መከባበር፣ መተማመን ብሎም መተጋገዝ የተለያዩ የኅብረተሰብ ክፍሎችን በአብሮነት ብዙ መንገድ ሊያስኬዳቸው ከማስቻሉም በላይ የእርስ በእርስ መግባባትንም ለመፍጠሩ አጠያያቂ አይደለም፡፡ ኢትዮጵያውያን በዚህ ዓይነት መንገድ የእርስ በእርስ መደጋገፍን አስቀጥለው ለዘመናት አብረው ዘልቀዋል፡፡ አሁን አሁን ግን በአንዳንድ አካባቢዎች የመገፋፋቱ ነገር ብቅ ማለት የጀመረ ሲሆን፣ አልፎ ተርፎም ስፍራ እስከማስለቀቅ መድረሱ ይታወቃል፡፡
በዚህ ጉዳይ በአብነት ማንሳት የሚቻለው በኦሮሚያ ምዕራቡ ክፍልና በቤኒሻንጉል ጉሙዝ አካባቢ ለወራት የዘለቀው መገፋፋት ዛሬም ትኩሳቱ እምብዛም አልበረደምና ወደ ስፍራው አቅንተው በሁለቱም ክልሎች ያሉትን የኅብረተሰብ ክፍል ያወያዩትን የኦሮሚያ ሚዲያ ኔትወርክ ሥራ አስኪያጅና አክቲቪስት ጃዋር መሃመድን በዚሁና በተለያዩ ጉዳዮች ላይ አዲስ ዘመን አነጋግሯቸዋል፡፡ እንደሚከተለው አቅርበነዋል፡፡ መልካም ንባብ ይሁንልዎ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ሰሞኑን በምዕራብ ኦሮሚያ ክፍልና አሶሳ አካባቢ ተንቀሳቅሰው ስላለው ሁኔታ አይተዋልና ተፈናቃዮች ለመፈናቀላቸው ምክንያቱ ምን ይሆን?
አቶ ጃዋር፡- እነርሱ እንደሚናገሩት በቤኒሻንጉል አካባቢ ያሉ ታጣቂዎች በሚፈጽሙት ድንገተኛ ጥቃት መፈናቀላቸውን ነው፡፡ በእርግጥ በአጠቃላይ በምዕራቡ አካባቢ የተረዳነው ነገር ቢኖር ችግር መኖሩን ነው፡፡ በኦሮሚያ ውስጥ የተወሰነ የጸጥታ ችግር እንዳለ በተለይ ደግሞ የመንግሥት መዋቅር በጣም መዳከሙንና ይህም ለተለያዩ ክስተቶች መንስዔ እንደሆነ ነው ማስተዋል የቻልነው፡፡
ወደ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ስንሄድም በአጠቃላይ የመስተዳድር መዳከም መኖሩን ተመልክተናል፡፡ ከዚህም የተነሳ ጥርጣሬዎች መንገሳቸውንና አንዳንድ የተደራጁ ኃይሎች ከየክልሎቹ እየተነሱና ድንበር እየተሻገሩ ጥቃት እንደሚያደርሱ፣ ይህም በሕዝቡ ውስጥ ከፍተኛ መሸበርን ፈጥሮ ከሁለቱም ክልል ሰዎች እንደተፈናቀሉ ነው የተረዳነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ቀደም ሲል በስፍራው ለዘገባ ተንቀሳቅሶ ለነበረው የኢትዮጵያ ፕሬስ ድርጅት ጋዜጠኞች የየዞኑ አመራር ታጣቂ ኃይሎች በስፍራው እንዳሉና ማንነታቸውን ግን እንደማያውቁ ገልጸውልን ነበር፤ እርስዎ በዚህ ጉዳይ ምን አስተዋሉ? እውን ታጣቂ ኃይል በስፍራው አለ? ካለስ ማንነቱ ይታወቃል?
