-በምስረታውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ውይይት እየተካሄደ ነው
አዲስ አበባ፡- የብልጽግና ፓርቲ ውህደት ሕጋዊ ሥርዓትን የተከተለ መሆኑ ተገለፀ፡፡ ፓርቲውን የመሰረቱ ድርጅቶች በምስረታውና ተያያዥ ጉዳዮች ዙሪያ ከህብረተሰቡ ጋር ውይይት እያካሄዱ ነው፡፡
የኢህአዴግ ጽህፈት ቤት ሃላፊ አቶ ብናልፍ አንዱዓለም እንደገለፁት አዲሱ የፖለቲካ ፓርቲዎች ውህደት ሕግ እና ሥርዓትን የተከተለ በመሆኑ አግላይ ነው እንዲሁም ሕግን መሰረት አላደረገም የሚሉ ሐሳቦች ተቀባይነት የላቸውም፡፡
ኃላፊው እንዳሉት፤ የግንባሩ አባል ድርጅቶች በጥርጣሬና አንዱ ድርጅት ሌላውን የጋራ አድርጎ ማሰብ ሳይሆን እንደሌላ ተፃራሪ አካል አድርጎ የመተያየት ሁኔታዎች ተፈጥረው የነበረ በመሆኑ ድርጅቱ አደጋ ላይ ወድቆ ቆይቷል።
ችግሩን ለመፍታት በተለያዩ ጊዜያት በተካሄዱ የኢህአዴግ ጉባኤዎች በጥልቀት በመገምገም የተቀመጡ አቅጣጫዎችን መሰረት በማድረግ ግንባሩን ለማዋሐድ ተሠርቷል ብለዋል።
በብልጽግና ፓርቲ ፕሮግራም ላይ የምንገነባው ዴሞክራሲ በመግባባት ላይ የተመሰረተ መሆን እንዳለበት ተቀምጧል ያሉት ሃላፊው፣ በዚህ የዴሞክራሲ ባህልም ጠንካራ ሀገር መንግሥት እና ብሔረ መንግሥት መገንባት እንችላለን ብለዋል።
የብልጽግና ፓርቲ ምስረታን የተቀበሉና ህዝባዊ ወይይቱን እያካሄዱ ካሉ ድርጅቶች መካከል የአዴፓ ማዕከላዊ ዞን (የክልል አመራሮች)፣ የዞን አመራሮችና የባህር ዳር የሁሉም ክፍለ ከተማ አመራሮች በተገኙበት የድርጅቱን ፕሮግራም፣ የመተዳደሪያ ሕገ ደንብና የድርጅቱን አወቃቀር፣ የንቅናቄው የህዝብ ግንኙነትና ኮሚዩኒኬሽን ዕቅድ እንዲሁም በፓርቲው ላይ የሚነሱ የተለያዩ የግልፀኝነት ጥያቄዎችን አስመልክቶ ውይይቶች በመደረግ ላይ ናቸው፡፡
የአዴፓ ማዕከላዊ ኮሚቴ ጽህፈት ቤት የፖለቲካ ዘርፍ ኃላፊ አቶ አብርሃም አለኸኝ እና ምክትል ኃላፊው አቶ መስፍን በዚሁ ወቅት ባደረጉት ገለፃ መድረኩ ከህዳር 25 ቀን እስክ ታህሳስ 10 ቀን 2012 የዞን፣ የወረዳና የቀበሌ አመራሮችን፣ የከተማና የገጠር ወጣትና ሴቶችን፣ የኪነ ጥበብ ሙያተኞችን፣ ምሁራንና የሲቪክ ማኅበራትን በማግኘት ገለፃዎች ለማድረግ ከተያዘው ዕቅድ የመጀመሪያው መሆኑን የአማራ ብዙኀን መገናኛ ድርጅት ዘግቧል፡፡
በሌላ በኩል የብልጽግና ፓርቲ ውህደት አስፈላጊነትና ቀጣይ አቅጣጫ ላይ የተካሄደው የደቡብ ክልል አመራሮች መድረክ የነቃ ተሳትፎ ተደርጎበት በመተማመን መጠናቀቁን የደቡብ ብልጽግና ፓርቲ ዛሬ በጽህፈት ቤቱ በሰጠው ጋዜጣዊ መግለጫ አስታውቋል፡፡
የደቡብ የብልጽግና ፓርቲ የህዝብ ግንኙነትና ሚዲያ መምሪያ ኃላፊ አቶ ገዛኸኝ ሜጎ እንዳሉት፤ በውይይቱ በስፋት የተነሳው የውክልና ጉዳይ ሲሆን በተለያዩ ማህበራዊ ሚዲያ የደቡብ ክልል ውክልና በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ ይቀንሳል ተብሎ የሚናገሩት መረጃን መሠረት ያላደረጉ መሆኑን ገልፀው በብልጽግና ፓርቲ ውስጥ የሥራ አስፈፃሚ ቁጥር ሳይቀንስ ይቀጥላል ብለዋል፡፡
ውህደቱን አስመልክቶ የሚደረጉ ህዝባዊ የውይይት መድረኮች ውህደቱን በተቀበሉ ክልሎች እንደሚቀጥልም ለማወቅ ተችሏል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2012
አዲሱ ገረመው