ሰኔ አራት ቀን 2010 ዓ.ም ማልደው ከጎጇቸው የወጡት አቶ ኃይሉ አለማየሁ ድርጊታቸው ሥነሥርዓት የተሞላበት ነበርና የመኪና አደጋ የሕይወት ዘመናቸውን አስከፊ ያደርገዋል ብለው አልጠረጠሩም። የእግረኛ መንገድ አክብረው በመጓዝ ላይ ሳሉ ለተሽከርካሪ የተዘጋጀውን መንገድ የሳተ መኪና ቀሪ ሕይወታቸውን አጨለመው እንጂ።
አቶ ኃይሉ፤ ተሯሩጠው ቤተሰባቸውን መመገብ በሚያስችሏቸው ሁለት እግሮቻቸው ላይ በደረሰው የአጥንት ስብራት ሳቢያ ካሰቡት ሳይደርሱ የአካል ድጋፍ (ክራንች) ተጠቃሚ ለመሆን ተገድደዋል።
በተለይ ደግሞ ድርጊቱን የፈፀመው አሽከርካሪ ያለመያዙ ትውስ ሲላቸው ይበግናሉ። በአሁኑ ወቅት ለችግር መጋለጣቸውንም ነው የገለጹት። የትራፊክ አደጋ ሠዎች ካሰቡት እንዳይደርሱ ከማሰናከሉ ባሻገር ተጎጂው እስትንፋሱ ቢቀጥል እንኳ በወደፊት ሕይወቱ ላይ የሚያደርሰው ሥነልቦናዊ፣ ማህበራዊና ኢኮኖሚያዊ ጉዳት ከፍተኛ መሆኑን ይናገራሉ።
የትራፊክ ጥበቃና ቁጥጥር ማስተባበሪያ ኃላፊ ምክትል ኢንስፔክተር አንተነህ ኃይሉ፤ የትራፊክ አደጋን አስከፊ የሚያደርገው ዜጎች ባልጠበቁትና ባላሰቡት ሁኔታ በወጡበት እንዲቀሩ ብሎም ከቀላል እስከ ከባድ የአካል ጉዳት የሚያደርስ መሆኑ ነው። ለቤተሰብና ለወዳጅ ዘመድ ከአዕምሮ ተቀርፆ የሚቀር ትልቅ ጠባሳ ትቶ የሚያልፍ መሆኑም አደጋውን አስከፊ ያደርገዋል። በአሽከርካሪዎችም ላይ አደጋው ከደረሰ በኋላ የሚያስከትለው ሥነልቦናዊ ጉዳት እንዲሁም የሕግ ተጠያቂነት ችግሩ የበርካቶችን በር እንዲያንኳኳ ያደርገዋል።
በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ 80 ከመቶ በላይ አደጋው የሚደርሰው በአሽከርካሪዎች የሥነምግባር ጉዳት ምክንያት መሆኑን የተናገሩት ኃላፊው፤ አደጋዎቹ የሚመነጩት ከፍጥነት በላይ በማሽከርከር፣ ጠጥቶ በማሽከርከር፣ አደንዛዥ ዕፅ ተጠቅሞ በማሽከርከር፣ ለእግረኛ ቅድሚያ ባለመስጠትና ሌሎች ተያያዥ በሆኑ የሕግ መተላለፎች መሆኑን ጠቁመዋል።
በአደጋው 86 በመቶ እግረኞች፣ ዘጠኝ በመቶ ተሳፋሪዎች ሲሆኑ፤ አሽከርካሪዎች አምስት በመቶ ብቻ ጉዳት እንደሚደርስባቸው መረጃዎች ያመላክታሉ። ይህም ዕለት ተዕለት በሚስተዋለው ችግር አሽከርካሪዎች ከፍተኛውን ድርሻ እንደሚወስዱ ነው የገለጹት።
እንደ ምክትል ኢንስፔክተር አንተነህ ገለጻ፤ አሽከርካሪዎች አደጋውን የሚያደርሱት ባለማወቅ ሳይሆን የሚደርሰውን ጉዳት ባለማገናዘብ የሚፈፀሙ ጥፋቶች ናቸው።