አቶ ጃዋር፡- እንደሚታወቀው አካባቢው ኦነግ ለረጅም ጊዜ ሲንቀሳቀስበት የነበረ መሆኑ ግልጽ ነው፡፡ በአሁኑም ወቅት የታጠቀ የኦነግ ኃይል በአካባቢው አለ፡፡ ከሕዝቡ እንደሰማነው ግን ጥቃት የሚያደርሰው ኃይል እርሱ አይደለም፡፡ በሁለቱም ወገን ሌሎች የታጠቁ ኃይሎች ሊኖሩ ይችላሉ የሚል ጥርጣሬ ነው ያለው፡፡
በመፍትሄ ደረጃ እያየን ያለነውና አሁን እየተደረሰበት ያለው ነገር ኦነግ ወደ ሰላማዊ ትግል ተቀላቅሏል፡፡ በዚሁ መሠረት ከፌዴራልና ከክልሉ መንግሥት ጋር ባደረጉት ስምምነት መሠረት የታጠቀው ኃይል ከጫካ ወጥቶ የክልሉንና የፌዴራል ደህንነት የሚቀላቀልበትና በጋራ በመተባበር የአካባቢውን ሰላም ማስከበር አስፈላጊ እንደሆነ ነው ማስተዋል የቻልነው፡፡
ስለዚህ ጥቃቱን እፈጸሙ ያሉት የኦነግ አሊያም የሌላ ፖለቲካ ድርጅት ይሁኑ አይሁኑ በእርግጥ የምናውቀው ነገር ባይኖርም የእነሱ በዚያ አካባቢ መንቀሳቀስ ለሌሎች ክፍሎች ግን መንገድ እንደከፈተ ተረድተናል፡፡
አዲስ ዘመን፡- በዚያ አካባቢ በተለይ ወደ ካማሺ ዞን የሚወስደውን መንገድ ኅብረተሰቡ ለመጠቀም በስጋት ላይ በመሆኑ ዝግ ነው፤ እርዳታም እንደልብ መድረስ አልቻለም፡፡ ለዚህ መፍትሄው ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ጃዋር፡- እኛ መጀመሪያ የመጣነው የወለጋ ዞኖችን ለማየት ነው፡፡ ሆኖም ከሕዝብ ጋር ባደረግነው ውይይት እዚያ ያለው የጸጥታ ችግር ከቤኒሻንጉል ጉሙዝ ጋር እንደሚያያዝ ስለተረዳን ከዛኛው ወገን ያለውን ሁኔታ ማየትና ሕዝብንም ማወያየት አስፈላጊ ነው ብለን ወደ አሶሳ ዘልቀን ከክልሉ አመራርና እንዲሁም ከአሶሳ ከተማ ማህበረሰብ ጋር ውይይት አካሂደናል፡፡
ወደ ካማሼ የሚወስደው መንገድ ብቻ ሳይሆን ዋናው መንገድ ራሱ ማለትም ከአሶሳ የሚነሱ መኪናዎች ለመንቀሳቀስ ፍራቻ እንዳለባቸውና አስፈላጊ ግብዓቶች ወደ አሶሳ ከተማ እየገቡ እንዳልሆነ ነው የተረዳነው፡፡ ይህ ደግሞ በጣም አሳሳቢ ነው፡፡በነገራችን ላይ ይህኛው መንገድ ብቻ ሳይሆን በሞያሌ የሚገባውም መንገድ ለተወሰኑ ማህበረሰቦች ዝግ እንደሆነና ለመንቀሳቀስ እንደሚፈሩ ተረድተናል፡፡ እንዲሁም ከትግራይ የተነሳ መኪና በአማራ ክልል አልፎ መምጣት ስላልቻለ 300 ኪሎ ሜትር ጨምሮ በአዳማ ነው የሚመጣው፡፡ ይህ በተለያየ መልኩ የሚደረገው የአውራ ጎዳናዎች የመዝጋት ችግር የፌዴራል ሥርዓትን የሚያዳክም፣ የኢኮኖሚ እንቅስቃሴውንም የሚጎትት እንዲሁም የማህበረሰብ ቁርኝነትን የሚበጣጥስ ስለሆነ በጣም በአስቸኳይ መፈታት ያለበት ጉዳይ ነው፡፡
