አዲስ አበባ፡- ወጥነት የጎደለውና የተበጣጠሰ የሕግ ማዕቀፍ መኖሩ የምግብ ጥራትና ደህንነት ቁጥጥር ስርዓቱ ደካማ እንዲሆን ማድረጉን የኢትዮጵያ የምግብና መድኃኒት ባለስልጣን አስታወቀ።
በባለስልጣኑ የምግብ ጥራት ምርመራ ዳይሬክተር አቶ ስዩም ወልዴ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፣ የምግብ ጥራትንና ደህንነትን የሚቆጣጠሩ ብዙ ተቋማት ስላሉና ለአንዱ መስሪያ ቤት በሕግ የተሰጡት ኃላፊነቶች በድጋሚ ለሌሎች ተቋማትም ስለተሰጡ በጥራት ቁጥጥሩ ላይ አሉታዊ ተፅዕኖ አሳድሯል። በተቋማቱ መካከል ያለው ቅንጅታዊ አሰራርም ጠንካራ የምግብ ጥራት ቁጥጥርን ለማስፈን የሚበቃ አይደለም።
የምግብ ጥራት ቁጥጥር ስርዓቱ ደካማና በዝቅተኛ ደረጃ ላይ መሆኑን የተናገሩት ዳይሬክተሩ፣ ይህም ጥራትና ደህንነታቸውን ያልጠበቁ ምግቦች ለገበያ እንዲቀርቡ ምክንያት እንደሆነ ገልጸዋል።
ዳይሬክተሩ የምግብ ጥራት ቁጥጥር ሥራ ኃላፊነት በተሰጠው ተቆጣጣሪ የመንግሥት ተቋም ብቻ የሚከናወን ባለመሆኑ ሕገ ወጥ የምግብ ዝውውር ችግርን ለመፍታት አምራቾች ማኅበራዊ ኃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚኖርባቸው፤ በአምራቾችና በተቆጣጣሪ አካላት መካከል መግባባትና ትብብር ሊኖር እንደሚገባም ተናግረዋል።
ዳይሬክተሩ ቀድሞ የኢትዮጵያ የምግብ፣ የመድኃኒትና የጤና ክብካቤ አስተዳደርና ቁጥጥር ባለስልጣን በመባል የሚታወቀውና በርካታ የዘርፉ ተግባራት አንድ ላይ የተከማቹበት መስሪያ ቤት ለውጤታማነት እንዲያመች በአዲስ መልክ መደራጀቱን ጠቁመው፣ አዲሱ አደረጃጀት የቁጥጥር ሥራውን ለማሻሻል ያግዛል ተብሎ እንደሚጠበቅ አመልክተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2012
አንተነህ ቸሬ