ጥፋቶቹ ዕለት ተዕለት የሚከሰቱ በመሆናቸውም ችግሮቹን መላመድና ትክክል እንደሆኑ ማሰብም ይስተዋላል። ችግሩ በሚፈለገው ደረጃ ላለመቃለሉም አሽከርካሪዎች የሚያደርሱት አደጋና የሚጣልባቸው ቅጣት ተመጣጣኝ አለመሆን አንዱ ምክንያት ነው።
ኃላፊው የሕግ ቅጣቱ ተመጣጣኝ አለመሆኑን በቅርቡ በአዲስ አበባ አዲስ ከተማ አካባቢ የነበረ ገጠመኝን በማሳያነት አንስተው ተናግረዋል። አንድ የሕዝብ ማመላለሻ ትራንስፖርት አሽከርካሪ በሥራ ላይ እያለ ባደረሰው አደጋ የሠው ሕይወት ያልፍበታል።
ለእስራት ከበቃ በኋላም ተገቢው የዋስትና መብቱ ተጠብቆለት ከወጣ በኋላ በአንድ ወር ከ15 ቀናት በኋላ በድጋሚ በተመሳሳይ ቦታ ላይ ባደረሰው አደጋ የሠው ሕይወት አልፏል። ይህም በሕጉ ላይ በትኩረት መሠራት ያለባቸው በርካታ የቤት ሥራዎች መኖራቸውን አመላካች መሆኑን ጠቁመዋል።
በትናንትናው ዕለት ‹‹የአሽከርካሪዎች ሥነምግባር የመንገድ ላይ የትራፊክ አደጋ›› በሚል ርዕስ የፐብሊክ ሠርቪስ ሠራተኞች የትራንስፖርት ድርጅት ከትራንስፖርት ሚኒስቴር ጋር በመተባበር በተዘጋጀ የውይይት መድረክ ላይ የፐብሊክ ሠርቪስ ትራንስፖርት አገልግሎት ድርጅት ዋና ዳይሬክተር ወይዘሮ ፍሬሕይወት ትልቁ ‹‹ የትራፊክ አደጋ በርካታ ተስፋ የተጣለባቸውን አገር ተረካቢ ዜጎች የቀጠፈና ካሰቡት እንዳይደርሱ በአጭር ያስቀረ ›› ሲሉ ከቤተሰብ አልፎ በአገር ላይ የሚያደርሰውን ጉዳት ገልፀዋል።
የትራንስፖርት ሚኒስትር ወይዘሮ ዳግማዊት ሞገስ በበኩላቸው፤ ‹‹አደጋው እጅግ አስከፊና ክቡሩን የሠው ልጅ ሕይወት ባልታሰበ ሁኔታ የሚቀጥፍ ነው ።
በተለይም በርካታ አደጋ የሚደርሰው በሕግ ጥሰት በመሆኑ ትኩረት ይሻል። በዚህ ዘርፍ ተሠማርተው የሚገኙ አሽከርካሪዎች፣ እግረኞች፣ እንዲሁም የትራፊክ ፖሊስ አባላትና እያንዳንዱ ዜጋ በየጊዜው የሚደርሰውን ጉዳት ለመቀነስ በሚደረገው ርብርብ የበኩሉን አስተዋፅዖ ማበርከት የገባዋል›› ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
መረጃዎች እንደሚያመላክቱት፤ በትራፊክ አደጋ በ10 ዓመት ውስጥ ከ40 ሺህ በላይ ሠዎች ሕይወታቸው ሲያልፍ፤ በየጊዜው በተሠሩ የግንዛቤ ማስጨበጫ ሥራዎች ደግሞ የመጠነ ሞት ዕድገቱን መቀነስ ተችሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2012
ፍዮሪ ተወልደ