ማንኛውም ዋና ዋና መንገድ መዘጋት የለበትም፡፡ ለማንኛውም ማህበረሰብም ሆነ ማንኛውም ዓይነት ታርጋ ላለው መኪና የሚዘጋ ከሆነ የሚጎዳው ሁሉም ማበረሰብ ነው፡፡ ከዚህ አኳያ የተረዳነውና ለመንግሥትም መምከር የምንፈለገው አንደኛ ሕዝቡ እንዲረጋጋና በሕዝቡ መካከል መተማመን እንዲመጣ መስራት ያስፈልጋል፡፡ ከዚህ ባለፈ ደግሞ የፌዴራል ኃይልን በመጠቀም እነዚህ የጠቃቀስኳቸው መንገዶች እንዲከፈቱ ማድረግ አስፈላጊ እንደሆነ ነው የተገነዘብነው፡፡ እንዳጋጣሚ ከቀናት በፊት አሶሳ ነበርኩና በከተማዋም የፌዴሬሽን ምክር ቤት ስብሰባ ሲካሄድ ነበር፡፡ ጉዳዩን ለአፈ ጉባኤዋ በመግለጽ በአስቸኳይ ይህ ችግር መፈታት እንዳለበትና ሁሉም መንገዶች በተለይ ወደ አሶሳ የሚመጣው፣ ወደ ጂግጂጋ የሚሄደውና ወደ መቀሌ የሚሄደው መንገድ በአስቸኳይ ለሁሉም ትራፊክ ክፍት መሆን እንዳለበት አሳውቀናል፡፡ እኛም በበኩላችን ሕዝባችንን በማስተማርና ከሕዝባችን ጋር ለመወያየት አስፈላጊውን ድጋፍ ሁሉ ማድረግ እንደምንፈልግ ነው አበክረን የነገርናቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- አንዳንድ አካላት ቄሮ ስጋት እንደሆነና አደጋም አድራሽ አድርገው ሲስሉት ይስተዋላልና በዚህ ላይ እርስዎ ምን ይላሉ? በወለጋ አካባቢና ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ላይ ከሕዝብ ጋር ያደረጉት ውይይት አለና ምን ስምምነት ላይ ደረሳችሁ?
አቶ ጃዋር፡- ቄሮን እንደ ስጋት የሚስሉ ኃይሎች እንዳሉ እናውቃለን፡፡ በዘመኑ የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ ለመጣው ለውጥ ትልቁን ሚና የተጫወተው ቄሮ ነው፡፡ ይህ ታግሎ ያመጣው ለውጥ ነው፡፡ ቄሮ የፖለቲካው አቅጣጫ ትክክለኛውን እንቅስቃሴ እንዲይዝ ያደረገም ነው፡፡ ይህን እንቅስቃሴውን የሚፈሩ ኃይሎች ስሙን ለማጠልሸት እንደሚን ቀሳቀሱም እሙን ነው፡፡ በአጠቃላይ ግን ወጣቱ አሁን ባለው የኢትዮጵያ ፖለቲካ ውስጥ እየተሳተፈ ነው ያለው፡፡
እንዲያም ሆኖ ከፍተኛ ሥራ አጥነት አለ፡፡ በተጨማሪ ደግሞ የመንግሥት መዋቅር መዳከም ይታይበታል፡፡ ያልተመለሱ የሕዝብ ጥያቄዎች አሉ፡፡ የመንግሥት መዋቅር መላላቱና ለረጅም ጊዜ የታፈነ ሕዝብ ከመሆኑ አንጻር በሚደረጉ ግጭቶች ውስጥ ወጣቶች መሳተፋቸው እሙን ነው፡፡ በኦሮሚያ በተለይ በምዕራብ ወለጋም ሆነ ሌላው አካባቢ የሚካሄደው ነገር ከቄሮ ጋር የሚያያዝ ግን አይደለም፡፡ የፖለቲካ ልዩነቶች የሚፈጥሯቸው የፖለቲካ መፍትሄ ሊደረግባቸው የሚገባቸው ጉዳዮች ናቸው፡፡
