የኢትዮጵያ መንግሥት ለሚያካሂዳቸው ሀገር በቀል የኢኮኖሚ ማሻሻያዎች ተጨማሪ የገንዘብ ድጋፎች ቃል መገባቱ እየተነገረ ይገኛል፡፡ እንደ ሮይተርስ ዘገባም፤ ኢትዮጵያ ከዓለም ባንክ የሶስት ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ቃል በተገባላት በሁለተኛው ቀን የዓለም የገንዘብ ድርጅት በበኩሉ በሦስት ዓመት ውስጥ የሁለት ነጥብ ዘጠኝ ቢሊየን ዶላር ድጋፍ ለማድረግ መስማማቱን ዘግቧል፡፡ ባለሙያዎች የተገኘው ብድርና ድጋፍ ተስፋም ስጋትም እንዳለው እየገለጹ ናቸው፡፡
የማክሮ ኢኮኖሚክስ ባለሙያው ዶክተር እዮብ ተስፋዬ፤ አለም አቀፍ የገንዘብ ተቋማትና ለጋሽ ድርጅቶች ገንዘብ ለመስጠት የገቡት ቃል በኢኮኖሚ ማሻሻያው ላይ ያላቸውን እምነት ያሳያል ባይ ናቸው፡፡ አይኤም ኤፍ ከኮታ በላይ ብድር እንደማይሰጥ ያመለክታሉ፡ ፡ ለኢትዮጵያ የተሰጠው ከ700 በመቶ በላይ እጥፍ መሆኑንም ይጠቁማሉ፡፡
ዶክተር እዮብ እንደሚያብራሩት፤ የገንዘብ ተቋማቱ የሰጡት ብድርና የለጋሽ አገራት ድጋፍ ኢንቨስትመንት የመሳብ አቅምን ይጨምራል፡፡የውጭ ባለሃብቶች የማክሮ ኢኮኖሚን ስለሚከታተሉ የውጭ ምንዛሬ ባለበት ይሳባሉ፡፡ይህም ተጨማሪ የልማት አቅምን እንደሚፈጥር ያመለክታሉ፡፡
የኢኮኖሚ ተንታኙ አቶ ሸዋፈራሁ ሽታሁን፤ የተገኘውን ብድርና ድጋፍ እንደመልካም አጋጣሚ ይመለከቱታል፡፡ የማክሮ ኢኮኖሚ መዛባትን እንደሚያስተካክል፣ የዕዳ ጫና፣ የዋጋ ግሽበትና ስራ አጥነት ችግሮቹን በተወሰነ ደረጃ ለመሸፈን ግልጋሎት ላይ ሊውል እንደሚችልም እምነታቸውን ይገልጻሉ፡፡የዕዳ ጫና፣ የወጪ ንግድ ቀውስ፣ የዋጋ ግሽበትና ስራ አጥነትን አደብ ለማስገዛት እንደሚጠቅም ይጠቁማሉ፡፡
በሶስት ዓመታት መስተካከል ያለባቸው ነገሮች እንዳሉ የሚናገሩት ዶክተር እዮብ፤ ቀደም ሲል ገንዘብን በከፍተኛ ሁኔታ ኢኮኖሚው ውስጥ በመርጨት ‹‹ዕድገት እናመጣለን›› በሚል የተሄደበት መንገድ የፈጠረውን ምስቅልቅል ማስተካከል ይገባል ይላሉ፡፡የውጭ ምንዛሬና የገንዘብ ፖሊሲውን እንደገና መፈተሽ፣ግሽበትን መቆጣጠርና የውጭ ምንዛሬ ክምችቱንም ማጎልበት እንደሚጠይቅም ያመለክታሉ፡፡ ተግባሮቹ ኢኮኖሚውን ከሰባት እስከ ስምንት በመቶ ሊያሳድገው እንደሚችልም ይጠቁማሉ፡፡
በትግበራው ቋሚ ገቢ ያላቸውና ጡረተኞች እንዳይጎዱ መንግስት ጥንቃቄ እንዲያደርግም የሚያመለክቱት ዶክተር እዮብ፤ የማክሮ ኢኮኖሚው ሳይዘነጋ የግብርና ምርትና ምርታማነትን ማሳደግ እንደሚገባ ይጠቁማሉ፡፡የሪፎርም ፕሮግራሙ ማስተካከያ ሲደረግ ኢኮኖሚው እንደቀድሞው በ10 በመቶ ላያድግ ስለሚችል በታሳቢነት ስራ ፈጠራ ላይ ርብርብ ማድረግ እንደሚገባም ያሳስባሉ፡፡
አቶ ሸዋፈራሁ በበኩላቸው፤ ለስኬቱ መንግስት ጠበቅ ያለ የበጀትና የገንዘብ ፖሊሲ በመከተል የገንዘብ ብክነትን መከላከልና ገንዘብ ወደ ገበያ እንዳይረጭ ማድረግ ይገባዋል ይላሉ፡፡
ኢትዮጵያ የአይ ኤም ኤፍን ድጋፍ ለማግኘት እንደ ቅድመ ሁኔታ ከተቀመጠው የምንዛሬ ተመን በገበያ እንዲወሰን ለማድረግ መስማማቷን እንደሰሙ የሚጠቁሙት አቶ ሸዋፈራሁ፤ ምንዛሬ በገበያ እንዲመራ ቢደረግም በኢትዮጵያ ንግድ ባንክ አማካኝነት ለህብረተሰቡ በማቅረብ የግል ባንኮች በተመሳሳይ ዋጋ እንዲሸጡ ሚዛኑን ማስጠበቅ እንደሚገባም ይጠቁማሉ፡፡
