ያለወቅቱ ደርሶ የሚያንዣብበው ደመና በሰበታ ሃዋስ ወረዳ አርሶአደሮች ዘንድ ስጋትን ካሳደረ ውሎ አድሯል። በአከባቢው ሰብልን በኮምባይነር መሰብሰብ እምብዛም የተለመደ ባለመሆኑ ከዛሬ ነገ ዘንቦ የደረሰ ሰብላቸውን እንዳያበላሽባቸው ሰማዩን በስጋት ከመመልከት ባለፈ አርሶ አደሮቹ በተለመደው የመተባበር ባህላቸው ሰብሎቻቸውን የመሰብሰብ ተግባራቸውን በትጋት ያከናውናሉ። ሆኖም ይህን ስጋታቸውን በተወሰነ መልኩም ቢሆን የሚያቃልል ነገር በዚህ ዓመት አግኝተዋል፤ የስንዴ መውቂያ ማሽን።
ይህን ማሽን ካገኙት መካከል የወረዳዋ የባልጪ ጂምጂም ቀበሌ አርሶአደሮች ተጠቃሽ ናቸው። እነዚህ አርሶ አደሮች አሁን ላይ በደቦ የሰበሰቧቸውን የደረሱ ሰብሎች በዝናብ እንዳይበላሹባቸው በመውቃት ሂደት ላይ ተጠምደዋል። ጤፍና ባቄላን የመሳሰሉ ምርቶችን በሰው ጉልበትና በበሬ፤ ስንዴን ደግሞ በመውቂያ ማሽን እየወቁ ወደጎተራ በማስገባት ላይ ይገኛሉ።
አርሶ አደር ቦጋለ በዳዳ እና ለገሰ ያዳ፣ የወራት ልፋት ውጤታቸው የሆነውን ሰብል ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ ለማድረግ በሰውም በማሽንም ታግዘው የመሰብሰብና የመውቃት ተግባር እያከናውኑ ካሉ የቀበሌው አርሶአደሮች መካከል ናቸው።
አርሶአደር ቦጋለ እንደሚሉት፤ የስንዴ መውቂያ ማሽኑ መገኘት በቀላሉ ለዝናብ ተጋላጭና ለመበላሸት ዕድሉ ከፍተኛ የነበረው የስንዴ ምርት ቶሎ ተወቅቶ ወደጎተራ እንዲያስገቡ ዕድል ፈጥሮላቸዋል። በማሽኑ በሁለትና ሦስት ሰው ጉልበት በሰዓታት ጊዜ ውስጥ የሚያከናውኑት የሰብል መውቃት ሥራ በበሬና በሰው ጉልበት ቢሆን በ20 በሬዎች በሁለትና ሦስት ቀናት አጠናቅቆ ለማስገባት አይቻልም ነበር።
ምርጥ ዘርና ማዳበሪያ በመጠቀማቸው ዘንድሮ በሄክታር እስከ አርባ ኩንታል የማግኘት ሃሳብ የነበራቸው አቶ ቦጋለ፤ ሰብሉ በመሰብሰቢያው ወቅት ዝናብ የመከሰቱ ሁኔታ ስጋት ፈጥሮባቸው ነበር። የማሽኑ መገኘት ስጋታቸውን ቀንሶላቸዋል፤ በውቂያ ወቅት የሚፈጠርን የምርት ብክነትና ልፋትም አቃሎላቸዋል። ካለው ፍላጎትና የዝናብ ስጋት አኳያ አሁንም ማሽኑን አርሶአደሩ በስፋት እየፈለገው ሲሆን፤ በሌሎች የሰብል ዓይነቶች ላይ ተመሳሳይ ማሽን ባለማግኘቱ በቀጣይ ሊታሰብበት እንደሚገባ ጠቁመዋል።
አርሶ አደር ለገሰ በበኩላቸው እንደሚናገሩት፤ ቀደም ሲል ስንዴንም ሆነ ሌሎች ሰብሎችን ለማምረት የእርሻም ሆነ የአጨዳ እንዲሁም ውቂያውን በሰው ጉልበት፣ በበሬና በአህዮች ታግዘው ሲከውኑ ቆይተዋል። ዘንድሮም በተመሳሳይ መልኩ ያከናወኑ ቢሆንም፤ በሰብል መውቂያ ወቅት የስንዴ መውቂያ ማሽን ማግኘት በመቻላቸው ሰብላቸውን ሳይባክን ወደጎተራ ለማስገባት ዕድል ሰጥቷቸዋል።
አርሶ አደር ለገሰ ፤በስንዴው መሰብሰቢያ ሰዓት የታየው ደመናም ዝናብ ሊያስከትል እንደሚችል ስጋት ያሳደረባቸው ሲሆን፤ የአጨዳ ሥራውን በህብረት ቢያከናውኑም፤ አጭዶ መከመር ብቻውን ስንዴውን በዝናብ ከመበላሸት ስለማያድነው በወቅቱ ወቅቶ ከማስገባት አኳያ ስጋት ገብቷቸው ነበር።