በየቦታው ለሚፈጠሩ ችግሮች ቄሮን ለመወንጀልና ለማጠልሸት የሚደረጉ ሩጫዎች መኖራቸው አይካድም፡፡ ያም ሆነ ይህ ግን አገሪቱ በፍጥነት የፖለቲካ ሽግግሩን ካልጨረሰችው በተለይ በምርጫ ጉዳይ ላይ የፖለቲካ ድርጅቶች ቁጭ ብለው የጋራ ስምምነት ላይ ደርሰው አገሪቱን በቀጥተኛ መንገድ ላይ ካላደረጉ እነዚህ ግጭቶች እየሰፉ ነው የሚሄዱት፡፡
በአገሪቱ የተለያዩ ክፍሎች ተንቀሳቅሼ እንደተመለከትኩት ከሆነ የታችኛው የመንግሥት መዋቅር በዞን፣ በወረዳ፣ በከተማም ሆነ በቀበሌ ያለው በጣም ተዳክሟል፡፡ አመራሩ በራስ መተማመን የለውም፡፡ እንደ ድሮው በጉልበት እንዳይገዛ ጉልበት የለውም፡፡ ሕዝቡን ተጠቃሚ እንዳያደርግ በጀት የለውም፡፡ ከዚህ አንጻር የመዋቅር መላላቱ በተለይ ደግሞ እቅድ ካለመኖር ጋር ተያይዞ አደጋ እየፈጠረ ነውና ይህን አደጋ ከወጣቱ ጋር አያይዞ ወጣቱ ላይ ብቻ ጣት መቀሰር አግባብ አይመስለኝም፡፡
ወጣቱ የአምባገነን ሥርዓቱን ለውጦታል፡፡ ከለወጠ በኋላ አሸጋግሩን ብሎ ለፖለቲካ አመራሩ አደራ ሰጥቶታል፡፡ ያንን የፖለቲካ አመራር በፍጥነት ሽግግሩን ከመጨረስ ይልቅ በተለያየ ሁኔታ ሌላ ስም ሊሰጠው አግባብ አይደለም፡፡
በሌላ በኩል ያነሳሽው ጥያቄ ከሕዝቡ ጋር ስለተደረሰበት ጉዳይ ነውና ወደ ምዕራብ የመጣነው በአካባቢው የጸጥታ ችግር እንዳለና የሕዝብም ቅሬታ መኖሩን ስለሰማን ነው፡፡ በኦነግና በመንግሥት መካከል አንዳንድ ነገሮች አሉ የሚል ነገር ስለሰማን ነው የመጣነው፡፡ ምክንያቱም ባለፉት አራት ዓመታት አብረን ስንታገልና ስናታግለው የነበረ እና ስናወጣ የነበረውን ስትራቴጂ እና ትዕዛዝ ሲያስፈጽም የነበረ ሕዝብ ዛሬ ችግር አለበት፤ ችግር ውስጥ ወድቋል ሲባል ከሩቅ ሆነን ከሚዲያ መስማት አልፈለግንም፡፡ ወደ አካባቢው በመሄድ ከሕዝቡ ከራሱ አንደበት ዓይናቸውን እያየን ማዳመጥ ፈለግን፡፡ ስለዚህም ከዚሁ ጋር ተያይዞ ካለን ተሰሚነት አንጻር የእኛ በስፍራው መገኘት የመንግሥትና የአገሪቱ እይታ እንዲሁም የሚዲያውን ቀልብ እንደሚስብ ስለምናውቅ ነገሮች እንዳይባባሱ ይረዳል ብለን ስላሰብን ነው፡፡
ከነቀምት ጀምሮ በብዙ ከተሞች ላይ ከሕዝቡ ጋር በግልጽ ተወያይተናል፡፡ ከአካባቢው ሕዝብ ሲነሳ የነበረው ሦስት ዋና ጉዳዮች ላይ ያጠነጠጠነ ነበር፡፡ ይኸውም አንዱ ከፀጥታና ከሰላም ጋር የሚነሳ ነው፡፡ ሁለተኛው ደግሞ የልማት መጓተትና የሥራ ሁኔታ መቀዛቀዝና መቆም ሲሆን፣ ሦስተኛ ደግሞ የአስተዳደር ሁኔታ መዳከምና ከላይ የጀመረው ለውጥ ወደታች አለመድረሱንና መዳከሙን የሚገልጽ ውይይት ነው የተደረገው፡፡ እነዚህን አስተያየቶችንና ጥያቄዎችን ሲያነሱ የነበረው በተደራጀ፣ በሰለጠነና ክብር ባለው መልኩ ነው፡፡ እኛም የቻልነውን ያህል ለመምክር ሞክረናል፡፡ የተረፈውን ደግሞ ላለው የመንግሥትም ሆነ የተፎካከካሪ አመራር ለማቅረብ ነው ያሰብነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- የኦሮሚያ ክልል አሁን እየተመራ ያለው በኦዴፓ አሊያም በመንግሥት መዋቅሩ ብቻም ሳይሆን እርስዎን ጨምሮ ተሰሚነት ባላቸው ታዋቂ በሆኑ አክቲቪስቶች ነው የሚሉ ወገኖች አሉና እዚህ ላይ ያልዎት አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ጃዋር፡- አሁን ያለው መንግሥት እኛም ባደረግነው ትግል እንዲሁም ቄሮዎችም ሆኑ ሌሎች ታጋዮች ባደረጉት ትግል የመጣው ነው ተብሎ የሚወሰድ ነው፡፡ ያለውን ሥርዓት ከማፍረስ ይልቅ ለውጥ ፈላጊውን ኃይል በማጠናከር የሽግግር ጊዜውን እንዲመራ ነው የስትራቴጂ ውሳኔ የተደረገው፡፡ ከዚህ አንጻር የእኛ ኃላፊነትም አሁን ያለው መንግሥት እንዲጠናከር ብሎም እንዳይዳከም የሽግግር ጊዜ ኃላፊነቱንም በተሳካ መልኩ እንዲያከናውን ፍላጎታችን ነው፡፡
ስለዚህም ከዚህ አንጻር በየቦታው እየሄድን ሕዝብን የማረጋጋትና ተስፋ እንዲኖረው የማድረግ ሥራ እንሰራለን፤ ይህ ደግሞ ትልቁ ኃላፊነታችን ነው፡፡ ይህም ብቻ አይደለም፤ በመንግሥትም ላይ ጫና በመፍጠር እንዲሁም በሚዲያም በመተቸትም ሆነ በውስጡ ምክረ ሃሳብ በማገዝ በፍጥነት ሕዝቡን እያዳመጡም የሽግግር ሁኔታውን በፍጥነት ወደፊት እንዲገፉት እየሞከርን ነው ያለነው፡፡ በተወሰነ ደረጃም እየተሳካልን እንገኛለን፡፡
ችግሩ ግን ምን መሰለሽ ወደ አማራ፣ ደቡብም፣ ቤኒሻንጉል ጉሙዝ ክልልም ሄጄያለሁ፡፡ ያስተዋልኩት ነገር ቢኖር ግን የታችኛው የመንግሥት ተቋም በጣም ተዳክሟል፡፡ ለመዳከሙ ማሳያ የሆነው አንደኛ ለ27 ዓመታት በአምባገነናዊ ሥርዓት የዘለቀ በመሆኑ ቅቡልነት የለውም፡፡ ታች ያሉ አመራሮች ከሕዝቡ ጋር ሲጋጩ የነበሩ ናቸው፡፡ ሲገዙ የነበረው በጉልበት ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ደግሞ ጉልበት ስለሌላቸው ተቀባይነትን አጥተዋል፡፡ የመሠረተ ልማት ሥራ ሰርተው እንኳ ሕዝቡን በጥቅም እንዳይዙት የገንዘብ አቅማቸው በጣም የተዳከመ ነው፡፡ ከዚህ የተነሳ የሚያሰጋ ሁኔታ ነው ያለው፤ አመራሮቹ በራስ የመተማመን ችግር ይታይባቸዋል፡፡
አዲስ ዘመን፡- ይህ እዚህም እዚያም የሚታየው ችግርና የፖለቲካው ሁኔታ እንዲሰክን መፍትሄው ምን ቢሆን ጥሩ ነው ይላሉ?
አቶ ጃዋር፡- አገሪቱ ሽግግር ውስጥ ነው ያለችው፡፡ ሽግግር ደግሞ ድልድይ ነው፡፡ እናም ድልድዩ አቅጣጫ ሊኖረው ይገባል፡፡ ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ የፖለቲካ አመራሩ ቁጭ ብሎ የምርጫ ሕግጋትን፣ የምርጫ ሥርዓት ላይ ተደራድሮና የሕዝቡ ዓይንና አዕምሮ የሆነ ቀንና ጊዜ እንዲሁም ፕሮግራም ላይ እንዲሆን ማድረግ አለባቸው፡፡
