ስለ ዋግኽምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ሲነሳ ለቀድሞ የኢትዮጵያ ህዝቦች ዴሞክራሲዊ ንቅናቄ /ኢህዴን / ታጋዮች ያበረከተው አስተዋጽኦ ይወሳል። ትግሉን የተቀላቀለው ብቻ ሳይሆን፣ በቀዬው ሆኖ ስንቅ በማቀበልና ልጁን ወደ ትግሉ እንዲቀላቀል ያደረገው ነዋሪ ሚና አይዘነጋም።
ተራራዎቹም ባለታሪክ ናቸው። የያኔዎቹ ታጋዮች የአሁኖቹ ጡረተኞች ታጋይ ሰለሞን መሐመድ፣ ታዘበ ከፍያለው እና ከበደ ተገኝ ትግሉን በተቀላቀሉበትና ተወልደው ባደጉበት አካባቢ ማህበር መስርተው ጥቅሞቻቸውን ለማስከበር በእንቅስቃሴ ላይ ይገኛሉ። ያለፈውን የትግል ትውስታቸውንና ሁለተኛ ዓመቱን ስለያዘው ለውጥ ሀሳባቸውን አካፍለውናል።
በሰቆጣ ከተማ ያገኘኋቸው የቀድሞ ታጋዮች እንዳጫወቱኝ በወጣትነት እድሜያቸው ነበር በ1970ዎቹ ኢህዴንን የተቀላቀሉት። ትግሉን የተቀላቀሉት በወቅቱ የዜጎችን ዴሞክራሲያዊ መብት በማፈን፣ ሰብዓዊ መብትን በመጣስ፣ በማሰር፣ በመደብደብ፣ በመረሸን ህዝብን ለስቃይና እንግልት ይዳርግ የነበረውን ጨቋኝ ሥርዓት ለመጣል ነው። ትግሉም ግቡን መቷል ይላሉ።
በጨቋኙ መንግሥት ቦታ በህዝብ የተመረጠ መሪ መቀመጡንም ያስረዳሉ። እንደታሰበው የኢትዮጵያን ነባራዊ ሁኔታ ባገናዘበና ህዝብን ከድህነት ያላቀቀ የላቀ ውጤት ባይመዘገብም በልማቱና በፖለቲካው ሰፊ ሥራ መሰራቱን ይናገራሉ።
ይሁን እንጂ በሂደት የታገሉለት ዓላማ ወደ ኋላ መመለሱን ካለው ነባራዊ ሁኔታ መገንዘባቸውንም ይገልጻሉ። ከህዝብ ጥቅም ይልቅ እራስን ማስቀደም እየሰፋ መምጣቱ፣ የሰብዓዊ መብት ጥሰቶችና ሌሎችም በህዝብ የሚቀርቡ ቅሬታዎች እየበዙ መምጣታቸው ‹‹ለዚህ ነበር እንዴ የታገልነው›› እንዲሉ አድርጓቸዋል። አሁን የመጣው ለውጥም የዚሁ ውጤት እንደሆነ ይገልጻሉ።
ታጋዮቹ ከሁለት ዓመት በፊት ሀገሪቷ ውስጥ የመጣውን ለውጥ ይደግፋሉ። የቀድሞ ታጋዮች ራስ አገዝ ማህበርን በአስተባባሪነት የሚመሩት ታጋይ ሰለሞን መሐመድ በሰጡት አስተያየት ለውጡን ቢደግፉም ሁለት ነገሮችን እንዲገነዘቡ አድርጓቸዋል።
በአንድ በኩል የመረረው
ህዝብ፣ በሌላ በኩል ደግሞ ስልጣን የሚፈልግ አካል መኖሩ ይሰማቸዋል። ከዚህ ቀደም የሚያውቁት ኢህአዴግ
የተፈጠረውን ችግር ይገመግማል። ጥፋተኛውንም ያስተካክላል። ያም ሆነ ይህ ‹‹ኢህአዴግ ጎዳን በደለን
የሚል የህዝብ ቅሬታ በማየሉ›› ለውጡ አስፈላጊ ሆኖ አግኝተውታል። የመስተካከል ዋና መርሁ ለውጥ እንደሆነና ህዝባዊ የሆኑ አሰራሮችን ማስፈን ጭምር ነው ይላሉ።
