ላልይበላ፡- የአማራ ክልል ከአራት ዓመት በፊት በከተማው ያስገነባውን የላልይበላ ብሄራዊ የንብ ሀብት ሙዚየም በገንዘብ እጥረት ምክንያት በቁሳቁስ ማደራጀት እንዳልቻለ ተገለጸ።
የክልሉ የእንስሳትና ዓሣ ሀብት ልማት ማስፋፊያ ኤጀንሲ እንዳመለከተው በማር ልማት ዘርፍ የአርሶ አደሮችን አቅም በስልጠና ለመገንባትና ለቱሪዝም መዳረሻነትም በማዋል ገቢ እንዲያመነጭ ታስቦ የህንጻው ግንባታ ቢጠናቀቅም ለውስጥ ቁሳቁስ ማሟያ 80 ሚሊዮን ብር ስለሚያስፈልግና ይህም ከክልሉ አቅም በላይ በመሆኑ የሙዚየሙን የውስጥ ክፍሎች ማደራጀት አልተቻለም።
የኤጀንሲው ሥራ አስኪያጅ አቶ ደበበ አድማሱ እንደገለጹት፣ ክልሉ የሙዚየሙን የውስጥ ክፍሎች በዘመናዊ ቴክኖሎጂ በታገዘ ቁሳቁስ ለማደራጀት ጥረት ቢያደርግም፤ ለቁሳቁስ መግዣ የሚያስፈልገው ገንዘብ ከክልሉ አቅም በላይ ሆኗል። ሙዚየሙ ሊሰጥ ከታሰበው ከፍተኛ አገልግሎት አንጻር የፌዴራል መንግሥትን ጨምሮ ከማር ልማት ጋር በተያያዘ የሚሰሩ አካላት ትብብር ያስፈልጋል ።
በላልይበላ ብሄራዊ የንብ ሀብት ሙዚየም የንብ ሀብት ጥበቃ ምርምር ኤክስቴንሽን አስተባባሪና የሙዚየሙ ተወካይ አቶ አበራ አረቄ ሙዚየሙ በአንድ መቶ ሄክታር መሬት ላይ ያረፈ ሲሆን፣ንብ ማነቢያን ጨምሮ ቤተመጽሐፍት፣ማሰልጠኛና የምርምር ማዕከል፣የተቀነባበረ ማር መሸጫና ማሳያ፣በአንድ ጊዜ 730 እና 110 ሰዎችን የማስተናገድ አቅም ያላቸው የተለያዩ የስብሰባ አዳራሾች፣ 58 ቢሮዎች፣ባህላዊ መመገቢያ ከነማብሰያው፣የንብ አናቢዎች መኖሪያ ቤትና ሌሎችንም ማካተቱን ተናግረዋል።
በዓለም አቀፍ ሥነ ነፍሣት ሣይንስ ሥነ ምህዳር ማዕከል(አይ ሲ አይ ፒ ኢ) ከንብ ማነብ ጋር የተያያዙ ፕሮጀክቶች አስተባባሪ ዶክተር ወርቅነህ አያሌው፣የሙዚየሙ ተልዕኮ ተቋማቸው ወጣቶችን ማዕከል ካደረገው የንብ ማነብ፣ የማርና የሐር ልማት የሥራ ዕድል ፈጠራ ሥራ ጋር እንደሚያያዝ ጠቁመዋል።
እንደ ዶክተር ወርቅነህ ገለጻ፤ ረጅም ታሪክ ያለውን የተከዜ ተፋሰስን ይዞ የሚከናወነውን ንብ ማነብ በማዘመን ከአካባቢ ጥበቃና ከቱሪዝም ኢንዱስትሪው ጋር በማስተሳሰር ቢጠናከር ከዘርፉ ከፍተኛ ገቢ ማግኘት ይቻላል። ተቋሙ ሳይንስን መሰረት ያደረገ የንብ ማነብ ልማት ከሙዚየሙ ጋር ተሳስሮ እንዲከናወን ሙያዊ ድጋፍ ለማድረግ ዝግጁ ነው።
በሙዚየሙ በ60 ባህላዊና ዘመናዊ ቀፎዎች የማነብ ሥራ እየተካሄደ እንዳለ፤ ለ19 ሠራተኞች የሥራ ዕድል መፈጠሩ፤ ባህላዊና ዘመናዊ ማነቢያና ሌሎችም ቁሳቁስ የማሰባሰብ እንዲሁም የስልጠና አደረጃጀቶችን የማዘጋጀት ተግባራት በመከናወን ላይ መሆኑን ለመረዳት ተችሏል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2012
ለምለም መንግሥቱ