እንቅጩን አስረግጬ የምናገረው ኢህአዴግ አሁን ባለው ሁኔታ አገር ማስተዳደር አይችልም፡፡ ከታች ያለው መዋቅር ፈርሷል፡፡ ስለዚህ ሕዝቡ ይህን የፈረሰ ሥርዓት እያየ ትዕግስት እያጣ በመሄድ ላይ ነው፡፡ መንግሥት ሊሰጠው የሚገባውን የደህንነት፣ የልማትና ሌሎች ነገሮችን መስራት አልቻለም፡፡ የሚያስችለው አቅምም የለውም፡፡
እንደ ፖለቲካ ሊሂቃኖች ሆነን ሕዝቡ ጊዜ እንዲሰጠን ከፈልግን «ጊዜ ስጠን፤ ይኸው ቀነ ቀጠሯችን፤ ራስህ በመረጥከው መንግሥት ትተዳደራለህ» የሚለውን ማሳየት መቻል አለብን፡፡ ስለዚህ መፍትሄው አሶሳ ላይ አሊያም ጊምቢ ላይ የለም፡፡ ወይም ደግሞ አላማጣ ላይ የለም፡፡ ችግሩ አዲስ አበባ ውስጥ ነው፡፡ ስለዚህ የገዢው ፓርቲና የተፎካካሪ ፓርቲ አብረው ቁጭ ብለው ተደራድረው የሽግግር አቅጣጫ ካላስቀመጡ በቀር ወደ ከፍተኛ አደጋ ነው እየገባን ያለነው፡፡ ከታች ያለው የመንግሥት አካል ተሸመድምዷል፡፡ ይህም ወደ ላይ እየመጣ ነው፡፡
እንደ እኔ እኛም የሚፈለገውን መፍትሄው እያመጣን አይደለም፡፡ እኔ እዚህ አገር ከመጣሁ ጀምሮ በስፋት እየሰራሁ ያለሁት በኦሮሞና በሱማሌ ጉዳይ ላይ ነው፡፡ በየወረዳው ያሉትን ሽማግሌዎች ወይ እየሄድኩ አሊያም እየጠራሁ ሳወያይና ሳስታረቅ ነበር፡፡ ያ ማህበራዊ ሥራ ፖለቲካዊ ስምምነትን ይጠይቃል፡፡ በተለይ በክልሎችና በፌዴራል መንግሥት ደረጃ አስተማማኝ የሆነ ሕጋዊ እና የፖለቲካ መፍትሄ ያስፈልገው ነበር፡፡ ሁለት ወር ለፍተን የሰራንበት የማህበራዊ ሥራ ብትንትኑ ወጥቶ ነው ያገኘነው፡፡
አሁን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጀምሮ ያለው አመራር ትልቁ ሥራቸው የሽግግር ሥራ መስራት እንደሆነ መቀበል ነው፡፡ ተፎካካሪውም ኃይል አሁን ያለው መንግሥት የሽግግር መንግሥት መሆኑን ተቀብሎ መጋፋትን በመተው በመንግሥት ላይ የሚያደርገውን ጫና የሽግግር መንገዱን ማስተካከል ላይ ብቻ መሆኑ አለበት፡፡ ይህ ካልሆነ በስተቀር አገሪቱ ከፍተኛ አደጋ ውስጥ እየገባች መሆኗ ነው የሚታየኝ፡፡
አዲስ ዘመን፡- ማጣራት ተደርጎባቸው ለፍርድ የቀረቡ ተጠርጣሪዎችን የተመለከተ ዘጋቢ ፊልም መቅረቡ እንዲሁም ጠቅላይ ሚኒስትሩ መግለጫ መስጠታቸውም ይታወቃልና ይህ አካሄድ ግን በዳኞች ላይ ተጽዕኖ ይፈጥራል የሚሉ ወገኖች አሉና እዚህ ላይ የእርስዎ አስተያየት ምንድን ነው?
