አዲስ አበባ፡- በ2012 በጀት ዓመት ለ700 ኢንዱስትሪዎች ሽግግር ለማድረግ መታቀዱን የፌዴራል አነስተኛና መካከለኛ ማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ማስፋፊያ ባለሥልጣን ገለፀ። በ2012 ሩብ ዓመት ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ 23 እንዲሁም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ሁለት ኢንዱስትሪዎች ሽግግር ማድረጋቸው ተጠቁሟል።
በባለሥልጣኑ የኢንቨስትመንት ፕሮሞሽንና ኢንዱስትሪዎች ሽግግር ዳይሬክተር አቶ ከላሊ ወልደገብርኤል ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ በ2011 ዓ.ም ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ እንዲሁም ወደ ከፍተኛ ደረጃ 467 ኢንዱስትሪዎች ሽግግር አድርገዋል። ይህንን መነሻ በማድረግ በተሠራ ሥራ በ2012 ለ700 ኢንዱስትሪዎች ሽግግር ለማድረግ በመታቀዱ፤ በሩብ ዓመቱ ከአነስተኛ ወደ መካከለኛ 23 እንዲሁም ከመካከለኛ ወደ ከፍተኛ ሁለት ኢንዱስትሪዎች ሽግግር ማድረግ ችለዋል።
ዳይሬክተሩ በአብዛኛው ለፍጆታ የሚውሉ ከውጭ የሚገቡ ምርቶች በአገር ውስጥ ምርቶች እንዲተኩ ለማኑፋክቸሪንግ ዘርፉ ትኩረት መሰጠቱን ገልጸው፤ወደ አገር ከሚገቡ ምርቶች ይልቅ ወጪ ምርቶችን ማብዛት ስኬታማ እንደሚያደርግ፣ የውጭ ምንዛሬን እንደሚያድንና በዓለም ገበያ ተወዳዳሪ የሆነ ምርት በማቅረብ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት እንደሚቻል ጠቁመዋል።
ባለፈው ዓመት የሥራ አፈፃፀም ላይ የተስተዋሉ መልካም ተግባራትና ተግዳሮቶች ተለይተው እንደ መነሻ መወሰዳቸውን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፤ በተለይም አንዳንድ የኢንዱስትሪ አንቀሳቃሾች ከመንግሥት የሚደረገውን የማምረቻና መሸጫ ቦታ እንዲሁም መሠል ድጋፎች ለማግኘት ሲሉ መስፈርቱን ሳያሟሉ እንዳሟሉ አድርጎ የማቅረብ አዝማሚያዎች መከሰታቸውን ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ ባለሙያዎች ይህንን መሰል ድርጊት ለመከላከልና ለመቆጣጠር ከደረጃ ሽግግር ጋር በተያያዘ በባለሙያዎች ላይ የግንዛቤና የክህሎት ክፍተት ቢስተዋልም ሆነ ተብሎ የሚፈፀም እንዳልሆነ ገልፀው፤ ኢንዱስትሪዎች ካፒታል አሟልተናል ብለው ሲገልጹ አስፈላጊው ፍተሻ ሳይደረግ በግምት መሥራት ለችግሮች መነሻ እንደነበሩ አመልክተዋል።
ባለሥልጣኑ ለሽግግሩ ከቁጥር ባሻገር ምን ዓይነት ስራ እንደተሰራ ፣ ትክክለኛ ሂደቱንና መስፈርቱን የጠበቀ መሆኑን ማረጋገጥ የሚያስችል የሥራ አፈፃፀምና የሪፖርት የአሰራር ሥርዓት መዘርጋቱን የገለጹት ዳይሬክተሩ፤ ባለሙያዎችን ተከታታይነት ባላቸው ገንቢ ሥልጠናዎች የማብቃትና ችግሮችን ማቃለል የሚያስችል ስራ እየተከናወነ እንደሚገኝ ጠቁመዋል።
እንደ ዳይሬክተሩ ገለጻ ፤ ዘመናዊ ኢንዱስትሪዎች እንዲፈጠሩ ያላቸው አቅም መነሻ ተደርጎና በሒሳብ መዝገብ የተረጋገጠ ሽግግር እንዲኖራቸው እየተሰራ ይገኛል ። የግምት አሠራር እንዳይኖርና ኢንዱስትሪዎች አቅማቸው የተለካና በኦዲት የተረጋገጠ እንዲሆን የሚያስችል ስራ እየተከናወነ ነው። መልካም ጅማሮውን አጠናክሮ ለማስቀጠልም የሚመለከታቸው ባለድርሻ አካላት ትብብር ሊያደርጉ ይገባል ።
ባለሥልጣኑ በ 2008 ዓ.ም መጨረሻ ተደራጅቶ 2009 ዓ.ም ራሱን ችሎ ሥራ በመጀመሩ በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ በአነስተኛና መካከለኛ ደረጃ ላይ 15 ሺህ ኢንዱስትሪዎች ይገኛሉ። ከዚህም ውስጥ በሁለተኛው ዕድገትና ትራንስፎርሜሽን ዕቅድ በአጠቃላይ ለሦስት ሺህ ኢንዱስትሪዎች ሽግግር ይደረጋል በሚል እቅድ ተይዟል።
ከተቋሙ የተገኘው መረጃ እንደሚያመለክተው፤ በሩብ ዓመቱ በቀጥታም ሆነ ቀጥተኛ ባልሆነ መንገድ ለውጭ አገር ገበያ አንድ ሚሊየን 862 ሺህ 502 ነጥብ 94 ኪሎ ግራም የማኑፋክቸሪንግ ኢንዱስትሪ ምርቶችን ዋና መዳረሻ ለሆኑት አሜሪካ፣ ፊንላንድ፣ ስፔን፣ ካናዳና ሌሎች አገራት በማቅረብ ሁለት ሚሊየን 727 ሺህ 855 ዶላር ማግኘት ተችሏል።
በተያያዘ በሩብ አመቱ በአገር ውስጥ ለ 1087 ኢንዱስትሪዎች 94 ሚሊየን 549 ሺህ 455 ብር ማስገኘት የሚያስችል የገበያ ትስስር መፍጠር የተቻለ ሲሆን፤ ክልሎችና ከተማ አስተዳደሮች በተገቢው ሁኔታ አቅደው በመንቀሳቀስ ለኢንዱስትሪዎች የገበያ ትስስር ለመፍጠር ተገቢውን ስራ አለመስራታቸው፤ በየአካባቢው ግጭት እየተበራከተ መምጣቱ፤ በፌዴራል ደረጃ በቂ ክትትልና ድጋፍ ማድረግ አለመቻሉና የተናበበ መዋቅር አለመዘረጋቱ ለአፈጻጸሙ ዝቅተኛ መሆን ምክንያት መሆናቸው ተጠቅሷል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
ፍዮሪ ተወልደ