አዲስ አበባ፡- በኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ዘርፍ የሚስተዋሉ የሙስናና የመልካም አስተዳደር ችግሮችን በመከላከልና በመፍታት ረገድ ውጤታማ ተግባራትን ማከናወኑን የኢ.ፌ.ዴ.ሪ የኬሚካልና ኮንስትራክሽን ግብዓቶች ኢንዱስትሪ ልማት ኢንስቲትዩት አስታወቀ።
የኢንስቲትዩቱ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ዳይሬክተር አቶ ጌታዬ ማሞ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ ኢንስቲትዩቱ ከ2009 ዓ.ም እስከ 2011 ዓ.ም በመልካም አስተዳደርና አገልግሎት አሰጣጥ፣ በኪራይ ሰብሳቢነት ምንጮች እንዲሁም አገር አቀፍ የኢንዱስትሪ ሙስናን የመከላከል ስትራቴጂ ላይ ያተኮሩ ጥናቶችን በማድረግ ሙስናን የመከላከልና መልካም አስተዳደርን የማስፈን ተግባራትን አከናውኗል።
እንደእርሳቸው ገለፃ፣ የኢንስቲትዩቱ የስነ ምግባርና ፀረ-ሙስና ክፍል በስነ ምግባር መርሆዎች፣ በፀረ ሙስናና በጨረታ ሕግጋት፣ በመንግሥት ንብረት አስተዳደር እንዲሁም በመልካም አስተዳደር መርሆች ላይ ያተኮሩ የአመለካከት ግንባታ ስልጠናዎችን በመስጠት ስነ ምግባርን አጎልብቶ ሙስናን በዘላቂነት መከላከል ላይ ያተኮረ ሥራ ሰርቷል።
የተጭበረበሩ ሰነዶችን በመጠቀም ወንጀል ላይ በተሳተፈ ግለሰብ ላይ ሕጋዊ እርምጃ አስወስዷል፤ከመመሪያ ውጭ በሆነ አሰራር ለውጭ ጉዞ አበል ሊከፈል የነበረን ገንዘብ ማዳንና የኢንስቲትዩቱ ንብረት የነበረ መኪና ተዘርፎ ከተደበቀበት ማስመለስ ተችሏል።ከዚህ በተጨማሪም በሦስት ዓመታት ጊዜ የቀረቡለትን ቅሬታዎች በተገቢው ሁኔታ በማጣራት ስህተት የተገኘባቸው እንዲስተካከሉ አድርጓል።
ዳይሬክተሩ የሙስና ምንጮችን በዳሰሳ ጥናት ለይቶ ሕግ እንዲወጣ በማድረግና አገልግሎት አሰጣጥን በማቀላጠፍ የደንበኞችን እርካታ 92 በመቶ ማድረስ እንደተቻለም ጠቁመው፤ ኢንስቲትዩቱ ሙስናን ቀድሞ በመከላከል፤ ችግሮች ከተፈጠሩም በኋላ ለሕግ በማቅረብና የመንግሥትን ገንዘብ በቁርጠኝት በማስመለስ ግንባር ቀደም ተቋም ሆኖ እንደተመረጠ ተናግረዋል።
‹‹ከባለድርሻ አካላት ጋር የሚደረጉ ትብብሮች የፀረ-ሙስና ትግሉ መሰረቶች ናቸው›› ያሉት ዳይሬክተሩ፣ ኢንስቲትዩቱ ከበርካታ ዘርፉ ተዋናዮች ጋር በትብብር እየሰራ እንደሆነ ገልጸዋል።
ለባለድርሻ አካላት ተከታታይ ስልጠናዎችን መስጠት፣ ከኢንስቲትዩቱ ኃላፊነት ጋር ተዛማጅነት ያላቸው የኢንዱስትሪ ታሪፍና የኢንቨስትመንት ሕግጋት በተገቢው መንገድ መተግበራቸውን በጥናት ማረጋገጥና ለክፍተቶች መመሪያ እንዲወጣላቸው ማድረግ የተቋሙ የ2012 በጀት ዓመት ዋነኛ ዕቅዶች መሆናቸውንም ዳይሬክተሩ አስረድተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2012
አንተነህ ቸሬ