አቶ ጃዋር፡- ኢህአዴጋዊ አሠራር እኮ ነው የሆነው፡፡ ምክንያቱም እነዚህ ግለሰቦች በሙስና ተጠርጥረው ከተያዙ በፍርድ ተረጋግጦባቸው እስካልተፈረደባቸው ጊዜ ድረስ ንፁህ እንደሆኑ ነው የሚገመተው፡፡ ከዚህ አንጻር በተለይ የመንግሥት ሚዲያ በተጠርጣሪዎች ላይ የሚያቀርበው ዘጋቢ ፊልም የተበላሸ ኢህአዴጋዊ አሠራር እንዲሁም ፍትህን የሚያስፋፋ ሳይሆን ፍትህን የሚያጓድል አሠራር በመሆኑ በተጨማሪ ከዚህ በፊት ይደረግ የነበረ ዓይነት አካሄድ ነው፡፡
ከዚህ በፊት እኛ በዚህ ዓይነት አሠራር ተጠቂዎች ነበርን፡፡ አሸባሪ ተብለን ተከሰን በእኛ ላይ ዘጋቢ ፊልም ይሰራ ነበር፡፡ ፍርድ ቤት ሳይወስንብን በአሸባሪነት ስንከሰስ ነበር፡፡ ዛሬ ላይ ባሉ ሰዎች ጠንካራ ጥርጣሬ ቢኖረንና መረጃ እንኳ አለን ብለን ብንናገር ፍርድ ቤት እስኪወስንባቸው ድረስ በተለይ በመንግሥት ደረጃ የሚደረገው የፕሮፖጋንዳ ሥራ አደገኛና የፍትህ ሥርዓቱን የሚያስተጓጉል ነው፡፡
እንደ እኔ አመለካከት በተለይ ነፃ የሆነው ሚዲያ በራሱ መንገድ ሄደ ከሰራ አንድ ነገር ነው፡፡ እዚህ ጋር ከሳሽ መንግሥት ነው፡፡ ዓቃቤ ሕጉም፣ ፍርድ ቤት እንዲሁም የኢትዮጵያ ቴሌቪዥን የመንግሥት አካል ናቸው፡፡ የመንግሥት አካላት እየተረባረቡ የሚሰሩት ሥራ የመጨረሻው የፍርድ ውሳኔ ተዓማኒነት እንዲጎድለው የሚያደርግ፣ የኢትዮጵያ የፍርድ ሂደትም ከአምባገነናዊ ሥርዓት እንዳይላቀቅ የሚያደርግ ስለሆነ መቆም ያለበት ነው፡፡ በሚዲያ የምርመራ ዘገባ ይሰራ ከተባለ ለሁሉም ሚዲያ ምቹ ሁኔታ ተፈጥሮ መስራት ያለበት ሁሉም ሚዲያ ነው እንጂ አሁን እየተኬደበት ያለው አካሄድ ትክክለኛ አይደለም፡፡
እንደ እኔ አይደለም ዘጋቢ ፊልም መስራት ገለልተኛ የሆነ ዓቃቤ ሕግ ጉዳዩን በነፃና ከፖለቲካ አመለካከት በወጣ መልኩ ሊመረምረው ይገባል ባይ ነኝ፡፡ ምክንያቱም ይህን የምለው አንደኛ የፍትህ ሥርዓቱ እንዲለወጥ ነው፡፡ ሁለተኛ ደግሞ እንዲህ ዓይነት ትልልቅ የሆኑ የሙስና እና የሰብዓዊ መብት ጥሰት የፍርድ ሂደቶች የሚቀጥለውም ትውልድ የሚማርባቸው እንዲሆኑ መቻል አለባቸው፡፡ ቀጣዩ ትውልድ መማር የሚችለው ግን የፍትህ ሂደቱ ግልጽ፣ ገለልተኛና ተዓማኒ በሆነ መልኩ ከተካሄደ ብቻ ነው፡፡ በመሆኑም በመንግሥት በኩል የሚደረግ ፕሮፖጋንዳ የዳኞችንም አመለካከት የሚለውጥ ነው፡፡ የሕዝቡንም አመለካከት ባልተገባ መስመር እንዲሄድ የሚያደርግ ነው፡፡ ተከሳሾችም ደግሞ የሚመጣውን ፍርድ ሕጋዊ ነው ብለው እንዳይቀበሉ የሚያደርግ ነው፡፡
አዲስ ዘመን፡- በአገሪቱ ባለው ተጨባጥ ሁኔታ በ2012 ምርጫ እንደሚካሄድ ይጠበቃልና የተሳካ ምርጫ ማካሄድ ይቻላልን? ይህ ካልሆነ መሆን ያለበት ምንድን ነው ይላሉ?
