አዲስ አበባ:- የድሬዳዋ ከተማ አስተዳደር በሩብ ዓመቱ ለስድስት ሺ 117 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠሩ ተገለጸ። በበጀት ዓመቱ ለ19 ሺ 864 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ ነውⵆ
የከተማ አስተዳደሩ የሥራ ዕድል ፈጠራና ምግብ ዋስትና ኤጀንሲ ዳይሬክተር አቶ ማርቆስ ባዩህ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤የከተሞች የሥራ አጥ ቁጥር ለመቀነስ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተቀመጠላቸው አቅጣጫ በበጀት ዓመቱ ለ19ሺ 864 ወጣቶች የሥራ ዕድል ለመፍጠር እየሠራ ሲሆን፤ በሩብ ዓመቱ ለስድስት ሺ 117 ወጣቶች የሥራ ዕድል መፍጠር ችሏል።
እንደ ዳይሬክተሩ ማብራሪያ፤ የፌዴራል የሥራ ዕድል ፈጠራ ኮሚሽን እ.ኤ.አ በ 2018 ባጠናው ጥናት የከተሞች የሥራ አጥ ቁጥር በአማካኝ ወደ 19 በመቶ ከፍ ብሏል። በድሬዳዋ 25 በመቶ የሚሆኑ ነዋሪዎች ሥራ አጥ ከመሆናቸው ጋር ተያይዞም በ 2012 ዓ.ም በከተማዋ የተንሰራፋውን ሥራ አጥነት ለመቅረፍ የተለያዩ ሥራዎች ተሠርተዋል።
‹‹በመጀመሪያው ሩብ ዓመት የሥራ ዕድል ሊፈጥሩ የሚችሉ ተቋማትን አቀናጅቶ መምራት የሚያስችል አምስት ንዑሳን ኮሚቴ ያሉት የሥራ ዕድል ፈጠራ ምክር ቤት ተቋቁሟል›› ያሉት አቶ ማርቆስ፤ በከተማዋ በሚገኙ ዘጠኝ ቀበሌዎች በተደረገ የሥራ ፈላጊዎች ምዝገባ ከ12 ሺ በላይ ወጣቶች በመመዝገብና ከድሬዳዋ ዩኒቨርሲቲ ጋር በመተባበር ለሥራ አጥ ዜጎች የሥራ ዕድል መፍጠር የሚችል ተፈጥሮ ሀብት መኖሩ በጥናት መረጋገጡን ጠቁመዋልⵆ
ዳይሬክተሩ ከሚታወቁ አምስት ወይም አራት የሥራ ዘርፎች ባሻገር 70 በሚደርሱ የሥራ ዕድል አማራጮች ላይ የግንዛቤ ማስጨበጫ ስልጠና በመስጠት በመንገድ ፕሮጀክት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በንግድ፣ በከተማ ግብርና፣ በቱሪዝምና በጋራ መኖሪያ ቤቶች ግንባታ ተደራጅተው እንዲሠሩ እየተደረገ እንደሚገኝ ጠቅሰው፤ መንግሥታዊ እና መንግሥታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች ቋሚ ሥራ እንዲያገኙ በማመቻቸት በሩብ ዓመቱ ለ ስድስት ሺ 117 ሥራ ፈላጊዎች የሥራ ዕድል መመቻቸቱን ገልጸዋል።
በመጀመሪያው ሩብ ዓመት ለዜጎች የተሻለ የሥራ ዕድል ለመፍጠር የሚያስችሉ አደረጃጀቶች ቢከናወኑም በከተማዋ የተከሰተው የጸጥታ መደፍረስ በሩብ ዓመቱ የታቀደውን ያህል የሥራ ዕድል እንዳይፈጠር እንቅፋት መሆኑን ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
ሶሎሞን በየነ