‹‹የተከበረችውን አገርህን ከአንድ ምዕራፍ ወደ አንድ ምዕራፍ አሸጋግረሀል!›› ተብሎ በዓለም የክብር መድረክ ላይ ለሽልማት መቆም ምንኛ ያኮራል። እንኳን የራስ የሆነው የአገር ልጅ ይቅርና ኢትዮጵያ ለተሸለመችው ሌሎቹ ተደስተው ሲያወድሱን ከርመው የለ።
የተባበሩት መንግሥታት ዋና ፀሐፊ አንቶኒዮ ጉቴሬዝ “ብዙ ጊዜ የተስፋ ንፋስ በአፍሪካ እየነፈሰ ነው እላለሁ። ለዚህ ደግሞ ዋነኛው ምክንያቴ አብይ አሕመድ ነው። የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ ራዕይ ኢትዮጵያና ኤርትራ ታሪካዊ ስምምነት ላይ እንዲደርሱ አስችሏቸዋል። ባለፈው ዓመት ይህንን ስምምነት ሲፈራረሙ በቦታው በመኖሬ ክብር ተሰምቶኛል።
ይህ አዲስ ምዕራፍም በአካባቢው ደህንነትንና መረጋጋትን የሚያሰፍኑ አዳዲስ ዕድሎችን ከፍቷል። ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ በአመራርነታቸው ለሌሎች የአፍሪካ ሀገራትና ከአፍሪካ ውጭ ላሉ መሪዎችም ግሩም ምሳሌ መሆን ችለዋል” ሲሉ በመልካም ምኞት መግለጫቸው ላይ አስፍረው ነበር።
አዎ! ይህ ውዳሴ ከንቱ አልነበረም፤ የኖቤል ሽልማቱም እንዲሁ። ሽልማቱን ይፋ ያደረጉት የኖቤል ተቋሙ ሊቀመንበር በሪት ራይስ አንደርሰን ‹‹አንዳንዶች ምናልባት ሽልማቱ እጅግ ፈጠነ ሊሉ ቢችሉም የጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ጥረት እውቅናና ማበረታቻ ይገባዋል›› ሲሉ ተደምጠዋል።
አምስት አባላት ያሉት የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ ሰብሳቢ በሪት ‹‹በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለ20 ዓመታት የነበረውን የድንበር ይገባኛል አለመግባባትን ሥልጣን በያዙ በወራት ጊዜ ውስጥ በመፍታት ሰላም አምጥተዋል። በሁለቱ አገሮች መካከል ያለውን ቁርሾም ተወግዶ ለእርቅና ለሰላም በማብቃታቸው የዘንድሮው የ2019 ኖቤል የሰላም ሎሬት ሆነው ተመርጠዋል።›› ሲሉ ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ ሽልማቱን አሸናፊ መሆናቸውን አብስረዋል።
በርግጥም ዶክተር አብይ ወደ ሥልጣን በመጡበት በመጀመሪያው 100 የሥልጣን ቀናት ውስጥ በሀገሪቱ ላይ ተጥሎ የነበረውን አስቸኳይ ጊዜ አዋጅ እንዲነሳ አድርገዋል፣ በሺዎች የሚቆጠሩ የፖለቲካ እስረኞችን ከእስር ፈትተዋል፣ መገናኛ ብዙሃንን በነጻነት እንዲሰሩ ተደርጓል።
የጸረ- ሽብር ህጉ በድጋሚ እንዲታይ ሆኗል፣ በውጭ አገር የነበሩ የተቃዋሚ ፓርቲ አባላት አገር ውስጥ ገብተው በሰላማዊ መንገድ የሚሠሩበትን ሁኔታ ተፈጥሯል፣ በሙስና ሲጠረጠሩ የነበሩት በሕግ እንዲጠየቁ አመቻችተዋል፣ የሴቶች የፖለቲካ ተሳትፎ እንዲጨምር አድርገዋል፣በክልሎች ውስጥ በሚነሱ አለመግባባቶች በባህላዊ የዕርቅ ሥነ – ሥርዓት እንዲፈቱ ሳይታክቱ አወያይተዋል፣በምሥራቅ አፍሪካ ቀጠናዊ ትብብርን በማበረታታት፣ በጎረቤት አገራት መካከል የተፈጠሩ ችግሮችን ለመፍታት የተራራቁትን የማገናኘት ሥራ ሰርተዋል፣ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ዓለም አቀፍ የስደተኞች ሕግጋትን ለማክበር በያዙት አቋም በመላው ዓለም ስደተኞችን እያስተናገዱ ላሉ አገሮች ሁሉ አርአያ መሆናቸው፣ ኢትዮጵያውያን ስደተኞች የልደትና የጋብቻ የምስክር ወረቀቶችን ወስደው የሥራ ፈቃድ እንዲያገኙና የመንጃ ፈቃድ ማውጣት እንዲችሉ መንገድ መክፈታቸው፣ ሱዳን ውስጥ በሽግግሩ ወታደራዊ ምክር ቤት እንዲሁም በነፃነትና
በለውጥ ኃይሎች መካከል ስምምነት ላይ እንዲደረስ በማሸማገል፣ በሶማሊያና በኬንያ መካከል ያለውን የባህር ላይ ይገባኛል ጥያቄ ለመፍታት በማደራደር ያሳዩት ዲፕሎማሲያዊ ጥረት ሚዛን የሚደፋ በመሆኑ ሽልማቱን እንዲያገኙ አስችሏቸዋል።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኖቤል ሽልማቱን ማሸነፋቸው ሲነገር የዓለም አቀፉ የሰብዓዊ መብት ተሟጋች አምነስቲ ኢንተርናሽናል ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አህመድ እ.ኤ.አ በ2018 ወደ ሥልጣን ከመጡ በኋላ ለሁለት አሥርት ዓመታት በኢትዮጵያና ኤርትራ መካከል የነበረውን የድምበር ውዝግብ እልባት በመስጠት ሰላም ማውረድ የቻሉ መሪ መሆናቸውን በማስታወስ፤ ለዚህ ተግባራቸው የተሰጣቸው ሽልማት ተገቢ መሆኑን እንደሚያምን በመግለጫው አስተላልፏል።
ይህ ጠቅላይ ሚኒስትሩ ያገኙት ሽልማት በአገሪቱ የነበረውን የሰብዓዊ መብት ጥሰት ለመታደግ፣ የዜጎችን ስደትና የመገናኛ ብዙኃንን አፈና ለማስቀረት፤ ህገመንግሥ ታዊና ዴሞክራሲያዊ መብቶች በአግባቡ ተግባራዊ እንዲሆኑ ለማስቻል መደላድል የሚፈጥሩበት አቅም እንደሚያላብሳቸው፣ መላው ኢትዮጵያውያንም ሽልማቱ የራሳቸው መሆኑን አውቀው ዓለም የሰጣቸውን ክብር እንደሚያስጠብቁ ያላቸውን ዕምነት መግለጻቸው ይታ ወሳል።
ሽልማቱ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ብቻ ሳይሆን የመላው ኢትዮጵያውያን በመሆኑ በወቅቱ የኢፌዴሪ ፕሬዚዳንት ሣህለወርቅ ዘውዴ ‹‹የዚህች የተባረከች አገር ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ ! ጠቅላይ ሚኒስትራችን ዶክተር አቢይ አሕመድ የ2019 የኖቤል ሠላም ሽልማትን አገኙ! እንኳን ደስ አለዎት !እንኳን ደስ አለሽ እናት አገር ኢትዮጵያ ! በአገራችን አራቱ ማዕዘንና በዓለም ዙሪያ የምትኖሩ የዚህች የተባረከች አገር ልጆች ሁሉ እንኳን ደስ አላችሁ›› በማለት የደስታ መልዕክታቸውን ለመላው ኢትዮጵያውያን አድርሰው ነበር።
እነሆ የኖቤል የሠላም ሽልማት ፈጣሪው አልፍሬድ ኖቤል እ.አ.አ.ኅዳር 18 ቀን 1888 ዓ.ም ኑዛዜ ካኖረበት ወቅት አንስቶ 67 የሚሆኑ የኖቤል የሠላም ሽልማቶች በተናጠል ላሸነፉ ግለሰቦች የተሰጡ ሲሆኑ፤ 30ዎቹ ደግሞ ሁለት ግለሰቦች በጋራ የተሸለሟቸው ናቸው። ሁለት የሠላም ሽልማቶችን ሦስት፤ ሦስት ሰዎች በቡድን አሸንፈዋል። 100ኛው የኖቤል ተሸላሚው ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ሆነዋል።
