ የምገባ ፕሮግራሙን ማስተዳደር ከጀመረ ወዲህ ዞኑና የሰቆጣ ከተማ በጋራ በበጀት ድጋፍ እያደረጉ ይገኛሉ:: ዞኑ ባለፈው ዓመት አንድ ነጥብ ስምንት ሚሊዮን ብር በጀት የመደበ ሲሆን፣ ዘንድሮም በቅድም ዝግጅት ላይ ይገኛል:: የሰቆጣ ከተማ አስተዳደርም ባለፈው ዓመት ስድስት ሺ ብር ዘንድሮ ደግሞ አምስት ሺ ብር ድጋፍ አድርጓል::
እስካሁን በተከናወነው የምገባ ፕሮግራም ተማሪዎችን በመሳብ፣ መጠነ ማቋረጥን በማስቀረት፣ በተማሪዎች የትምህርት አቀባበልና ውጤት ላይ መሻሻል እንዲመጣ አግዟል::
ለውጤት የሚያበቁ የተጠናከሩ ድጋፎች ቢኖሩም በየትምህርት ቤቱ ፕሮግራሙን የሚመራ አካል አለመኖር፣ እንደ ተደራቢ ሥራ አድርጎ ማየት፣ በሁሉም ትምህርት ቤቶች ተመሳሳይ የሆነ ጥንካሬ አለመኖር የሚስተዋሉ ክፍተቶች መኖራቸውን አቶ ፈንታው ይጠቅሳሉ:: ክፍተቶቹን በማረም የምገባ ፕሮግራሙ በሌሎች የዞኑ ትምህርት ቤቶች ለማስፋት ጥረት እየተደረገ መሆኑንም ይገልጻሉ::
አዲስ ዘመን ታህሳስ 9/2012
ለምለም መንግሥቱ