– ዋና ዳይሬክተሮችና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ከአንድ በላይ ተሽከርካሪ እንዳይጠቀሙ ይከለክላል
አዲስ አበባ፡- በ2009 ዓ.ም የወጣው የተሿሚዎች የመኪና አጠቃቀም መመሪያ ለአንድ ወገን ያደላ ፤ ወጪ ከመቆጠብ ይልቅ አባካኝነቱ የጎላ በመሆኑ መመሪያውን ለመቀየር ጥናት እየተካሄደ መሆኑን የገንዘብ ሚኒስቴር አስታወቀ፡፡
ዋና ዳይሬክተሮችና ምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ከአንድ በላይ ተሽከርካሪ እንዳይጠቀሙ በሚኒስትሮች ምክር ቤት መታዘዙ ተጠቆመ፡፡
የሚኒስቴሩ የህዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር አቶ ሃጂ ኢብሳ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የቀድሞው መመሪያ ወጪ ቁጠባ በሚል ‹‹ቪ8››ን የመሳሰሉ መኪኖች እንዳይገዙ፤ የተገዙትም በከተማ ውስጥ ሳይሆን ከከተማ ውጪ ብቻ ለመስክ ሥራ እንዲያገለግሉ የሚያስገድድ፣ የመንግስት መኪናዎች ግዢ ከውጭ አገር ሳይሆን ከአገር ውስጥ አስመጪዎች ላይ እንዲገዛ የሚያዝ ሲሆን፤ መመሪያው ተግባር ላይ ሲውል ለአፈፃፀም አዳጋችና ለአንድ ወገን ያደላ ሆኖ ተገኝቷል፡፡
እንደ አቶ ሃጂ ገለፃ፤ በወቅቱ ትልልቆቹ መኪኖች በከተማ ውስጥ ሲነዱ ነዳጅ ያባክናሉ ቢባልም ከአገር ውስጥ አስመጪዎች የተሻሉ በሚል በጨረታ የተገዙት 400 ዎቹ መኪናዎች በከተማ ውስጥ ሲነዱ ነዳጅ የሚወስዱ ሆነው ተገኝተዋል፡፡ በተጨማሪ ከ50 በላይ መኪናዎች ተበላሽተው የቆሙ ሲሆን፤ እነዚህ መኪናዎች ሚኒስትሮችና ሌሎችም ተሿሚዎች በነበራቸው መኪና ላይ የተጨመሩ በመሆናቸው በተቋሞች ላይ ተጨማሪ ሹፌርና ነዳጅ እንዲያወጡ በማድረጉ የቀደመው መመሪያ ለብክነት አጋልጧል፡፡
አቶ ሃጂ ‹‹ተሰብስበው ገንዘብ ሚኒስቴር ይቁሙና ተሿሚዎች ፊልድ ሲሄዱ ብቻ ይጠቀሙባቸው›› የተባሉት መኪኖች ቢበላሹ ማን ኃላፊነቱን ይወስዳል? የሚለው በመመሪያው በግልፅ አልተቀመጠም፡፡ መኪናዎቹ ለወራት ሲቆሙ ሞተራቸው ለብልሽት የሚጋለጥበት ሁኔታ ታሳቢ ባለመደረጉ ተግባራዊ ለማድረግ አዳጋች ሆኗል›› ብለዋል፡፡
ቀደም ሲል ጀምሮ ለሚኒስትሮች የሚፈቀዱት መኪኖች ቁጥር ሁለት ቢሆንም፤ 400 መኪናዎች ተገዙ በሚል አንዳንዶቹ ሶስት መኪኖች እንዲኖራቸው መደረጉን የጠቆሙት አቶ ሃጂ፤ ነገር ግን ብዙዎቹ ትንንሾቹን መኪኖች ለሌላቸው ዳይሬክተሮች አዘዋውረው የመስኩንና ሌላ ሁለተኛ መኪና መያዛቸውን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሃጂ ዋና ዳይሬክተሮች በፊት የነበራቸው መኪና ላይ ትንሿ መኪና የተጨመረችላቸው በመሆኑ አንዳንዶቹ ሁለት መኪና ሲይዙ ሌሎች ግን አንድ መኪና መያዛቸውን ገልጸው፤ በዚህ ሳቢያ የተሿሚዎች የመኪና ቁጥር በመጨመሩ መመሪያው ለተጨማሪ የሹፌር ቅጥርና የነዳጅ ወጪ ዳርጓል፤ መመሪያው ብክነትን ለመቀነስ የወጣ ነው ቢባልም በተገላቢጦሽ ብክነት ያስከተለ መሆኑን ተናግረዋል፡፡
አቶ ሃጂ መመሪያውን ተከትሎ አዲስ ተሿሚዎች በመብዛታቸውና በፊትም የነበሩ ከኃላፊነት የተነሱ ሚኒስትሮች በህጉ መሰረት መኪና የሚመደብላቸው በመሆኑ፤ ከመመሪያው ውጪ ከአገር ውስጥ አስመጪዎች ሳይሆን ከውጭ የመኪና ግዢዎች እየተፈፀሙና መመሪያው እየተተገበረ አለመሆኑን ጠቁመው፤ መመሪያውን ለመቀየር ጥናት እየተካሄደ መሆኑን አብራርተዋል፡፡
የከፍተኛ የመንግስት ኃላፊዎች የደመወዝና ጥቅማጥቅምን ለመወሰን የወጣውን መመሪያ ለማሻሻል ከጠቅላይ ሚኒስትር ጽህፈት ቤት የተላለፈ ሰርኩላር ለዋና ዳይሬክተሮችና ለምክትል ዋና ዳይሬክተሮች ከአንድ በላይ ተሽከርካሪ እንዳይጠቀሙና ለቤተሰቦቻቸው የሚመደብ ተሽከርካሪም እንደማይኖር ያመለክታል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
ምህረት ሞገስ