‹‹እንኳን ለኢትዮጵያ የንጋት ባለቤት፣ የብርሃን ምንጭ ልትሆኑ እንደምትችሉ ታጤኑ ዘንድ ‹ድቅድቅ ጨለማም እንዲከሰት ማድረግ እንደምትችሉ ሁሉ› እግዚአብሔር ልቦናችሁን ከፈተላችሁ›› የሚል ጽሁፍ ከመረጃ መረብ ላይ አነበብኩና በስተመጨረሻ ወደ ልቦናቸው የተመለሱትን ፖለቲከኞች ጅምራቸውን በጥሩ እንዲያስጨርሳቸው እኔም መልካሙን ተመኘሁላቸው።
ባለፉት ጊዜያት ለሁላችንም የምትመች ኢትዮጵያን መገንባት የምንችልበትን “የብርሃን ፍንጣቂ” ማየት ተስኖን ሁሉም እንደየፖለቲካ ዕምነቱና ምኞቱ ሕዝብን ከጀርባው አሰልፎ ሲራወጥ፣ በወገን ላይ ጉዳት መድረሱ፣ መፈናቀልና ሞት መታየቱ አሳዛኝ ቢሆንም፤ ከብዙ መከራና ስቃይ እንዲሁም ያላሰለሰ ውይይት በኋላ ምን እየሠራን ነበር ወደሚለው ዕሳቤ መመለስ ነገም ሌላ ቀን ነው ያስብላል።
አገርን ከገባችበት ያለመግባባት አዘቅት ያወጣታል በሚል ተስፋ የተደረገበትና በጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ አነሳሽነት በተቃውሞ ጎራ በተሰለፉ የፖለቲካ ኃይሎች መካከል በተደጋጋሚ እየተካሄደ ያለው ውይይትና ይህንኑ ተከትሎ የመጣው “አገርን ማስቀደም” የሚለው ዕሳቤ በርግጥም በውኑ ላሰበው ከዚህ የተሻለ ምን ሊመጣ ይችላል?
እነሆ አሁን ደግሞ ተስፋችን የበለጠ ለምልሞ ሁላችንም የኛ የምንላትን አገር ብሩህ ዕድል ከወዲሁ ስናማትር ተስፋችንን የሚያጨልሙ ነገሮችን በውይይትና በመነጋገር ለመፍታት በእጃችን ባለውና ቀድሞም ባዳበርነው ቁጭ ብሎ በመነጋገር ችግሮችን የመፍታት ባህላችን የታላቋን አገር ታላቅ ተስፋ ለማፅናት መነሳታችን ታላቅ የመሆን ምኞታችንን ዕውን ያደርግልናል።
“የምንፈልጋት የነገዋን ኢትዮጵያ” ለመገንባት ከተዘጋጁ ወርቃማ ዕድሎች መካከል “ማድረግ የሚገባንን ማድረግ” የሚለውን ከግብ ለማድረስ በተወጠነው ‹‹የንጋት ብርሃን ሴናሪዮ›› የኢትዮጵያ የዕድገት ደረጃ እየጎለመሰ ሄዶ ዕውን የሚሆንበት መፃኢ ተስፋን ሰንቋል። ይህ ውጥን የሙሉ ቀን ብርሃን ባይታይም የአዲሱ ቀን ብርሃን ወገግታ መታየቱን የሚያበስር ነው።
ከቅርብ ጊዜያት ወዲህ በተለያዩ ክልሎችና በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ እየተቀጣጠሉ ለሞትና ለአካላዊ ጉዳት እየዳረጉን ያሉት አለመግባባቶች መነሻቸው የፖለቲከኞች ቅስቀሳ በመሆኑ በረዱ ሲባል እየጋሉ ለብዙዎች ሐዘንን፤ ለአገርም ከፍተኛ ጉዳትን አስከትለዋል።
በተለይም በአማራና በኦሮሚያ ክልሎች ውስጥ እየተፈጠሩ ያሉ ችግሮችን ለመፍታት በርካታ የውይይት መድረኮች ተካሂደዋል። ከእነዚህም ውስጥ የአማራና የኦሮሞ ባለሀብቶች፣ የአማራና ኦሮሞ የሃይማኖት አባቶች፣ አባገዳዎችና የሀገር ሽግሌዎች፣ የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች፣ የአማራና ኦሮሞ ምሁራን፣ የአማራና ኦሮሞ አክቲቪስቶችና የሚዲያ ባለሙያዎች፣ የአማራና የኦሮሞ ወጣቶች መድረኮች ተጠቃሾች ናቸው።
እነዚህ የእርቅና የመፍትሄ ማስገኛ መድረኮች በጥቂት ክልሎች ብቻ ተወስነው መቅረት ያለባቸው ሳይሆን በአማራና በትግራይ እንዲሁም በሌሎች ክልሎችም ለመልካም ግንኙነት መሰረት የሚጥሉ በመሆናቸው በትኩረት ሊጠናከሩ ይገባል።
ሰሞኑን እየተካሄዱ ያሉት የፖለቲከኞች የውይይት መድረኮች ተቋማዊ ማሻሻያዎችንና የዕርቅ ሂደቶችን አጠናክረው የሚያስቀጥሉ፤ በአገሪቱ ውስጥ በተለያየ ደረጃ ሥር የሰደዱ ማህበራዊ ቅራኔዎች በጠረጴዛ ዙሪያ በውይይት እልባት እንዲያገኙ ተስፋ የሚጣልባቸው በመሆናቸው በሁሉም ዘንድ ተጠናክረው ሊቀጥሉ ይገባል። የብርሃንም የድቅድቅ ጨለማም ምንጩ የራስ አስተሳሰብ ነውና በቀና ውይይት ብሩሁን መንገድ እንከተል። በዚህ ነው የምንፈልጋት ኢትዮጵያን የተሻለ ደረጃ ላይ ማድረስ የምንችለው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012