አዲስ አበባ፡- በአሁኑ ወቅት በአገሪቱ ያለው የሰብዓዊ መብት አያያዝ ሁኔታ ከዚህ ቀደም ከነበረው በእጅጉ እንደሚሻል፤ እያጋጠሙ የሚገኙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችም በመንግሥት የሚፈጸሙ ሳይሆኑ በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት መሆኑ ተገለጸ።
የኢትዮጵያ
ሰብዓዊ መብት ኮሚሽን ኮሚሽነር ዶክተር ዳንኤል በቀለ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት ፤አዲስ የለውጥ
ምዕራፍ ከመጣ ወዲህ በኢትዮጵያ ውስጥ ያለው አጠቃላይ የሰብዓዊ መብት አያያዝ ከዚህ በፊት ከነበረው በእጅጉ የተሻለ
ሆኗል፤ ለዚህም የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱን፣ የሲቪክ ማህበራት እንቅስቃሴን የሚገድቡ የህግና የፖሊሲ ማዕቀፎች
እንዲሁም የመናገርና ሃሳብን በነጻነት የመግለጽ
መብትን የሚያፍኑ ጨቋኝ ህጎች መሻሻላቸው ነው።
ይህ ማለት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች የሉም ማለት አለመሆኑን የጠቆሙት ኮሚሽነሩ፤ “ይልቁንም እጅግ በጣም አሳሳቢ የሆኑ የሰብዓዊ መብት ጥሰት ችግሮች ገጥመውናል፤ ነገር ግን አሁን እየገጠሙን የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ከዚህ ቀደም ከነበሩት የሚለዩበት ምክንያቶች አብዛኞቹ በመንግሥት የሚፈጸሙ አለመሆናቸው ነው” ብለዋል።
“ከዚህ በፊት በነበሩት(ሁሉም ማለት ይቻላል) የሰብዓዊ መብት ጥሰት ፈጻሚዎቹ መንግሥትና የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ነበሩ” ያሉት ዶክተር ዳንኤል፤ በአሁኑ ሰዓት በኢትዮጵያ እየተፈጸሙ የሚገኙት የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች በመንግሥት ሳይሆን በአገሪቱ ውስጥ በተፈጠሩ የፖለቲካ ግጭቶች ምክንያት የተከሰቱ መሆናቸውን አመላክተዋል።
እንደ ዶክተር ዳንኤል ገለጻ፤ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችን በተመለከተ በአሁኑ ሰዓት በመንግሥት ላይ የሚነሳው ጥያቄ መንግሥት ለዜጎች በቂ የደህንነት ጥበቃ አላደረገም የሚል ነው እንጂ የመንግሥት የጸጥታ ኃይሎች ወይም መንግሥት ራሱ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶቹ ዋነኛ ተዋናይ ነው የሚሉ አይደሉም።
በእርግጥ በአንዳንድ አካባቢዎች በተፈጠሩ ግጭቶችና በተፈጸሙ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶች ውስጥ በተለይም የክልል የጸጥታ ኃይል አባላት በቀጥታ ወይም በተዘዋዋሪ ተሳትፈዋል የሚሉ አቤቱታዎች ለኮሚሽኑ የሚቀርቡ መሆናቸውን የጠቆሙት ዶክተር ዳንኤል ፤ ሁኔታው በከፍተኛ ትኩረት ተይዞ ጥብቅ ማጣሪያ እየተደረገበት መሆኑን ገልጸዋል።
ጥሰቶቹ የሚፈጸሙት በማንም ይሁን በማን ጥፋተኞቹን ተጠያቂ ለማድረግና ለህግ ለማቅረብ ኮሚሽኑ የተቻለውን ሁሉ እያደረገ መሆኑንም ተናግረዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2012
ይበል ካሳ