በሃዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ ሸቻና ለሬባ ቀበሌ የተቀናጀ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ፤ ጸረ ተባይና አይጥ ማጥፊያ መድኃኒት ማምረቻ ፋብሪካ ይገነባል ተብሎ የመሰረት ድንጋይ የተጣለው በግንቦት 12 ቀን 2007 ዓ.ም ነበር፡፡ የፋብሪካው ግንባታ በ2008 ዓ.ም ተጀምሮ በ2010 ዓ.ም እንደሚጠናቀቅ የመሰረት ድንጋይ በተጣለበት መርሃ ግብር ላይ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ለህዝቡ ቃል መግባታቸውን የሃዲያ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪ ያስታውሳሉ፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን የፋብሪካው ግንባታ አልተጀመረም፤ ስለ ጉዳዩም እኔ ይመለከተኛል የሚል የመንግሥት ወገን አልተገኘም፡፡
‹‹የወጋ ቢረሳ የተወጋ አይረሳም›› ነውና የመሰረት ድንጋይ የጣለው አካል ጉዳዩን ቢዘነጋውም ተስፋ ጥለው የነበሩት የአካባቢው ነዋሪዎች ግን ዛሬም ይገነባል ስለተባለው የማዳበሪያ ፋብሪካ ያነሳሉ፡፡ በሃዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ የሸቻና ለሬባ ቀበሌ አዋሳኝ የሆነው የሃይሴ ቀበሌ ነዋሪ አባገዳ ደበሮ አዴቦ በአካባቢው ይገነባል የተባለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ፋብሪካ የመሰረት ድንጋይ ሲጣል በስፍራው እንደነበሩ ያስታውሳሉ፡፡
ፋብሪካው ይገነባል ሲባል እጅግ እንደተደሰቱ በመናገር ‹‹የመሬት ላራሹ አዋጅ ከታወጀበት ቀን ቀጥሎ እጅግ የተደሰትኩበት ቀን ነበርም›› ይላሉ፡፡ በአጼ ኃይለ ስላሴ ዘመን 100 ኪሎ ግራም ማዳበሪያ በ44 ብር ገዝተው ይጠቀሙ እንደነበርና በአሁኑ ወቅት 100 ኪሎ ግራም ማዳበሪያ ዋጋ 1 ሺ 500 ብር መድረሱን በመግለጽ፤ ፋብሪካው ተገንብቶ ቢጠናቀቅ ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ የመጣውን የማዳበሪያ ዋጋ በመቀነስ በአነስተኛ ወጪ የግብርና ሥራቸውን እንዲያከናውኑ ያስችላል የሚል ተስፋ ሰንቀው እንደነበር ተናግረዋል፡፡
መሰረት ድንጋዩ ከተጣለ አራት ዓመት ቢያልፍም የግንባታው ሥራ አለመጀመሩ ቅር እንዳሰኛቸው የሚናገሩት አባገዳ ደበሮ፤ ቅሬታቸውን ከሌሎች የአካባቢው አርሶ አደሮች ጋር በመሆን ለዞኑ አመራሮች ማቅረባቸውንና አጥጋቢ ምላሽ እንዳላገኙ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው የማይገነባ ከሆነ ቀድሞውኑ መሰረት ድንጋይ መጣል አልነበረበትም የሚሉት ደግሞ በወረዳው የሸቻ ቀበሌ ነዋሪ አርሶ አደር በላቸው ኃይሌ ናቸው፡፡ የሚገነባ ከሆነም እስካሁን የግንባታ ሥራው መጀመር ነበረበት ይላሉ፡፡ ግንባታ ባለመጀመሩም ፋብሪካው ሌላ ቦታ ተወስዶ ሊሠራ ነው እየተባለ ሲወራም እንደነበር ተናግረዋል፡፡ ይህም የአካባቢውን ህብረተሰብ የልማት ተነሳሽነት የሚጎዳ መሆኑን ገልጸዋል፡፡
