ጎንደር፡- ለተለያየ ልማት ከመንግሥት የወሰዱትን መሬት ከማልማት ይልቅ ለበርካታ ዓመታት አጥረው ያስቀመጡ ባለሀብቶችን መሬት መውሰዱን በአማራ ክልል የጎርጎራ ከተማ መሪ ማዘጋጃ ቤት አስታወቀ።
የማዘጋጃ ቤቱ ዋና ሥራ አስፈጻሚ አቶ ወንዶሰን ዓለም በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደተናገሩት፤ የጣና ሀይቅ በስፋት ከሚያዋስናቸው ወረዳዎች መካከል አንዷ ጎርጎራ ናት። ይህ መልካም አጋጣሚም ከተማዋን ለኢንቨስትመንት ምቹ አድርጓታል።በጣና ሀይቅ ደሴት ላይ በርካታ ጥንታዊ ገዳማት የሚገኙ ሲሆን፣ ከአሥራ ስድስተኛው ክፍለ ዘመን በፊት የነገስታት ከተማ በመሆኗም የበርካታ ጎብኝዎች ቀልብ ትስባለች።
ባለሀብቶች ከ1994ዓ.ም ጀምሮ 23 ባለሀብቶች በሎጅ፣ በዶሮ እርባታ፣ በደን ልማትና በተለያዩ ዘርፎች ኢንቨስትመንት ለመሰማራት በጣና ሀይቅ ዳርቻ ላይ ቦታዎችን መውሰዳቸውን ጠቅሰው፣ ባለሀብቶቹ አጥሮ ከማስቀመጥ ውጪ በተጨባጭ የሚታይ ሥራ እንዳልሰሩ አስታውቀዋል።
ከአንድ ሎጅ በስተቀር እስካሁን ሥራ የጀመረ ባለሀብት እንደሌለም ጠቅሰው፣ ባለሀብቶቹ በወሰዱት መሬት ለበርካታ ወጣቶች የሥራ እድል መፍጠር ሲችሉ ቦታውን አጥረው ማስቀመጣቸውን ገልጸዋል።ባለሀብቶቹ የቦታ ግብር በወቅቱ እንደማይከፍሉ ቦታውን እንደትርፍ ሀብት በመቁጠር የባንክ መበደሪያ እንዳደረጉትም አስታውቀዋል። ‹‹አብዛኛዎቹ ከሀገር ውጭ ከመሆናቸው በተጨማሪም ህጋዊ ተወካይ የላቸውም፣ያላቸውም ስለ ጉዳዩ አያውቁም››ብለዋል።
እንደ ዋና ሥራ አስፈጻሚው ገለፃ፤ ባለሀብቶቹ ወደ ሥራ ገብተው እራሳቸውንና የአካባቢውን ወጣት እንዲጠቅሙ ለማድረግ በተደጋጋሚ ጥሪ ቢደረግላቸውም ምላሽ መስጠት ባለመቻላቸውና ቀርቦ ለመወያየት ባለመፈለጋቸው ግብረ ሀይል በማቋቋም የዘጠኝ ባለሀብቶችን የልማት ቦታ ከተማ አስተዳደሩ ወስዶታል። ለሶስት ባለሀብቶች ደግሞ ማስጠንቀቂያ እንዲደርሳቸው ተደርጓል።
የተቀሩት አሥራ አንድ ባለሀብቶች ሥራ ለመጀመር በዝግጅት ላይ መሆናቸውን ዋና ሥራ አስፈጻሚው ጠቅሰው፣ለእዚህም የክትትልና ድጋፍ ሥራ እየተደረገላቸው መሆኑን ጠቁመዋል።በጊዜ ወደ ሥራ የማይገቡ ከሆነ የልማት ቦታቸው ተነጥቆ ማልማት ለሚችሉ ባለሀብቶች እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
ጎርጎራ ለባህርዳርና ለጎንደር ቅርብና አማካኝ ቦታ ላይ እንደምትገኝ ተናግረው፣ በተለያዩ የኢን ቨስትመንት ዘርፎ ለመሰማራት ፍላጎቱ ላላቸው ባለሀብቶች ጥሪ አቅርበዋል። መንግሥትም ለሚያለሙ ባለሀብቶች መሰረተ ልማቶችን ከማሟላት በተጨማሪ ክትትልና ድጋፍ እንደሚያደርግ ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 30/2012
ሞገስ ፀጋዬ