የማሽኑ መገኘት ምርቱ በዝናብ እንዳይበላሽ ስላደረገላቸው ከስጋት ድነዋል። ሌሎች አርሷደሮችም በዚያው አግባብ ስንዴን የመውቃት ሂደቱን እያከናወኑ ሲሆን፤ ለጤፍና ለሌሎች የሰብል ዓይነቶች መውቂያ ማሽን ቢገኝ ምርትን በወቅቱ መሰብሰብ እንደሚቻል ይገልጻሉ።
አርሶአደር አበበ ገብርዬ የቀበሌው ነዋሪና የቀበሌው አርሶአደሮች በማህበር ያገኙትን የስንዴ መውቂያ ማሽን ተቆጣጣሪ ናቸው። እርሳቸው እንደሚሉት፤ በአካባቢው የማጨጃ ኮምባይነር ብዙም የተለመደ ባለመሆኑ አርሶአደሩ ሰብሉን በደቦ አጭዶ በየማሳው የከመረ ቢሆንም፤ በአሁኑ ወቅት በተከሰተው ደመና አማካኝነት ዝናብ ቢጥል እህሉ እንዳይበላሽበት ስጋት ላይ ወድቋል። የማሽኑን መምጣት ተከትሎም ዝናብ ከመጣሉ በፊት ሰብሉን ወቅቶ ለማስገባት ወረፋ እየያዘ ይገኛል።
ማሽኑ በሰዓት አስር ኩንታል የመውቃት አቅም ያለው ሲሆን፤ በእንስሳትና በሰው ጉልበት የሚከናወነውን አድካሚ ሥራ ቀንሶና የምርት ብክነትን አስወግዶ በሰዓታት ውስጥ ሰብልን መውቃት አስችሏል። ይሁን እንጂ ቴክኖሎጂዎች እየተሻሻሉ ከመሄዳቸው ጋር ተያይዞ አርሶአደሩ በቀጣይ ሌሎች ሰብሎችን በማሽን ሊሰበስብ የሚችልበት ዕድል ሊመቻችለት ይገባል።
የሰበታ ሃዋስ ወረዳ የግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ጽህፈት ቤት ኃላፊ አቶ ታፈሰ ካሳዬ እንደገለጹት፤ በምርት ዘመኑ በወረዳው በታቀደው መሰረት 57ሺ 148 ሄክታር መሬት ታርሶ በሰብል የተሸፈነ ሲሆን፤ የግብርና ፓኬጆችን በመተግበርም በሄክታር በአማካይ 34ነጥብ 22 ኩንታል ምርት ይገኛል በሚል አንድ ነጥብ92 ሚሊየን ኩንታል ምርት የማገኘት ግብ ተቀምጦ ተሠርቷል።
ይሁን እንጂ በወረዳው ጎርፍና የዋግ በሽታ ተከስቶ ስለነበር በተደረገው የቅድመ ምርት ትንበያ በምርታማነቱ ላይ ቅናሽ እንደሚያሳይና በሄክታር እስከ 31ነጥብ 22 ኩንታል እንደሚገኝ ተገምቷል። የምርት ዘመኑን የምርታማነት ደረጃ ለማወቅም የድህረ ምርት ግምገማ እየተሠራ ይገኛል።
እንደ ጽህፈት ቤት ኃላፊው ማብራሪያ፤ በአሁኑ ወቅት በወረዳው አብዛኛው የሰብል ምርት ደርሶ እየተሰበሰበ ሲሆን፤ ከዚህ ውስጥ 85 በመቶውን መሰብሰብ ተችሏል። የምርት ስብሰባ ሂደቱ ወቅቱን ባልጠበቀ ዝናብ እንዳይበላሽ የሚያስችሉ ተግባራት እየተከናወኑ ሲሆን፤ ለዚህም አርሶአደሩ በደቦም በማሽኖች ታግዞ ሰብሉን እንዲሰበስብ እየተደረገ ይገኛል።
አርሶአደሩ እየተደራጀ የስንዴ መውቂያ ማሽኖችን እንዲገዛ በመደረጉ በወቅቱ ስንዴውን እንዲሰበስብና በዝናብ ከመበላሸት እንዲታደግ ማድረግ ተችሏል። በቀጣይም መሰል ተግባራት የሚከናወኑ ሲሆን፤ በተለያየ መልኩ ተደራጅተው ማሽን ያላገኙ አርሶአደሮች ወደሥራ የሚገቡበት ዕድል ሲፈጠርም በአርሶአደሩ የሚነሱ ጥያቄዎች እየተመለሱ የሚሄዱበት አግባብ ይኖራል።
አዲስ ዘመን ህዳር 27/2012
ወንድወሰን ሽመልስ