እንደ አቶ በላቸው ማብራሪያ፤ ግንባታው ባለመጀመሩ ለፋብሪካው ግንባታ የተያዘው ስፍራ አንዳንድ ግለሰቦች ለግል ጥቅማቸው እያዋሉት ነው፡፡ የመኪና እጥበት አገልግሎትና የተለያዩ ግንባታዎችም ተጀምረዋል፡፡ በተለያዩ መድረኮች የፋብሪካው ግንባታ ለምን እንዳልተጀመረ በየደረጃው ላሉ የመንግሥት የሥራ ኃላፊዎች ጥያቄ ቢያቀርቡም አጥጋቢ ምላሽ አልተገኘም፡፡
የሀዲያ ዞን ምክትል ዋና አስተዳዳሪና የዞኑ የትምህርት መምሪያ ኃላፊ አቶ ሀብታሙ ታረቀኝ በሀዲያ ዞን በሆሳዕና ከተማ አቅራቢያ በሌሞ ወረዳ ሸቻና ለሬባ በሚባል አካባቢ ግንቦት 12 ቀን 2007 ዓ.ም የኬሚካል ማዳበሪያ ፋብሪካ ይገነባል ተብሎ መሰረት ድንጋይ መጣሉን አረጋግጠዋል፡፡ የፋብሪካው ግንባታ በ2008 ዓ.ም ተጀምሮ በሁለት ዓመት ውስጥ እንደሚጠናቀቅና የፋብሪካው በጀት ከፌዴራል መንግሥት መመደቡን በወቅቱ በቦታው ንግግር ያደረጉት የመንግሥት ሥራ ኃላፊዎች መናገራቸውን አስታውሰዋል፡፡
የመሰረት ድንጋዩ ሲጣል ሚኒስትሮች፤ የክልሉ ምክትል ርዕሰ መስተዳድር፤ የግብርና ሚኒስቴር እንዲሁም የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የሥራ ኃላፊዎች መገኘታቸውን የሚናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ ፕሮጀክቱን በባለቤትነት የማስተዳደር ኃላፊነት የተሰጠው ለኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ነው ብለዋል፡፡ ፕሮጀክቱን እንዲገነባ የተሰጠው ለብረታ ብረትና ኢንጅነሪንግ ኮርፖሬሽን መሆኑን ተናግረዋል፡፡
እንደ አቶ ሀብታሙ ማብራሪያ፤ ይገነባል የተባለው ፋብሪካ በዓመት አንድ ነጥብ 2 ሚሊዮን ሊትር ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ፤ 300 ሺ ሊትር ፈሳሽ ተፈጥሯዊ ጸረ ተባይና 250 ቶን ተፈጥሯዊ ጸረ አይጥ መድኃኒት የማምረት አቅም ያለው ነው፡፡ ለፋብሪካው 36 ሚሊዮን ዶላር በጀት ተይዞ የነበረ ሲሆን፤ ለ950 ዜጎች ጊዜያዊ ቋሚ የሥራ እድል ይፈጥራል ተብሎ ታስቦ ነበር፡፡
የፋብሪካው የግንባታ ሥራ እስካሁን አለመጀመሩ በአካባቢው ነዋሪዎች ዘንድ የቅሬታ ምንጭ ሆኗል፡፡ ህዝብ በተሰበሰበባቸው መድረኮች ሁሉ የፋብሪካው ግንባታ ለምን አልተጀመረም የሚል ጥያቄ ይቀርባል፡፡ ባለፈው ዓመት ሰኔ ወር ላይ ህዝቡ ለጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ የለውጥ ሥራዎች ድጋፍ ለመስጠት በወጣበት ሰላማዊ ሰልፍ ላይም ከታዩት ባነሮች አንዱ የፋብሪካው ግንባታ እንዲጀመር የሚጠይቅ ነበር፡፡ ህዝቡ በተለያዩ መድረኮች ያነሳቸውን ጥያቄዎች በተለያዩ መገናኛ ብዙኃን ለማሳወቅ ተሞክሯል፡፡ በወቅቱ መሰረት ድንጋዩን ለጣሉትና በባለቤትነት ይመሩታል ለተባሉት አካላትም የህዝቡን ቅሬታ የማሳወቅ ሥራ ተሠርቷል፡፡ ሆኖም እስካሁን ድረስ አጥጋቢ ምላሽ ማግኘት እንዳልተቻለ ተናግረዋል፡፡
ፋብሪካው ይገነባል የተባለበት ግማሹ የወል መሬት ሲሆን፣ ግማሹ የአርሶ አደሮች የግል መሬት መሆኑን የተናገሩት አቶ ሀብታሙ፤ ለአርሶ አደሮች መሬት የካሳ መጠን ተሠርቶ ምን ያህል እንደሚከፈላቸውም ተወስኖ እንደነበርም አንስተዋል፡፡ የአካባቢው ነዋሪዎች ስፍራው ለሌላ አገልግሎት እዋለ ነው ቢሉም፤ ለፋብሪካው የተከለለውን ቦታ ለመውረር የተደረጉ ተደጋጋሚ ሙከራዎች እርምጃ ተወስዶባቸው መሬቱን ከወረራ መታደግ መቻሉን ገልጸዋል፡፡
