ኢትዮጵያ በዓለም አቀፍ ደረጃ በቀንድ ከብቶች ሀብታም ተብለው ከአንድ እስከ አስር ደረጃ ከተሰጣቸው አገራት አንዷ ሲያደርጋት፤ ከአፍሪካ ደግሞ በቀዳሚነት እየመራች ነው። ይህ መሆኑ በገጠርም ይሁን ትናንሽ ከተሞች ላይ ያሉ ነዋሪዎች አኗኗራቸውን ከእንስሳት ከሚገኝ ውጤት ጋር የተቆራኘ አድርገዋል።
አሁን ላይ 60 ሚሊየን የሚጠጉ የቀንድ ከብቶች ባለቤት እንደሆነች የሚነገርላት አትዮጵያ ባላት ሀብት መጠቀም አልቻለችም። እርሻ ሚኒስቴር ከክልል ተጠሪ ተቋማትና ግብርና ቢሮዎች ጋር የ 2012 ዓ.ም ሩብ ዓመት እቅድ በገመገመበት ወቅት የእርሻ ሚኒስቴር ሚኒስትር ዴኤታው ዶክተር ገብረእግዚአብሔር ዮሀንስ ዘርፉ የመንግሥትን ኢንቨስትመንት ካላገኘ ከዘርፉ የሚገኘው ገቢ ከዚህም በላይ ዝቅ ሊል ይችላል ብለዋል።
እንደ ሚኒስትር ዴኤታው ገለጻ ግብርና በአገራችን ሊሟሉለት የሚገቡ ጉዳዮች ሳይሟሉለት በጥቂቱም ቢሆን ምርት የሚሰጥ ዘርፍ ነው፡፡ የመንግሥት የኢንቨስትመንት ውስንነት ስላለበት ዘርፉ ከፍተኛ ችግር ውስጥ ገብቷል። አርብቶ አደሩ ለውጭ ንግዱ እንስሳትን ያቀርባል ብለን የምናስብ ቢሆንም ካሉት 142 ወረዳዎች በተለያዩ ፕሮጀክቶች እየተደገፉና ምርታማ እየሆኑ ያሉት 60 ብቻ ናቸው። በተጨማሪም ለዘርፉ እድገት አንድ ዕርምጃ ይሆናሉ ተብለው የተጠበቁ እንደ ቦረና የእንስስት ማቆያና የከብቶች በሽታ የቁጥጥር ሥራዎች ተጀምረው ሳይጠናቀቁ መቅረታቸው ዘርፉ በከፍተኛ ሁኔታ እየተጎዳ ነው፡፡
ሚኒስትር ዴኤታው፤ ጥምር ግብርና በሚከ ናወንባቸው አካባቢዎች ላይ ወተትና ዕንቁላልን ከገበያ ጋር ለማስተሳሰር ምርት ማሰባሰቢያ፣ ማከማቻ፣ ማቀዝቀዣ እንዲሁም ሌሎች መሰረተ ልማቶች እንደሚያስፈልጉ ጠቅሰው፤ መሰረተ ልማቱ በራሱ ትልቅ ኢንቨስትመንት ስለሚፈልግ መንግሥት በእንስሳት ሀብቱ ላይ ትኩረት አድርጎ መሥራት እንደሚጠበቅበት አመልክተዋል።
በከተሞች አካባቢ መሬት ለማንኛውም አገልግሎት ሲፈለግ እንስሳት ያሉበት ቦታ እንዲነሳ ስለሚደረግ ፤ ያለው የመሬት ሊዝ የእንስሳትን ባህርይ ታሳቢ ያላደረገ በመሆኑ ለዘርፉ የሚሆን መሬትን ማስፋፋት እንዲቻል ትኩረት ሊሰጠው እንደሚገባ ሚኒስትር ዴኤታው አሳስበዋል።
የእንስሳት ዘርፉ ለኢንቨስትመንት ሳቢ እንዲሆን ባለሀብቱ ከመጣ በኋላ መሬት እየተፈለገ የሚሰጥበትን አሠራር መቀየርና ክልሎች ለእንስሳት ሀብት የሚመጥኑ መሬቶችን ለይተው በማዘጋጀት አልሚውንም ማበረታታት እንዳለባቸው ጠቁመዋል።
