አዲስ አበባ፡- በስፖርት ውርርድ ስም (ቤቲንግ) በሚል በኢትዮጵያ እየተስፋፋ የመጣው ዘመናዊ ቁማር በአንድ ወር ውስጥ የመፍትሔ እርምጃ እንደሚሰጠው የሴቶች፣ ሕፃናትና ወጣቶች ሚኒስቴር አስታወቀ።
በሚኒስቴሩ የወጣቶች ሰብዕና ልማት ዳይሬክተር አቶ አለሙ ሠዒድ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ድርጊቱ ከቅርብ ጊዜ ወዲህ እየተስፋፋ በመሆኑ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በቀጣዩ አንድ ወር ግብረ ሀይል በማቋቋም መፍትሔ ለማምጣት እየሰራ ይገኛል።
ዳይሬክተሩ ‹‹የስፖርት ውርርድ በሚል እየተከናወነ የሚገኘው ድርጊት ቁማር ነው፤ ለችግሩ ዋነኛ መንስዔ የቁማሩ ዓይነት የስፖርት ውርርድ መባሉ ብቻ ሳይሆን ፈቃድ አሰጣጡ ነው። በአገሪቱ ለአደንዛዥ ዕፅ ንግድም ፈቃድ ይሰጣል። ይህም ፈቃድ ሰጪ አካል ዘንድ ከፍተኛ ክፍተት መኖሩን ያሳያል›› ብለዋል።
‹‹ትንሽ ብር ከፍለው በመቶ ሺዎች ማግኘት ይችላሉ›› በሚል ከአቋማሪዎቹ የሚነገረው አሳሳች ማስታወቂያ ለአገሪቱም ሆነ ለወጣቶች ጠቀሜታ የሌለው ጎጂና የነበሩ እሴቶችንና ባህሎችን የሚሸረሽር፣ ጤናማ ሕይወታቸውን አልፎም የማህበረሰቡን ኢኮኖሚ የሚጎዳ መሆኑን ዳይሬክተሩ አስረድተዋል።
ድርጊቱ በተለያዩ የዓለም አገራት የተለመደ ቢሆንም እንደ ኢትዮጵያ ላለ ታዳጊ አገር በወጣቶች ላይም ሆነ በአገር ደረጃ ጠቀሜታ የለውም ፤ወጣቶች የራሳቸው ገቢ ሳይኖራቸው በዚህ ተግባር ላይ መግባታቸው ለመስረቅና ተያያዥ ወንጀሎችን ለመፈጸም በር ይከፍታል ያሉት ዳይሬክተሩ፤ በቤተሰብ ደረጃ ሠላም እንዳይኖርና መልካም ግንኙነት እንዲሻክር በማድረግ ግጭትን እንደሚያስከትል፤ ለአገር ፀጥታም ስጋት እንደሚሆን ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለፃ፤ በየትኛውም የንግድ እንቅስቃሴ ፈቃድ ሲሰጥ ዘርፉ ለአገሪቱ ያለው መልካም ገፀ በረከትና ጉዳት በሚገባ ሊመረመር ቢገባም ይህ ተግባራዊ ሲደረግ አይታይም። ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ በሚሰበስበውና የባህልና ቱሪዝም ሚኒስቴርን ጨምሮ 26 አጋር አካላት የተካተቱበት ግብረ ኃይል ተቋቁሞ እየሠራ ነው።
ዳይሬክተሩ ‹‹ በአገር አቀፍ ደረጃ አሉታዊ መጤ ልማዳዊ ድርጊቶችንና አደንዛዥ ዕፆችን የመከላከል ግብረ ኃይሉ በፌዴራል ደረጃ 26 የመንግሥት ተቋማት፣ ሲቪክ ማህበራት፣ የሃይማኖት ተቋማት እንዲሁም የሚመለከታቸው አካላትን በአባልነት ያቀፈ ሲሆን፤ ሥራው ከተጀመረ ሁለት ዓመት አስቆጥሯል። ግብረ ኃይሉ ይህን መሰል የወጣቶችን ሕይወት፣ ጤና፣ ሥነ ምግባርና ስብዕናቸውን ሊጎዱ የሚችሉ ተግባራት በመከላከል ላይ ያተኩራል›› ብለዋል።
ግብረ ኃይሉ በዓመት ሁለት ጊዜ ጠቅላላ ጉባዔውን እንደሚያደርግና በመጪው ጥር ወር ከሚያካሂደው መድረክ በፊት የቴክኒክ ኮሚቴው ጉዳዩን እንዲያውቀው በማድረግና ሰፊ ውይይት ተደርጎበት ከሚመለከታቸው አካላት ጋር ችግሩን ለማቃለል ጥረት እንደሚደረግ ዳይሬክተሩ አመላክተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
ፍዮሪ ተወልደ