አዲስ አበባ፡- የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል አገልግሎት እየሰጠ ያለ አንድ የኤም አር አይ የሕክምና መሣሪያ ቢኖረውም ለማሽኑ ክትትልና ጥገና የሚያደርግ፣ ልዩ ስልጠና የወሰደ ባለሙያ እንደሌለው የሆስፒታሉ የባዮ ሜዲካል ኢንጂነሪንግ ዘርፍ ሃላፊ አስታወቁ፡፡
ሃላፊው ኢንጂነር ለማ ቁንቢ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንዳስታወቁት የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል ከመላው የአገሪቱ ክፍሎች በየቀኑ ለሚመጡ ከ30 በላይ ታካሚዎች የኤም አር አይ የምርመራ አገልግሎት የሚሰጥ ቢሆንም መሣሪያው ለብልሽት ሲዳረግ ፈጣን ጥገና በማድረግ አገልግሎት እንዲሰጥና አገልግሎት ፈላጊውም ሳይጉላላ አገልግሎቱን እንዲያገኝ እንዲሁም መሣሪያው በሚፈለገው ደረጃ የተሟላ አገልግሎት እንዲሰጥ ማድረግ የሚችል በዘርፉ የሰለጠነ ባለሙያ እንደሌለው ተናግረዋል።
ኢንጂነር ለማ እንዳሉት፤ ኤም አር አይ ማሽኑ በሆነ ምክንያት አገልግሎት መስጠት ሲያቆም አስመጪው ኩባንያ በደብዳቤ ተጠይቆ የሚልካቸው ባለሙያዎች በክፍያ ወይም ከውጭ ሌላ ባለሙያ ተፈልጎ ይጠገናል። ይህ ሂደት ደግሞ በራሱ የሚወስደው ጊዜ ረዥም በመሆኑ ለአገልግሎት የሚመጡ ሰዎች እንዲጉላሉና ለአላስፈላጊ ወጪና እንግልት እንዲዳረጉ እያደረገ ነው።
የፌዴራል መድሃኒት ፈንድ አቅርቦት ኤጀንሲ መሣሪውን በሚገዛበት ወቅት ማሽኑ ቢበላሽ ባለሙያዎቹን ልኮ ኩባንያው እንዲጠግን እስከ አምስት ዓመት ድረስ የዋስትና ውል መፈራረም ይችል ነበር የሚሉት ኢንጂነር ለማ፤ በሌላ በኩል ደግሞ ኩባንያው ባለሙያዎችን እንዲያሠለጥንላቸው ማድረግ ይችሉ ነበር ብለዋል።
ገዥው አካል እስከ ማስገደድ ወይም ደግሞ እስከ መቀየር የሚደርስ መብት እንደነበረው የሚያስረዱት ሃላፊው፣ የሆስፒታሉ የሕክምና ባለሙያዎች በቀጥታ ከኩባንያው ጋር የሚገናኙበት አሠራር አለመኖሩን ተናግረዋል።
የሕክምና መሣሪያዎች ችግር የሚነሳው ከፖሊሲ እንደሆነ የሚያነሱት ኢንጂነር ለማ፤ ኤም አር አይም ሆነ ሌሎች የሕክምና መሣሪያዎች የሆነ የመለዋወጫ አካል ቢጎድላቸው መግዛት የሚያስችል ቀጥተኛ የፋይናንስ አሠራር አለመኖሩን ገልፀው፣ የበጀት አርዕስት ጭምር የሌላቸው በመሆኑ ለግዥ ሥርዓቱም አስቸጋሪ መሆናቸውን አስረድተዋል። ይሁን እንጂ አሁን እየተከናወኑ በሚገኙ የዘርፉ የሪፎርም ሥራዎች ችግሮቹ ሊቃለሉ እንደሚችሉ ነው የጠቆሙት።
ከአሥር በላይ የሕክምና መሣሪያ መሐንዲሶች በሆስፒታሉ የሚገኙ ቢሆንም የኤም አር አይ ማሽኑ ከተተከለ በኋላ በማንዋሎች እየታገዙ በራሳቸው ጥረት በንባብ በሚያዳብሩት እውቀት ከመደገፍ የዘለለ መጠገንና መለዋወጫዎች ገዝቶ እስከ መቀየር የሚያደርስ መፍትሄ ማምጣት የሚችሉ እንዳልሆኑም ሃላፊው ተናግረዋል። በዚህ የተነሳ የሆስፒታሉ የኤም አር አይ ማሽን በብልሽት ምክንያት ከሰባት ወር በላይ ቆሞ በቅርቡ ወደ ሥራ መመለሱን ጠቁመዋል።
የፌዴራል መድሃኒት አቅርቦት ኤጀንሲ የሕዝብ ግንኙነት ዳይሬክተር ወይዘሮ አድና በሬ በበኩላቸው የሕክምና መሣሪያዎች በሚቀርቡበት ጊዜ አቅራቢው አካል የሚገባው የዋስትና ጊዜ መኖሩን አንስተው ፣ በዚያ ጊዜ ውስጥ መሣሪያው ብልሽት ቢገጥመው ኩባንያው ጥገናውን እንደሚያከናውን ገልፀዋል።
ከዋስትና ጊዜ በኋላ የሕክምና መሣሪያዎች ብልሽት ሲገጥም የጠጋኝ ባለሙያ ችግር መኖሩ በአገር አቀፍ ደረጃ የሚታወቅ ነው ያሉት ዳይሬክተሯ፤ አሁን ላይ “ፕሌስመንት” የሚባል አሠራር እንደተጀመረ ጠቁመው፣ አቅራቢው የሕክምና መሣሪያዎችን ሲያቀርብ ለነዚያ መሣሪያዎች የሚያሥፈልጉ ‹‹ሪኤጀንቶችን›› በቀጣይነት ማቅረብ እንዲችል ለረዥም ጊዜ (ሦስት ዓመት) የሚደርስ የግዥ ውል በማስፈረም የሕክምና መሣሪያዎችን ጥገና፣ ተከላ፣ የባለሙያዎች ስልጠና እና ሌሎች የሚያጋጥሙ ችግሮችን እየተከታተለ መፍትሄ እንደሚሰጥ ተናግረዋል።
በአንድ ጊዜ ለሚከናወን የኤም አር አይ ምርመራ የጥቁር አንበሳ ሆስፒታል 500 ብር የሚጠይቅ ሲሆን አገልግሎቱን በሚሰጡ ሌሎች የግል ሆስፒታሎች ግን እስከ ሦስት ሺህ ብር ያስከፍላል። ማሽኑ በተለይ አዕምሮ፣ ህብለሰረሰር፣ ነርቮችና ጡንቻዎችን የመሳሰሉ የሰውነት የውስጥ ክፍሎችን ጥራት ባለው ምስል በማሳየት ህክምና ለመስጠት የሚያግዝ ዘመናዊ መሣሪያ ሲሆን መሣሪያው ጨረርን የማይጠቀም መሆኑም ተመራጭ እንደሚያደርገው ባለሙያዎቹ ይናገራሉ።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2012
ሙሐመድ ሁሴን