የልማት ሠራተኞች የአቅም ውስንነትና በሥራው ላይ ለመቆየት ፍላጎት ማጣት ከፍተኛ ተግዳሮት በመሆኑ የማበረታቻ ስርዓትን መፈተሽ እንደሚያስፈልግ የሚናገሩት ሚኒስትር ዴኤታው፤ በቀድሞው ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማሪያም ደሳለኝ አማካይነት ይካሄድ የነበረው “ የእንስሳት ልማት ንቅናቄ መድረክ” አሁን ላሉት አመራሮች በማዘጋጀት ሁሉም ዘርፉን ሊያውቁትና ሊደግፉት እንደሚገባ አስረድተዋል።
የጋምቤላ ክልል እርሻና ተፈጥሮ ሀብት ቢሮ ኃላፊ ዶክተር ሎው ኡቡፕ ‹‹ በክልሉ ለእንስስት ጤና ከፍተኛ ትኩረት ተሰጥቶ እየተሠራ ቢሆንም፤ ባለፈው ክረምት አካባቢው በከፍተኛ ጎርፍ ስለተጎዳ እንስሳቱም ጉዳት ደርሶባቸዋል›› ብለዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ፤ በክልሉ መንግሥት ልዩ ውሳኔ ለተጎዱት አርብቶ አደር አካባቢዎች የተለያዩ መድኃኒቶችንና ግብዓቶችን በመግዛት ዕርዳታ እንዲያገኙ የማድረግ ሥራ ሠርቷል፤ የእንስሳት ሀብቱን በመንከባከብና ለአገር የሚያስገኙትን የውጭ ምንዛሪ በተገቢው ሁኔታ ለመሰብሰብ እየተሠራ ይገኛል።
ለእንስሳት ዘርፉ የተሰጠው ትኩረት በጣም አነስተኛ መሆኑን የገለጹት ኃላፊው ‹‹ያለን ሀብት ብዙ ቢሆንም አልተጠቀምንበትም፤ ባለን ልክ መሥራት ችለን ቢሆን ኖሮ ከወተት፣ ከስጋና ከሌሎች ምርቶች ከፍተኛ ተጠቃሚ እንሆን ነበር›› ብለዋል።
ኃላፊው መንግሥት ዘርፉ ላይ ኢንቨስት ካለማድረጉም በላይ ለአልሚዎች እየሰጠ ያለው ማበረታቻ ዝቅተኛ በመሆኑ ከዚህ በበለጠ ኪሳራ ውስጥ እንዳይገባ ትኩረት ሰጥቶ መሥራት እንደሚያስፈልግ ተናግረዋል፡፡
የድሬዳዋ አስተዳደር የግብርና ውሃ ማዕድንና ኢነርጂ ቢሮ ኃላፊ አቶ ኡመር አህመድ በበኩላቸው፤ በአካባቢው አርብቶና ከፊል አርብቶ አደሮች ስላሉ የሚፈለገውን ያህል ባይሆንም እንስሳትን በመንከባከብ፣ ከተሻሻሉ ዝርያዎች ጋር በማዳቀል የመኖ አቅርቦትና ህክምና ላይ አተኩሮ በመሥራት የተሻለ ውጤት ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
እንደ ኃላፊው ገለጻ ፤ ዘርፉ ካለው ሀብትና ሊያስገኝ ከሚገባው ገቢ አንጻር እየተሠራ ያለው በቂ ነው ሊባል አይችልም፤ መንግሥት በልማቱ ተሳትፎ ማድረግ አለበት፤ የእርሻ ሚኒስቴርም ጉዳዩ በቀጥታ ስለሚመለከተው ለሚቀርቡለት ጥያቄዎች አፋጣኝ ምላሽ በመስጠት ተባባሪነቱን ሊያሳይ ይገባል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
እፀገነት አክሊሉ