አዲስ አበባ፡- ትምባሆ ማጨስን አስመልክቶ የተጣለውን ክልከላ የተላለፉና በአዋጁ የተቀመጠውን ያልፈጸሙ ድርጅቶች ላይ እርምጃ መወሰዱን የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድኃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ገለጸ።
በባለስልጣኑ የህዝብ ግንኙነት ኮሙዩኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ አበራ ደነቀ፤ ባለስልጣኑ በወሰደው ርምጃ፤ ትምባሆን ለመቆጣጠር የጸደቀውን አዋጅ ቁጥር 1112/2011 እንዲሁም የከተማ አስተዳደሩ ባወጣው መመሪያ መሰረት ትምባሆና ሺሻ እንዳይጨስ የተቀመጠውን ክልከላ ተግባራዊ ባላደረጉ ድርጅቶች ላይ የማሸግ፣ የገንዘብ ቅጣትና የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ መስጠቱን እንዲሁም ጉዳያቸው ወደ ፍርድ ቤት መተላለፉን ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ባለስልጣኑ በህግ ክልከላ በማድረግ፣ ህጉን በማስፈጸም፣ ስለትምባሆ አስከፊነት ህብረተሰቡን በማስገንዘብ የባህሪ ለውጥ እንዲመጣ በማድረግ ከትምባሆ ጭስ ነጻ የሆነ አካባቢን ለመፍጠር እየተንቀሳቀሰ እንደሚገኝ ተናግረዋል።
የኢትዮጵያ የምግብ፣ መድሀኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ከአዲስ አበባ ምግብ መድሃኒትና ጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን ጋር በመተባበር በቀንና በለሊት የትምባሆ ቁጥጥር መደረጉን ዳይሬክተሩ ተናግረዋል።
እንደ እርሳቸው ማብራሪያ በለሊት ቁጥጥር በተሰራ ስራ የ10 ድርጅቶችን ጉዳይ ወደ ፍርድ ቤት ያስተላለፈ ሲሆን፤ አንድ ድርጅት ታሽጎ በቅጣት እንዲከፈት ተደርጓል። 25 ድርጅቶች ማስጠንቀቂያ ሲጻፍባቸው፤ 59 የሺሻ ዕቃ በመያዝ 35 ሺ 500 የብር ቅጣት መሰብሰብ ተችሏል።
ሶስት ሺ 287 የሚሆኑት ድርጅቶች ላይ በተደረገ መደበኛ ቁጥጥር 587 አዋጁን ተላልፈው በመገኘታቸው የጽሁፍ ማስጠንቀቂያ ሲሰጣቸው፤ ሁለት ድርጅቶች እንዲታሸጉ ተደርጓል።
በ2011 ዓ.ም የጸደቀው አዋጅ ሲጋራና ሌሎች የትምባሆ ምርቶችን ማጨስን አስመልክቶ ክልከላ ማስቀመጡን ያስታወሱት
ዳይሬክተሩ፤ ማንኛውም ህብረተሰብ እንደ ሆቴል፣ ሬስቶራንት፣ ምግብ ቤት፣ የምሽት ቤቶችና በመሳሰሉት ማንኛውም
ድርጅቶች
ከበር መልስ ባሉ ቦታዎች ማጨስ መፍቀድ እንደሌለበት መከልከሉን ጠቁመዋል።
በእነዚህ ቦታዎች በ10 ሜትር ዙሪያ የማጨሻ ቦታ መከለል ወይም ማዘጋጀት እንዲሁም በእነዚህ ቦታዎች ውስጥ የሲጃራ መተርኮሻ ወይም ሌላ የትምባሆ ምርትን ለመጠቀም የሚያገለግል ማንኛውም ዕቃ ማስቀመጥ እንደማይፈቀድም ዳይሬክተሩ አብራርተዋል።
ዳይሬክተሩ ህብረተሰቡ መብቱን እንዲያስከብርና ከባለስልጣኑ ጋር በመተባበር ትምባሆን ለመቆጣጠር የጸደቀውን አዋጅ የማስፈጸም ሃላፊነቱን እንዲወጣ ጠይቀዋል።በአገር አቀፍ ደረጃ የሚገኙ የሚመለከታቸው ተቆጣጣሪ አካላትም ክትትልና ቁጥጥር በማድረግ የወሰዷቸውን እርምጃዎች ለህዝብ ይፋ ማድረጋቸውን እንደሚቀጥሉ ተናግረዋል።
የአለም ጤና ድርጅት በቅርቡ ባካሄደው ጥናት ስምንት ሚሊዮን የሚጠጉ ሰዎች በትምባሆ ምክንያት ይሞታሉ። ከእዚህ ውስጥ ደግሞ አንድ ነጥብ ሁለት ሚሊዮን የሚሆኑት ሁለተኛ አጫሾች ማለትም ትምባሆን በሚያጨሱ ሰዎች ዙሪያ በመገኘታቸው ለጭሱ የተጋለጡ ሰዎች ናቸው።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2012
ዘላለም ግዛው