የኬሚካል ኢንዱስትሪ ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ተወካይ አቶ ተባባል ውድነህ በበኩላቸው በሃዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ ፈሳሽ የተፈጥሮ ማዳበሪያ በባለቤትነት ለማስገንባት ተቋሙ እቅድ አልያዘም ብለዋል፡፡ ፋብሪካውን በባለቤትነት ለማስገንባት እንቅስቃሴ ያደርግ የነበረው የግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ ነው፡፡ ኮርፖሬሽኑ ከያዩ ማዳበሪያ ፋብሪካና ከሞሮኮ መንግሥት ጋር ይገነባል ከተባለው የድሬዳዋ የማዳበሪያ ፋብሪካዎች ውጭ በባለቤትነት ለማስገንባት የያዘው የማዳበሪያ ፕሮጀክት አለመኖሩንም አንስተዋል፡፡
የኢትዮጵያ ግብርና ትራንስፎርሜሽን ኤጀንሲ የኮሙዩኒኬሽን ቡድን፤ በሆሳዕና አካባቢ ይገነባል ስለተባለው ፋብሪካ ምንም መረጃ እንደሌለው አሳውቋል፡፡ የኤጀንሲው ዋናው ሥራም ከግብርና ሚኒስቴር፣ ከፌዴራል ህብረት ሥራዎች ኤጀንሲና ከክልሎች የግብርና ቢሮዎች ጋር በመሆን የማዳበሪያ ማቀናበሪያ ፋብሪካዎችን ማቋቋም እንጂ የተፈጥሮ ፈሳሽ ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን ማቋቋም አለመሆኑን ጠቁሟል፡፡ የፈሳሽ ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን የማቋቋም ኃላፊነት የግብርና ሚኒስቴር ነው ብሏል፡፡
በግብርና ሚኒስቴር የተፈጥሮ ሀብትና የምግብ ዋስትና ዘርፍ የአፈር ለምነት ማሻሻያ ዳይሬክተር አቶ ተፈራ ሰለሞን እንደሚሉት፤ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በተለያዩ የሀገሪቱ አካባቢዎች የኬሚካል ማዳበሪያ ፋብሪካዎችን በማስገንባት ላይ ነው፡፡ በሃዲያ ዞን በሌሞ ወረዳ ይገነባል ስለተባለው የተፈጥሮ ማዳበሪያ ፋብሪካ ግን እርሳቸውም ሆኑ አሁን ሥራ ላይ ያሉት የሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ከፍተኛ የሥራ ኃላፊዎች የሚያውቁት ነገር የለም፡፡
ሆኖም የሃዲያ ዞን አርሶ አደሮች በተለያዩ አጋጣሚዎች ስለማዳበሪያው ፋብሪካ ቅሬታ ሲያቀርቡ ነበር፡፡ የአካባቢው አርሶ አደሮች በምክር ቤት የግብርና ጉዳዮች ቋሚ ኮሚቴ ወደ አካባቢው ባቀናበት ወቅትም የፋብሪካው ግንባታ አለመጀመር ቅሬታ እንደፈጠረባቸው ጥያቄ ማቅረባቸውን አስታውሰዋል፡፡
እንደ አቶ ተፈራ ማብራሪያ፤ የምክር ቤት አባላትም ማዳበሪያ ፋብሪካ ግንባታ ለምን እንዳልተጀመረ ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ በደብዳቤ እንዲያሳውቅ ጠይቋል፡፡ ጥያቄውን መሰረት በማድረግም ስለማዳበሪያ ፋብሪካው ሚኒስቴር መሥሪያ ቤቱ ምንም መረጃ እንደሌለውና መሰረት ድንጋዩ ራሱ በማን እንደተጣለ እንደማይታወቅ የግብርና ሚኒስቴር መግለጹን ተናግረዋል፡፡
አዲስ ዘመን ታህሳስ 25/2011
በመላኩ ኤሮሴ