የኢህአዴግ ስልጣን ላይ መቆየትም ዘላለማዊ መሆን እንደሌለበትና ስልጣን ማሸጋገር እንደሚጠበቅበት ይገልጻሉ። በለውጡ የታዩት የእርስበርስ ግጭቶችና ዜጎችንም ከአካባቢያቸው እስከማፈናቀል መድረሱ አሳዝኗቸዋል።
የኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት ዴሞክራሲያዊ ግንባር (ኢህአዴግ) አባል እና አጋር ድርጅቶች ውህደትን ታጋይ ሰለሞን ከኢትዮጵያ ሰላም፣ ከህዝቦች መረጋጋትና ፍቅር እንዲሁም ከኢትዮጵያ ብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ጥቅም አንጻር እንደሚያዩት ይናገራሉ። በዓላማ የሚተሳሰሩ የፖለቲካ ድርጅቶች ተዋህደው መንቀሳቀሳቸው ለኢትዮጵያ አማራጭና እፎይታ እንደሆነ ባይተዋርነትንም እንደሚያስቀር ገልጸዋል።
ታጋይ ታዘበ እንዳሉት ታጋዩ ብቻ ሳይሆን፣ የዋግኸምራ ብሄረሰብ አስተዳደር ዞን ነዋሪ በአጠቃላይ ለውጡን በድጋፍ ሰልፍ እንደተቀበለው በማስታወስ፣ ሰላማዊ ሰልፉ የድጋፍ መግለጫ እንደሆነም አስምረውበታል።
ውህደቱንም በተመለከተ ለኢትዮጵያ ህዝቦች አንድነት፣ ማዕከላዊ መንግሥቱ እንዲጠናከር ለማድረግ፣ ሀገርንም በልማት ለማበልጸግና ዴሞክራሲን ለማስፈን ውህደቱ የሚኖረው ፋይዳ ከፍተኛ እንደሆነ ያስረዳሉ።
በድርጅት ደረጃም አማራ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ (አዴፓ) ለውጡን ተቀብሎ መንቀሳቀሱ ማሳያ እንደሆነና ታጋዮችም ከድርጅቱ የሚለዩ አለመሆናቸውን ይገልጻሉ። ከመነጣጠል በአንድ ሆኖ ሀገርን መምራት እንደሚጠቅም ተናግረዋል።
ታጋይ ከበደ ተገኝ በበኩላቸው የለውጡን አስፈላጊነት ይደግፋሉ። ለውጡ ያስገኛቸውንም መካድ አይገባም ይላሉ። ነገር ግን ለውጥ ሰሞነኛ መሆን እንደሌለበት ያምናሉ። እርሳቸው እንዳሉት የደርግ ሥርዓት የተገረሰሰው ለውጥ በማስፈለጉ ነው።
አሁንም የመጣው ለውጥ ይሄን የሚደግም እንዳይሆን ከሥር ከስር ማየት ይገባል። ችግሮች የማይደገሙበትና ወደ ህዝብ ጠብ የሚል ነገር ሲኖር ለውጡ ላይ እምነት መጣል ይቻላል ይላሉ።
ውህደቱንም በተመለከተ ዘግይቷል ይላሉ። በተለይ አጋር ድርጅቶች እስከ መቼ በአጋርነት ይቀጥላሉ ለሚለው ምላሽ የሰጠም እንደሆነ ይገልጻሉ። መስማማት ለውጤት ያበቃል ሲሉም አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 2/2012
ለምለም መንግሥቱ