አቶ ጃዋር፡- ይቻላልም፤ ግዴታም ነው፡፡ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አብይ አህመድ ወደ ሥልጣን ከመጡ ሰባት ወራትን አስቆጥረዋል፡፡ የጠቅላይ ሚኒስትሩ ትልቁና ዋነኛው ኃላፊነት የሚቀጥለው ምርጫ ፍትሃዊ፣ ዴሞክራሲያዊና ሰላማዊ እንዲሆን ማድረግ ነው፡፡ ይህንን ደግሞ ብቻቸውን የሚያደርጉት አይደለም፡፡ ከተፎካካሪዎች ጋር በመደራደርና በምርጫ ሕግጋትና ሥርዓት ላይ መወያየትን ይጠይቃል፡፡
ጊዜው እየሄደ ነው፤ ግን በዚህ ጉዳይ ምንም እየተሰራ አይደለም፡፡ ይህ ምርጫ በወቅቱና በሰላማዊ፣ ተዓማኒና ፍትሃዊ በሆነ መልኩ ካልተካሄደ ለዚህች አገር ከፍተኛ የሆነ አደጋ ነው ይዞ የሚመጣው፡፡ ለዚህ ማሳያው ምን መሰለሽ፤ አንዱ ኢህአዴግ የሚባል ሥርዓት ከታች ፈርሷል፡፡ ይህንን መቀበል መቻል አለባቸው፡፡ መልሰው ሊገነቡት አይችሉም፡፡ መልሶ ለመገንባት ከውስጥ ያሉና ሰው የሚጠላቸው ግለሰቦች መራገፍ አለባቸው፡፡ ይህን ደግሞ ማድረግ የሚችሉት በምርጫ ብቻ ነው፡፡ አለበዚያ አሁን ያለው ኢህአዴጋዊ አካሄድ ሊያራግፋቸው አይችልምና…
አዲስ ዘመን፡- መራገፍ አለባቸው ለሚለው አስተያየትዎ ማሳያው ሕዝቡ ግለሰቦቹን ባለመቀበሉ ነው? ወይስ…
አቶ ጃዋር፡- አዎ ሕዝቡ አይቀበላቸውም፤ አያዳምጣቸውምም፡፡ ኢህአዴግ የሚሾሟቸው ሰዎች የአቅምም የሞራልም ብቃት የላቸውም፡፡ ስለዚህ ምርጫውን አካሂደን ከታች ወደ ላይ ሕዝብ በመረጠው መዋቅር መተዳደር እስካልተቻለ ድረስ የመንግሥት መፈረካከስና መውደቅ ይመጣል ማለት ነው፡፡
ከዚህ አንጻር የሚቀጥለው ምርጫ ፍትሃዊና ዴሞክራሲያዊ መሆን የዴሞክራሲያዊ ጥያቄ ብቻ ሳይሆን የአገር ህልውናና አንድነት፣ የመንግሥት መቀጠል አለመቀጠል ጉዳይ ነው፡፡ ኢህአዴግ ሊወርድ ላይወርድ ይችላል፡፡ አንድ ፓርቲ ሥልጣን ሊይዝ ይችላል፡፡ ግን በአገሪቱ ሥርዓት መቀጠል መቻል አለበት፡፡ አሁን ግን እያልኩ ያለሁት ኢህአዴግ ብቻ አይደለም እየፈረሰ ያለው፤ ሥርዓቱም ነው እየፈረሰ ያለው፡፡ ያለው መዋቅር ሁሉ እየተሸመደመደ ነው፡፡ ይህንን መልሶ እንዲያንሰራራ ለማድረግ ምርጫ በጣም ወሳኝ ነው፡፡
በዚህ ረገድ እንደሚመስለኝ ኢህአዴጋዊ ጸባይ ስላለቀቃቸው እንደምንም ብለው መሬት ላይ አንከባለው አንከባለው ሲቀርቡ ‹የተሻለ አደረጃጀት አለን፤ እንዲሁም የፋይናንስና የሚዲያ አቅም አለን፡፡ ቀረብ ብለን ጥለን እንሄዳለን› የሚል አመለካከት እንዳለ ነው የሚታየኝ፡፡ ይህ አደገኛ የሆነ አስተሳሰብ ነውና አስረግጬ የምናገረው አሁን ባለው ተጨባጭ ሁኔታ ምርጫን መስረቅም ማጭበርበርም አይቻልም፡፡ ለማጭበርበር የሚያስችል ድሮ የነበረው የኢህአዴግ መዋቅር የለም፡፡ ወይ ከድቷል፤ ወይ ፈርቷል፡፡ ከዚህ አንጻር የምርጫ ጉዳይ ቁጥር አንድ አጀንዳ ሆኖ መሄድ አለበት፡፡
የምርጫ ቦርድ ሊቀመንበርም በጠቅላይ ሚኒስትሩም ሆነ በኢህአዴግም መሾም የለበትም፡፡ በተፎካካሪ ፓርቲዎችም ጭምር በሚደረግ ውይይት ተዓማኒነት ባለው መንገድ ነው መሾም ያለበት፡፡ የምርጫ ሕጉም ይለወጣል እየተባለ ነውና ኢህአዴግ ብቻውን ማድረግ አይኖርበትም፡፡ ሌሎቹም መሳተፍ አለባቸው፡፡
አዲስ ዘመን፡- ስለሰጡኝ ማብራሪያ አመሰግናለሁ፡፡
አቶ ጃዋር፡- እኔም አመሰግናለሁ፡፡