የውጭ ምንዛሬ በገበያ ሲወሰን ወደጥቂቶች እንዳይገባ፣ የማክሮ ኢኮኖሚው እንዲያገግም በገንዘቡ ላይ የባለሙያዎች ቁጥጥርና ግምገማ እንደሚያስፈልግ፣ፖለቲካው ሲታመም ኢኮኖሚው እንዳይጎዳ ሁለቱን መነጣጠል እንደሚያስፈልግም ያሳስባሉ፡፡
ዶክተር እዮብም ይህ ሁሉ ገንዘብ ሲሰጥ መስተካከል የሚገባቸውን ነገሮች ለማስተካከል ድርድር ተካሂዶና ስምምነት ተደርሶ መሆኑን ይጠቅሳሉ፡፡ በመጀመሪያው ዓመት ስራዎቹ ካልተጀመሩ የቀጣዩ ዓመት ገንዘብ እንደማይገኝም ይጠቁማሉ፡፡ለገንዘቡ መለቀቅ ብቻ ሳይሆን ለኢትዮጵያ ኢኮኖሚም ወሳኝ መሆኑን ተገንዝቦ መንግስት ለአገር በቀል የምጣኔ ሃብት ማሻሻያ ትግበራ ማድረጉንም ያመለክታሉ፡፡ገንዘቡን ባግባቡ ጥቅም ላይ በማዋል የሚፈለገውን ውጤት ለማምጣት ጠቅላይ ሚኒስትሩ በልዩ ሁኔታ ትኩረት በሚሰጡት መንገድ መፈጸም እንዳለበትም ይመክራሉ፡፡
የኢትዮጵያ ኢኮኖሚ የሚንቀሳቀሰው በጥቂቱ ከሚገኘው የወጪ ንግድ፣ ከሬሚታንስ፣ በአብዛኛው በውጭ ብድርና እርዳታ መሆኑንም ያስታውሱና፤ በተወሰዱ በርካታ ብድሮች የስኳር ፋብሪካዎችን፣ የኢንዱስትሪ ፓርኮችን፣ የባቡር መስመሮችን በመዘርጋት በመጀመሪያው የእድገትና ትራንስፎርሜሽን እቅድ ማብቂያ ከወጪ ንግድ 10 ቢሊዮን ዶላር ለማስገኘት ታስቦ እንደነበረ ይጠቁማሉ፡፡ ሆኖም የውጭ ምንዛሬ ያስገኛሉ የተባሉት ፕሮጀክቶች የዕዳ ጫና ማባባሳቸውን ይጠቅሳሉ፡፡
189 አባል አገራትን በአባልነት ያቀፈው የአለም አቀፉ የገንዘብ ተቋም (IMF) የተቋቋመው እ.ኤ.አ 1945 ነው፡፡ ተቋሙ በየጊዜው የባለሙያዎች ቡድን ወደአባል አገራቱ ይልካል፡፡ከሚመለከታቸው አካላት ጋርም በመምከር ለአገሪቱ መሰጠት የሚገባውን ብድርና ፈንድ ይወስናሉ፡፡ የኢትዮጵያን የኢኮኖሚ እንቅስቃሴ በተለምዶ «Article 4 consultation» ምክክርም የእዚሁ አካል ነበረ፡፡
ኢኮኖሚው የሚንቀሳቀሰው በውጭ ምንዛሬ በመሆኑ የብድር ጫናው ቢበዛም ተጨማሪ ብድር ወስዶ ከመንቀሳቀስ ውጪ ሌላ አማራጭ የለም፡፡ በውጭ ግብይት፣ በማኑፋክቸሪንግ፣ በኢንዱስትሪና በግብርና ዘርፎች ከተሰራ ዕዳው በሂደት ይቃለላል፡፡ኢንቨስትመንት ስለሚስብም የውጭ ምንዛሬ ማፍራት ያስችላል፡፡በሂደት የውጭ ዕዳ ጫናውን ማቃለል ያስችላል ይላሉ ዶክተር እዮብ፡፡
ገንዘቡን በአዋጭ ፕሮጀክቶች ላይ በማዋል ከትርፉ በየጊዜው እየተከፈለ ዕዳውን የማቃለል ስልት መከተል ይገባል፡፡ሂደቱን ባግባቡ መምራት ካልተቻለ የማክሮ ኢኮኖሚው መዛባት ይባባሳል፡፡የዋጋ ንረት፣የበጀትና የንግድ ሚዛን ጉድለት፣የገቢ ኢፍትሃዊነት ሊሰፋ ይችላል፡፡ኢኮኖሚው ከተዳከመ የውጭ ዕዳ ጫና ሊጨምር ይችላል፡፡በመሆኑም ዴሞክራሲያዊ ሁኔታን ማስፈን፣በቋንቋና በመሬት ላይ የተመሰረተ ፖለቲካን ትቶ ዜጎች በሚያዋጣቸው ቦታ እንዲንቀሳቀሱ ማድረግ ያስፈልጋል፡፡
ኢንቨስትመንትን በመሳብ ከውጭ የሚገባ ካፒታል መፍጠር፣ ገንዘቡን በማኑፋክቸሪንግ፣በግብርና ኢንቨስትመንት ማዋል ከተቻለ ብድሩን ለመመለስ፣ ስራ አጥነትንና ዋጋ ግሽበቱን አደብ ለማስገዛት ያስችላል ይላሉ – አቶ ሸዋፈራሁ፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
ዘላለም ግዛው