ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ባለፈው ሳምንት በኖርዌይ ኦስሎ ተገኝተው የተቀበሉት የሠላም የኖቤል ሽልማት በዓለም አቀፍ ደረጃ ትልቅ ዜና ሆኖ ቆይቷል። በኢትዮጵያም ባለፈው ሳምንት ከሽልማቱ ጋር የተያያዙ በርካታ መድረኮች እየተካሄዱ ሽልማቱ ያስገኘውን ክብር ለመቋደስ ተችሏል። ኢትዮጵያ ሽልማቱን የልማቷ እና የሠላሟ ግብዓት ማድረግ እንዳለባትም የተለያዩ ወገኖች እየተገለፁ ናቸው።
ሦስተኛ ዲግሪያቸውን በሠላምና ደህንነት እየተከታተሉ ያሉት አቶ አበበ አይነቴ ሽልማቱ መልካም አጋጣሚ መፍጠሩን ይገልፃሉ። ‹‹ይህን አጋጣሚ ለሀገሪቱ ዲፕሎማሲያዊ ሥራ ስትራጂክ በሆነ መልኩ መጠቀም ያስፈልጋል፤ የዲፕሎማሲ ሥራ ማለት ሀገር ውስጥ ያለው ሥራ ውጤት ነው›› ይላሉ። ሀገር ውስጥ የተጀመሩ ሥራዎች እንዳሉም አመልክተው ለዚህም የዴሞክራሲ ምህዳሩን ለማስፋት እየተወሰደ ያለውን እርምጃ ለአብነት ይጠቅሳሉ።
‹‹ከኤርትራ ጋር የተደረሰው ስምምነትም አገር ውስጥ የተሠራው ሥራ ውጤት ነው›› ያሉት አቶ አበበ፣ የፖለቲካ ምህዳሩን የማስፋቱ ሥራም በኢትዮጵያ ፖለቲካ ላይ የተቃውሞ እንቅስቀሴያቸውን ኤርትራ ላይ ያደርጉ የነበሩት ወደ ኢትዮጵያ እንዲመለሱ አስችሏል ይላሉ። ስለዚህ ትልቁ ቁልፉ ሥራ የሀገር ውስጡ ሥራ መሆኑን አምኖ ይህንኑ ሥራ አጠናክሮ መቀጠል ይገባል ብለዋል።
የፖለቲካ ምህዳሩ መስፋቱንና አንድ እርምጃ ወደፊት መሄዱን በመግለጽ ይሄ ደግሞ በሕግ የበላይነት እና ሰብአዊ መብት ላይ ያልተጠበቁ ነገሮችን አምጥቷል የሚሉት አቶ አበበ፣ ይህን ለማረም ሽልማቱን አንደ ትልቅ መሣሪያ መጠቀም እንደሚቻል ይገልፃሉ።
እንደ አቶ አበበ ገለፃ፤ ሽልማቱን ለዲፕሎማሲ ሥራ በግብዓትነት መጠቀም ይገባል። የተጀመሩ መልካም ሥራዎችን ለማስቀጠል ክፍተቶችንና ጉድለቶችን ማረም ላይ ትኩረት ለማድረግ እንደ መልካም አጋጣሚ መውሰድ ይቻላል።
‹‹አንድ ወቅት ላይ የአፍሪካ የኢንዱስትሪና የኢኮኖሚ ዕድገት ተምሳሌት ተደርገን ነበር፤ በኋላ ደግሞ የግጭትና የሁከት ተምሳሌት ተደርገናል›› ያሉት አቶ አበበ፣ ገጽታችን ጠይሞ ጉራማይሌ ቅርጽ ይዞ እንደነበርም ያስታውሳሉ። ይህን ጉራማይሌ ገጽታ ለመቀየር የኖቤል ሽልማቱን እንደ ትልቅ ግብዓት መጠቀም እንደሚገባ ያስገነዝባሉ። ይህም ያንን የተበላሸ ገጽታ ለመቀየርና ዓለም አቀፍ ግንኙነቱን የበለጠ ለማጠናከር ዕድል ይፈጥራል ይላሉ።
