‹‹ባለቤቴ ድብደባ አድርሶብኛል›› ያለችው ሰላማዊት ደጉ (ስሟ የተቀየረ) ወደ ፖሊስ ጣቢያ ታመራለች። በቦክስ ደጋግሞ እንደመታት፣ በጥቃቱም ሁለት ጥርሶቿ እንደወለቁ፤ ለፖሊስ ቃሏን ሰጠች።
የፌዴራል ጠቅላይ ዐቃቤ ሕግም ጥቃት አድራሹን በመክሰስ ሰላማዊትን በምስክርነት ችሎት ያቀርባታል። ምስክሯም እውነቱን ብቻ ለመናገር ቃለ መሀላ ትፈጽማለች። ፖሊስ ጣቢያ የሰጠችውን ቃል ግን መድገም አልሆነላትም። ዐቃቤ ህግም ‹‹ቃሏን በመቀየር ሐሰተኛ ምስክርነት በመስጠት ወንጀል ፈጽማለች›› ሲል ክስ ይመሰርትባታል። ፍርድ ቤቱም የፍትሕ ሥራን ያሳሳተች መሆኑን አረጋግጦ ጥፋተኛ ብሏታል።
በዚህ አካሄድ የሀሰት ምስክርነት መበራከቱንና በፍርድ ቤት ስራ ላይ ተጽእኖ መፍጠሩ በተደጋጋሚ ይነገራል። ከ1988 ዓ.ም እስከ 2012 ሩብ ዓመት ብቻ በሀሰት የመመስከር ወንጀል 173 መዝገቦች ለጠቅላይ ፍርድ ቤት ቀርበው ስምንቱ ፍርድ ተላልፎባቸዋል። ቀሪዎቹም የስር ፍርድ ቤቶች ውሳኔ ጸንቶባቸዋል።
የፌዴራል ጠቅላይ ፍርድ ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት አቶ ሰለሞን አረዳ፤ ሀሰተኛ ምስክርነት፣ ሙግት፣ ማስረጃዎች፣ ክሶችና የሀሰት መከራከሪያዎች በከፍተኛ ደረጃ ፍርድ ቤት እየቀረቡ መሆናቸው፤ ዳኞች በሀሰት የቀረቡላቸውን ማስረጃና ምስክርነት ሲመዝኑ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ እንደሚችሉ በመጥቀስ ሁኔታው መታረም እንዳለበት ያሳስባሉ።
ምስክሮች ቃላቸውን ከመስጠታቸው በፊት ዕውነት ለመናገር በእምነታቸው መሰረት እንደሚምሉ የሚያስታውሱት አቶ ሰለሞን፤ ‹‹ኢትዮጵያውያን ግብረ ገብ ያላቸው ፣ የሞራል ልዕልናቸው የላቀና ሃይማኖተኞች ናቸው ቢባልም› አሁን ያለው ተጨባጭ ሁኔታ ግን ተቃራኒ ሆኖ ተገኝቷል›› ይላሉ።
እንደ አቶ ሰለሞን ማብራሪያ፤ ሐሰተኛ ምስክርነት በኢትዮጵያ ፍርድ ቤቶች መሰረታዊ ችግር ሆኗል። ሁኔታው የዳኞችን ጊዜ ያባክናል። በሐሰት የቀረቡላቸውን የሰውና የሰነድ ማስረጃዎች በሚመዝኑበት ጊዜ የተሳሳተ መደምደሚያ ላይ ሊደርሱ ይችላሉ። በፍርድ ቤቶች፣ በዳኞች፣ አስተዳደራዊ ውሳኔዎችን ለመመልከት በህግ በተቋቋሙ አካላት የሀሰት ምስክርነት የሚቀርብ ከሆነ ከዕውነታው ያፈነገጠ ድምዳሜ ይፈጥራል። በፍትህ ተቋማቱም ላይ ዕምነት እንዲታጣ ያደርጋል።
አቶ ሰለሞን ዜጎች ለፍትህ መቆም እንዳለባቸውና በክርክር ሂደት እውነትን በመያዝ የሌሎችን መብቶች ማክበር እንደሚገባና ሐሰተኛ ምስክርነት የሚያስቀጣ በመሆኑ ጥንቃቄ እንደሚያስፈልገው ያሳስባሉ።
በጠቅላይ ዐቃቤ ህግ የወንጀል ምስክሮችና ጠቋሚዎች ጥበቃ ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገበየሁ በፖሊስ ጣቢያ የሰጡትን ቃል ፍርድ በሚሰጥበት ቦታ የሚቀይሩ ሰዎች መብዛታቸውን፤ የሀሰት ምስክርነት ሰዎች ያላግባብ እንዲታሰሩና የፍትሃብሄር መብታቸውን እንዲያጡ እንደሚያደርጋቸው ይናገራሉ።
እንደ አቶ ገብሩ ገለጻ፤ ወንጀል የሰራ ሰው ሳይቀጣ በህብረተሰቡ ውስጥ እንዲኖር መፍቀድ ሰዎችም ከጥፋተኛው እንዳይማሩ፣ ወንጀልን ድጋሚ የመፈጸም ዕድል እንዲያገኙና የፍትህ ስርዓቱ ተዓማኒነትን እንዲያጣ ያደርጋል። በመሆኑም ሀሰተኛ ምስክርነት ከተረጋገጠበት ቅጣቱ አይቀርም ድርጊቱም መታረም ይገባዋል ።
መጀመሪያ ‹‹ይህ ሲደረግ አይቻለሁ›› ያሉ ሰዎች በኋላ በገንዘብ በመደለልና በመፍራት ቃላቸውን የሚቀይሩባቸው አጋጣሚዎች በርካታ መሆናቸውን፤ ድርጊቱ ሰዎች ከታሰሩና ከተንገላቱ በኋላ የሚፈጠር በመሆኑ በፍትህ ስርዓቱ ላይ ተጽዕኖ ማሳደሩን ፤ እንዲህ አይነት ሁኔታ ሲገጥም ተቋሙ በሀሰት ምስክርነት ክስ መስርቶ እንደሚያስቀጣ አቶ ገብሩ ያስረዳሉ።
አቶ ገብሩ የሀሰት ምስክሩ በሰጠው ቃል በወንጀል ጉዳይ የተፈረደበት ሰው በስህተት በተወሰነበት ቅጣት ልክ ሀሰተኛ መስካሪው ሊቀጣ እንደሚችል የወንጀል ህጉ መደንገጉንና እስከ ዕድሜ ልክ ሊያሳስር እንደሚችል ይገልፃሉ።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
ዘላለም ግዛው