ከሽልማቱ በኋላ በትዊተር ገፃቸው በአጭሩ ምስጋና ያቀረቡት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ “ይህ ሽልማት የኢትዮጵያ ና የአፍሪካ ነው :: በኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ሰጪ ኮሚቴ ውሳኔ በጣም ተደስቻለሁ። ለሰላም ሲሉ ጠንክረው ለሚሠሩ ሁሉ ከልብ የመነጨ ምስጋናዬን አቀርባለሁ” ማለታቸው የቅርብ ጊዜ ትዝታ ነው።
ጠቅላይ ሚኒስትሩ የኢትዮጵያ መሪ ናቸው፤ ይህንን ሽልማት ያገኙትም በመሪነታቸው ላከናወኑት ተግባር ነው። አገሪቱ በዓለም ፊት በክብር እንደቆመች ማሰብ የግድ ነው። በዚህ ሽልማት በመላ ዓለም ያሉ ኢትዮጵያውያን መንፈሳቸው በኩራት እንደሚሞላ ይመሰክራሉ።
ለዚህም ነው የዓለም የጤና ድርጅት ዋና ዳይሬክተርና የኢትዮጵያ የቀድሞው የውጭ ጉዳይ ሚኒስትር ዶክተር ቴዎድሮስ አድሃኖም “ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ አሕመድ እ.አ.አ. የ2019 የኖቤል የሰላም ሽልማት በማሸነፍዎ እንኳን ደስ ያለዎ! ኢትዮጵያዊ በመሆኔ ኮራሁ ” ያሉት።
ትናንት በኖርዌይ ኦስሎ በክብር ሽልማታቸውን የተቀበሉት ጠቅላይ ሚኒስትር አብይ በመድረኩ ለሽልማት
ያበቃቸው ሥራዎቻቸው በኖቤል ሽልማት ኮሚቴው ሊቀ መንበር ሲዘረዘሩ ‹‹ በኤርትራና በኢትዮጵያ መካከል የነበረውን
ግጭት በማስወገድ መደበኛ የዲፕሎማሲ ግንኙነት እንዲጀመር ላከናወኑት ተግባር፣ ዴሞክራሲ ሊጎለብትባቸው በሚገቡ
ተቋማት ዴሞክራሲ እንዲጎለብቱ በማድረግዎ፣በምስራቅና በሰሜን ምሥራቅ የአፍሪካ አገራት ስለሰላም ላበረከቱት
አስተዋጽዎ የኖቤል የሽልማት ኮሚቴ ይህንን ሽልማት ሲያበረክትልዎ በታላቅ ደስታ ነው።
የአፍሪካ ቀንድ መዋዕለ ዜናና ታሪክ እንደሚያስረዳው ኢትዮጵያ የሰው ልጅ መፈጠሪያና የመጀመሪያው ሆሞ ሳፒየን ቅሪተ አካል የተገኘባት በመሆንዋ በዚህ ዕሳቤ እኛ ሁላችንም ኢትዮጵያዊ ነን ማለት ነው።
አገርዎ ልዩ ታሪክ ያላት ነች። በቅኝ ግዛት አልተገዛችም፤ በዚህ ምክንያት የአፍሪካ ህብረት ዋና መቀመጫ ነች።የዛሬው ልዩ ዝግጅትም ለሰላም ላደረጉት አስተዋፅኦ የኖቤል ኮሚቴ በወሰነው መሰረት እርስዎ ሽልማቱን እንዲቀበሉ ሆኗል። ›› በማለት የኖቤል ሽልማቱን አስረክበዋቸዋል።
በሽልማቱ ሥነ ሥርዓት ወቅት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ ‹‹ የኖርዌይ የኖቤል ሽልማት ኮሚቴ ለሰጠኝ እውቅና አመሰግናለሁ።በኢትዮጵያና በኤርትራ መካከል ለሁለት አሥርት ዓመታት ሰላም አልነበረም፣ ሰዎች ተለያይተዋል፣ በርካታ ሠራዊት በሁለቱ አገራት ድንበር ላይ መሽጎ ነበር፤ ይህ የሰላም እጦት እንዲያበቃ ለወሰድኩት እርምጃ የኤርትራው ፕሬዚዳንት ኢሳያስ አፈወርቂ የሰላም ቁርጠኝነት ወሳኝ ነበር።ይህንን ሽልማት የአፍሪካና የዓለም ህዝቦችን ወክዬ ነው የምቀበለው ›› በማለት ተናግረዋል።
ዓለም በጉጉት በሚከታተለው መድረክ በሰራው ሥራ ተወድሶ ፣እውነቱን ተናግሮ እርሱም አገሩም ተከብረው ከመታየት ሌላ ምን የሚያስደስት ነገር ይኖር ይሆን?
አዲስ ዘመን ታህሳስ 1/2012
አያሌው ንጉሤ