የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች የነገ ሀገራቸውን በጋራ መገንባት እንደሚገባቸው ጥሪ አቅርበዋል
- የሁሉም ፖለቲካ ፓርቲዎች ራዕይ አንዲት ዲሞክራሲያዊትና የበለጸገች አገር መገንባት ነው
አዲስ አበባ፡- በዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚፈጠሩ ግጭቶችን መነሻ በማድረግ እንዲሁም በሀገሪቱ አጠቃላይ ወቅታዊ ችግሮች ላይ የተወያዩት የኦሮሞና የአማራ የፖለቲካ ፓርቲዎች ተባብረው በመስራት ችግሮችን በዘላቂነት ለመፍታት ተስማሙ፡፡
ስምንት የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ፓርቲዎች እንዲሁም ከሃምሳ በላይ ምሁራን የተሳተፉበትና ለሁለት ቀናት ሲካሄድ የቆየው የውይይት መድረክ ትናንትና ምሽት ሲጠናቀቅ፤ የሀገሪቱን ችግሮች በዘላቂነት ለመፍታት ስምምነት ላይ መድረሳቸውን ፓርቲዎቻቸውን ወክለው የተገኙ ከፍተኛ አመራሮች በጋራ በሰጡት መግለጫ ተናግረዋል፡፡
የኦሮሞ ነጻነት ግንባር ሊቀ መንበር አቶ ዳውድ ኢብሳ፤ የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች ከሳምንታት በፊት ባካሄዱት የጋራ ውይይት ህዝብን ለማጋጨት በተለይም በሁለቱም ክልሎች የሚገኙ ዩኒቨርሲቲዎችን ማዕከል አድርገው የሚንቀሳቀሱ አካላት መኖራቸውን እንደተገነዘቡ አስታውሰው፤ ችግሮቹን ለመፍታት ፓርቲዎቹ ባደረጉት ስምምነት መሰረት የበኩላቸውን ጥረት ሲያደርጉ መቆየታቸውን ተናግረዋል፡፡
ሊቀመንበሩ “ችግሩ ሁሉንም የሚነካና የሀገሪቱን ፖለቲካም እንዳይረጋጋ የሚያደርግ በመሆኑ ሌሎች በርካታ አጀንዳዎች ቢኖሩብንም በድጋሚ ለጉዳዩ ልዩ ትኩረት ሰጥተን በጥልቀት ተወያይተንበታል፡፡ ችግሩ የመጨረሻ መፍትሔ እንዲያገኝ እጅ ለእጅ ተያይዘን ሁላችንም በጋራ የምንሰራበትን ሁኔታ ለመፍጠርም ተስማምተናል” ብለዋል፡፡
የአማራ ብሔራዊ ንቅናቄ ሊቀመንበር ዶክተር ደሳለኝ ጫኔ በበኩላቸው፤ ፓርቲዎቹ ለችግሩ አጽንኦት ሰጥተው መወያየታቸውንና ልዩነቶችን በውይይትና በሰለጠነ መንገድ ለመፍታት መስማማታቸውን ጠቅሰው፤ የፖለቲካ ልዩነቶች ቢኖሩም አብሮ ላለመኖርና እርስ በእርስ ለመገዳደል ምክንያት መሆን እንደሌለባቸው ተናግረዋል፡፡
ዶክተር ደሳለኝ “የአማራ ተማሪዎች በአማራ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች ውስጥ የሚማሩ የኦሮሞ ተማሪዎች ወንድሞቻችሁ ናቸው፤ የኦሮሞ ተማሪዎችም በኦሮሚያ ክልል ዩኒቨርሲቲዎች የሚማሩ የአማራ ተማሪዎች ወንድሞቻችሁ ናቸው፡፡ ስለሆነም የማትግባቡበት ነገር ሲኖር እርስ በእርሳችሁ ተወያዩ፣ ተመካከሩ፣ ጥርጣሬያችሁንና ልዩነቶቻችሁን በመግባባት ፍቱ ” በማለት መልዕክት አስተላልፈዋል፡፡
የአማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው (ከብልጽግና ፓርቲ) የተገኙት ዶክተር ደስታ ተስፋው በበኩላቸው፤ የአማራና የኦሮሞ የፖለቲካ ድርጅቶች በጉዳዩ ላይ በትኩረት ከመከሩበት በኋላ አንድ የጋራ አቋም ላይ መድረሳቸውን ገልጸዋል፡፡ ዶክተር ደስታ በአማራና በኦሮሞ ወንድማማች ተማሪዎች መካከል የተፈጠረው ችግር በምንም ዓይነት መለኪያ ተቀባይነት እንደሌለውና በአፋጣኝ መቆም እንደሚገባው ገልጸው፤
የነገዋ ኢትዮጵያ ተስፋ የሆኑት ወጣት የዩኒቨርሲቲ ተማሪዎች ችግሮቻቸውን በእርቅና በሰላም ፈትተው ተስፋዋ የለመለመችና የበለጸገች ኢትዮጵያን ለመገንባት መነሳት እንዳለባቸው ተናግረዋል፡፡
የኦሮሞ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲን ወክለው (ከብልጽግና ፓርቲ ) በውይይቱ የተሳተፉት አቶ ታዬ ደንደአ “የተማሪዎችን ህይወት እስከ መንጠቅ የደረሰው ግጭት በወንድማማቾች መካከል የተፈጠረና በፍጹም መደረግ ያልነበረበት አሳዛኝና አሳፋሪ መሆኑን ባደረግነው ውይይት ተገንዝበናል” ካሉ በኋላ ‹‹ጉዳዩ የሚመለከተን አካላት ችግሩን በዘላቂነት ለመፍታትና ወጣቶቹ የጋራ ሀገራቸውን በጋራ የሚገነቡበትን መንገድ ለማመቻቸት ተባብረን የምንሰራበትን ስምምነት ፈጥረናል›› ብለዋል፡፡
አቶ ታዬ ችግሩን በማባባስ ላይ የተጠመዱ አንዳንድ መገናኛ ብዙሃን ከድርጊታቸው እንዲቆጠቡ፣ ማህበረሰቡም ተማሪዎችን በማቅረብና በመንከባከብ
ከፓርቲዎች ጎን እንዲቆም ጥሪ አቅርበው፤ መንግስት ለተማሪዎች የሚያደርገውን ጥበቃ አጠናክሮ ለመቀጠል ዝግጁ መሆኑን አመልክተዋል፡፡
ከውይይት መድረኩ አዘጋጆች አንዱ ዶክተር ገበያው ጥሩነህ ‹‹የውይይቱ ውጤት ከሞት እንደ መነሳት ያህል ነው፤ ችግሩን ከሥር መሰረቱ ሊፈታ የሚችል ወሳኝ ውይይትና ስምምነት አድርገናል፣ የሀገራችሁ ጉዳይ ለሚያሳስባችሁ ሁሉ እንኳን ደስ ያላችሁ” ብለዋል፡፡
ዶክተር ገበያው “መንገዳቸው የተለያየ ቢሆንም ሁሉም የፖለቲካ ድርጅቶች የሚፈልጉት የበለጸገች አንዲት የጋራ ኢትዮጵያን መገንባት ነው፤ ውይይቱ ተማሪዎችን የተመለከተ ብቻ ሳይሆን አጠቃላይ ሀገሪቱን ከገባችበት ችግር ሊያወጣ የሚችል ትልቅ ውጤት የተገኘበት ነው፡፡ ወደፊትም ተጠናክሮ ሊቀጥል ይገባል›› በማለት በውይይቱ የተገኘው መልካም ውጤት ከልብ እንዳስደሰታቸው ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
ይበል ካሳ