አዲስ አበባ፡- በኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎችና ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶች ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ከፍተኛ ታክስ እንዲጣልባቸው የሚያደርግ ድንጋጌ መቀመጡ ተጠቆመ። ረቂቅ አዋጁ በህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት ውይይት ተደርጎበት ለሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ ተመርቷል።
የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት አምስተኛ ዓመት ስድስተኛ መደበኛ ስብሰባውን ትናንት ሲያካሂድ የመንግስት ረዳት ተጠሪ አቶ ጫላ ለሚ እንደተናገሩት፤ በኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ አዋጅ ውስጥ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች በአካባቢ ደህንነት ላይ የሚያደርሱት ጉዳት እያደገ በመምጣቱ ወደ አገር ውስጥ እንዳይገቡ ለማድረግ ከፍተኛ ታክስ መጣል አስገድዷል። በሌላም በኩል ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶች በተለይ ትንባሆ ላይ ከፍተኛ ታክስ ለመጣል የሚያስችል ማሻሻያ ተቀምጧል።
ከምክር ቤት አባላት ረቂቅ አዋጁ ያገለገሉ ተሽከርካሪዎች፣ ለጤና ጎጂ የሆኑ ምርቶች እንዲሁም የቅንጦት እቃዎች ላይ ከፍተኛ ታክስ እንደሚጣል መቀመጡ መልካም ነገር መሆኑን በመጥቀስ፤ በረቂቅ አዋጁ ላይ ስኳርና ዘይት የቅንጦት እቃዎች መደረጋቸው፣ በመገናኛ ብዙሀን የቪዲዮና የድምፅ ማስተላለፊና መቀበያ፣ የምስልና ድምፅ መቅረጫ፣ የተዘጋጁ ልብሶችና የታሸጉ ውሃዎች ላይ የተጣለውን ከፍተኛ የኤክሳይዝ ታክስ በዝርዝር የሚያየው ቋሚ ኮሚቴ ትኩረት እንዲሰጠው አሳስበዋል።
በሌላ በኩል ምክር ቤቱ የመንግስት የልማት ድርጅቶችን ወደግል ማዘዋወርንና የኢንቨስትመንት ረቅቅ አዋጆችን ለሚመለከታቸው ቋሚ ኮሚቴዎች መርቷል። የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደግል ሲዘዋወሩ ተወዳዳሪና ተደራሽነታቸው፣ የሰራተኞች ሁኔታ፣ የሚሸጡበት የዋጋ ግመታ በተመለከተ አዋጁ ላይ የተቀመጡት ቅድመ ሁኔታዎች ቢታዩ እንዲሁም በከፊልና ሙሉ በሙሉ ወደ ግል የሚዘዋወሩ የልማት ድርጅቶች ዝርዝር በረቂቅ አዋጁ ላይ መካተት እንደነበረበት የምክር ቤቱ አባላት ጥያቄ አንስተዋል። አዋጁን የሚመለከተው ቋሚ ኮሚቴ የተነሱትን ሃሳቦች በአግባቡ እንዲመለከትም አሳስበዋል።
በኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅ ላይ የባለሀብቶች የካፒታል መጠን፣ መሬት ወስደው አጥረው በተቀመጡት ላይ ያለው ተጠያቂነት በተመለከተ፣ የኢንዱስትሪዎች የአየር ብክለት፣ የኢንቨስትመንት ፈቃድ ማደስና ማገድ፣ የውጭ ብድርና የውጭ ምንዛሬን የተመለከተ እንዲሁም የውጭ ዜጎች ቅጥርና የስራ ፈቃድ ዝርዝር ጉዳዮች አለመቀመጣቸውን የምክር ቤቱ አባላት ተናግረዋል።
የኤክሳይዝ ታክስ ረቂቅ፣ የመንግስት የልማት ድርጅቶች ወደግል ማዘዋወር አዋጆች፣ የኢንቨስትመንት ረቂቅ አዋጅ ለገቢዎች፣ በጀትና ፋይናንስ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴና የንግድና ኢንዱስትሪ ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ በዝርዝር እንዲያዩት ተመርቶላቸዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 8/2012
መርድ ክፍሉ