አዲስ አበባ፡- የወጪ ንግድ ምርቶችን በዓይነት፣ በመጠንና በጥራት የማሳደግ ሥራ ልዩ ትኩረት እንደሚሻ የፌዴራል ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ አሳሰቡ፡፡
የኢፌዴሪ የህዝብ ተወካዮች ምክር ቤት የመንግሥት ወጪ አስተዳደርና ቁጥጥር ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ከ2008 እስከ 2010 ዓመት ድረስ የወጪ ንግድ አፈጻጸምን በተመለከተ በተከናወነ የክዋኔ ኦዲት ሪፖርት ላይ ትናንት ከፌዴራል ዋና ኦዲተር መስሪያ ቤት፣ ከንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴርና ከሌሎች ባለድርሻ አካላት ጋር ተወያይቷል፡፡
በውይይቱም የወጪ ንግድ ምርቶች በዓይነት በመጠንና በጥራት እድገት አለማሳየቱንና የወጪ ንግድ አፈጻጸምም ከጊዜ ወደ ጊዜ ማሽቆልቆሉ በስፋት የተነሳ ሲሆን፣በጉዳዩ ላይ ዋና ኦዲተር አቶ ገመቹ ዱቢሶ እንዳሉት፤ለውጭ ገበያ የሚቀርበውን ምርት አይነት፣ መጠንና ጥራት ማሳደግ አንገብጋቢ ጉዳይ ነው፡፡
በዘርፉ የሚስተዋለውን መዋቅራዊ ችግር ለመቅረፍ የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስቴር ከግብርና ሚኒስቴር ጀምሮ በወጪ ንግድ ሰንሰለት ውስጥ የሚገኙትን አቀናጅቶ በመንቀሳቀስ በትኩረት ሊሰራ እንደሚገባ አስገንዝበዋል፡፡
እንደ አቶ ገመቹ ማብራሪያ፤ እያንዳንዱ ባለድርሻ አካል የሚሰራው ሥራ መለየት እንዳለበት፣ ምክር ቤቱም ተጠያቂነትን ሊያሰፍን እንደሚገባ፣የተሰጣቸውን ተግባር የማይወጡትንም ተጠያቂ በማድረግ እንዲሁም ከሌሎች ተሞክሮ በመውሰድና ቴክኖሎጂዎችን በመቀመር አንገብጋቢ የሆነውን የወጪ ንግድ መታደግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
የንግድና ኢንዱስትሪ ሚኒስትር ዴኤታ አምባሳደር ምስጋኑ አርጋ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ ከባለድርሻ አካላት ጋር በቅንጅት የወጪ ንግድን በአይነት፣ በመጠንና በጥራት ከፍ ለማድረግ እየሰራ መሆኑንና ከቋሚ ኮሚቴውና ከዋና ኦዲተሩ የተገኙ ግብዓቶችን በመጠቀም የተሻለ ውጤት ለማስመዝገብ እንደሚንቀሳቀስ አስታውቀዋል፡፡በዘርፉ የሚስተዋሉ ችግሮችን እንደሚፈታም ገልጸዋል፡፡
የቋሚ ኮሚቴው ሰብሳቢ አቶ መሃመድ የሱፍ፤ ሚኒስቴር መስሪያ ቤቱ፤ ከባለድርሻ አካላት ጋር ተባብሮ የተቋቋመበትን ዓላማ በተግባር ላይ እንዲውል በማድረግ፣ በኦዲት የተገኙ ጉድለቶችን በአስቸኳይ ማረም እንደሚገባውና ለዚህም ተቋሙ የውስጥ ኦዲቱን ማጠናከር እንዳለበት ጠቁመዋል፡፡ በዋና ኦዲተሩና በቋሚ ኮሚቴው የተሰጡ ግብዓቶችን በመጠቀም ፈጥኖ ክፍተቶቹን አርሞ ሪፖርት እንዲያደርግ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2012
መላኩ ኤሮሴ