አቶ አበበ እንዳሉት፤ የሀገር ውስጥ ሰላምን ማረጋገጥና የሕግ የበላይነትን ማስከበር ይገባል። የዴሞክራሲ ምህዳር መስፋቱ በራሱ ግብ አይደለም። ዜጎች በነፃነት ያለሥጋት ያለፍርሃት በሕገ መንግሥቱ መሰረት በየትኛውም አካባቢ በነፃነት እንዲንቀሳቀሱ ማስቻል ያስፈልጋል፤ በዚህም ላይ መሠራት ይኖርበታል።
የምጣኔ ሀብት ባለሙያው አምባሳደር ጥሩነህ ዜና ሽልማቱ ከነግለቱ መቀጠል እንዳለበት ጠቅሰው ይሄ ነገር ግለቱ ሳይቀዘቅዝ እንዲቀጥል ማድረግ አለብን ይላሉ።
አምባሳደሩ እንደሚሉት፤ በዓለም አቀፍ ሁኔታ በሳምንታት ውስጥ ብዙ ነገር ይረሳል። ሌላ አዲስ ነገር ይመጣል። ዓለም እኛን ብቻ አይደለም የሚያስበው።
በዓለም ላይ እየተፈፀሙ ያሉ ብዙ ሁኔታዎች አሉ። ስለዚህ እኛ እንዳንረሳ የተፈጠረውን መልካም ሁኔታ ተጠቅመን ሌሎች ነገሮችን እየጨመርን የኢትዮጵያ ስም በአዎንታዊ መልኩ እንዲነሳ ማድረግ ያስፈልጋል። ለእዚያ ደግሞ ምቹ ሁኔታዎች አሉ።
አሁን እየያዙን ያሉት በጣም ትናንሽ ሁኔታዎች ናቸው ያሉት አምባሳደር ጥሩነህ፣ ብዙ ልናገር የማልችለውና የማላወቀው የፖለቲካ ሁኔታ አለ። ሰላምና ደህንነት እንዲጠበቅ ለማድረግ ደግሞ የፖለቲካ ሁኔታ ወሳኝ ነው። ይህ እንዴት እንደሚሻሻል አላውቅም፤ ይህ ሁኔታ ባለው መልኩ ከቀጠለ ጥሩ አይደለም።›› ብለዋል።
የቱሪዝም ኢትዮጵያ የገበያ ልማት ተጠባባቂ ዳይሬክተር አቶ ንጉሴ እሸቱ የኖቤል ሽልማቱ ኢትዮጵያን በማስተዋወቅ በኩል ትልቅ ፋይዳ ይኖረዋል የሚል እምነት ማሳደሩን ይገልፃሉ። ‹‹ ይህን ዕድል መጠቀም ይቻላል። የኖቬል ሽልማቱን ሥነ ሥርዓት መላው ዓለም ተከታትሎታል። በዓለም ደረጃ ትልቅ የማስተዋውቀው ዕድል አግኝተናል። ›› ያሉት አቶ ንጉሴ፣ ሀገሪቱን የማያውቃት ጭምር እንዲያውቃት ሊያደርግ የሚችል የማስተዋወቅ ሥራ እንደተሠራ አርጎ መውሰድ እንደሚቻል ይገልፃሉ።
‹‹ይህን ካፒታላይዝ ማድረግ ይቻላል፤ ይህን እየጠቀስን በምንሰራቸው የማስተዋወቂያ መሣሪያዎች ሁሉ እያነሳን ፣ በምናካሂዳቸው ሁሉም እንቅስቃሴዎች ውስጥ እያነሳን እንሠራለን። እንዴት እንጠቀማለን የሚለውን ወደፊት እናሳድገዋለን›› ሲሉ ያመለክታሉ። ከገበያ ልማት አኳያ ትልቅ ግብዓት መሆኑን ነው የተናገሩት።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 7/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል