– ያለሥራ የተቀመጡ አንዳንድ ቦታዎች የሰላም ስጋት ሆነዋል
ሰበታ፡- በሰበታ ሃዋስ ወረዳ ከሚገኙ 47 የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች ውስጥ 34ቱ ወደ ሥራ አለመግባታቸው ተገለጸ። ያለሥራ የተቀመጡ አንዳንድ ቦታዎች የሰላም ስጋት መሆናቸውም ተጠቁሟል።
የወረዳው የኢንቨስትመንት ጽሕፈት ቤት ኃላፊ አቶ ግርማ ከበደ በተለይ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ በወረዳው ከኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶቱ ወደ ምርት የገቡት 13ቱ ብቻ ሲሆኑ፤ የተቀሩት ገሚሱ ግንባታ ላይ፣ ገሚሱ ደግሞ ግንባታ አጠናቀው ወደ ምርት ለመግባት ሙከራ ላይ ይገኛሉ።
አንዳንዶቹም ግንባታ ጨርሰው ማሽን ለመግጠም ከውጭ የሚገቡ ማሽኖችን ለመግዛት በውጭ ምንዛሬ ችግር ምክንያት የተቀመጡ ሲሆን፤ አንዳንዶቹም ግንባታ ጨርሰው የኤሌክትሪክ ኃይል በመጠባበቅ ላይ እንዳሉም ኃላፊው ጠቁመዋል።
በወረዳው ያለው የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች እንቅስቃሴ አበረታችና ተስፋ ሰጪ ቢሆንም አንዳንድ የኢንቨስትመንት ፕሮጀክቶች በገቡት ውል መሰረት ከመሥራት ይልቅ፤ ጀምረው ያቋረጡበት፤ ለህዝቡም ተስፋ አሳይተው የጠፉበት፤ የያዙትንም ቦታ ያለሥራ ባክኖ ለዓመታት እንዲቀመጥ ያደረጉበት ሂደት መታየቱንም አቶ ግርማ ጠቁመዋል።
በዚህ መልኩ ሦስት ፕሮጀክቶች ተጠቃሽ ናቸው ያሉት አቶ ግርማ፣ ከእነዚህ ውስጥ በ23 ሄክታር መሬት ላይ የአግሮ ኢንዱስትሪ ለማቋቋም ውል የወሰደው ካሱ በርኼ የተሰኘ ፕሮጀክት የነበረበትን ክፍተት እንዲያርም በወረዳው በተነገረው መሠረት ችግሩን አርሞ ወደ ማልማት ሥራ ተመልሷል ብለዋል።
በአንፃሩ ሞቢል ላንድ ፈርኒቸር እና ሮዝ ፋርም የተሰኙ ፕሮጀክቶች ቦታውን ያለ ሥራ እንዲቀመጥ ከማድረጋቸውም በላይ፤ ለአካባቢው ህብረተሰብ የመልካም አስተዳደር ምንጭ ሆነዋል፤ የአካባቢው ሰላም ስጋት እስከ መሆን ደርሰዋል ብለዋል።
በሰበታ ሃዋስ ወረዳ የደበል ዮሐንስ ቀበሌ ተወላጅና ነዋሪ የሆኑት አቶ መገርሳ ተስፋዬም ፣ ሮዝ ፋርም ትቶት የሄደውና ዛሬ ላይ ምድረ በዳ ሆኖ የቀረው መሬት፤ በደርግ ዘመን አንድ የዕርዳታ ድርጅት መዋዕለ ሕፃናት አቋቁሞ ቦታው ላይ ሲያስተምርበት እንደነበር ይጠቅሳሉ።
ኢህአዴግ ከገባ በኋላ ግን ድርጅቱ በመልቀቁ ቦታው ለአምስት ዓመታት ያለ ሥራ መቀመጡንና በ1991 ዓ.ም ግንቦት ወር ላይ ግን አንድ የውጭ ባለሀብት ቦታውን አጥሮ የአበባ እርሻ ሥራ እንደጀመረበት ተናግረዋል።
በሂደት ሥራውን በማስፋት ለአካባቢው ህብረተሰብ ሥራ ፈጥሮ እየሠራ ሳለ፤ በመሃል ባላወቁት ምክንያት ንብረቶችን ሽጦና ሠራተኛውንም አባሮ በስፍራው በጥበቃ ላይ ለነበሩ ሠራተኞች እንኳን ደመወዛቸውን ሳይከፍል ባዶ ሜዳ ላይ ጥሎ መሄዱንም ጠቁመዋል።
አቶ መገርሳ እና ሌሎች የአካባቢው ነዋሪዎች እንደሚሉት፤ ባለሀብቱ ባዶ ቦታ ትቶ ሲወጣ በአካባቢው ምንም ዓይነት የጸጥታ ችግር አልነበረም። የአካባቢው ህብረተሰብም በተፈጠረለት የሥራ ዕድል ከመደሰትና የተሻለ ተጠቃሚ እንደሚሆን ተስፋ ከማድረግ ያለፈ ምንም ተጽዕኖ አላደረገበትም።
የተፍኪ አካባቢ ቀበሌ አርሶአደሮች ከአበባ እርሻው የሚወጣው ኬሚካል ሽንብራና ምስር የመሳሰሉ ሰብላቸውን ሲጎዳባቸው እንኳን ነገ የተሻለ ሠርቶ ሲያገኝ መብራትና ውሃ ሊያስገባልን ይችላል በሚል እምነት ከመደገፍ ባለፈ የተናገሩት ምንም ነገር እንዳልነበረና ባለሀብቱ ባዶውን ትቶት የሄደው ቦታ ወይ ለአካባቢው ሥራ አጥ እንዲሠራበት ባለመደረጉ ወይም ሌላ ባለሀብት ገብቶ እንዲያለማበት ባለመሆኑ ዛሬ ላይ ምድረ በዳ ሆኖ ያለምንም አገልግሎት መቀመጡን በቁጭት የሚገልጹት አቶ መገርሳ፣ ከአምስት ዓመት በላይ የማንም መጨፈሪያ ብቻ ሳይሆን ለአካባቢው የሰላም ስጋትም የመልካም አስተዳደር ጥያቄም እየሆነ መምጣቱን ይገልጻሉ።
በመሆኑም ቦታው በዚህ መልኩ ባክኖ ከሚቀር ወይ ሥራ አጥተው በየቦታው ለሚንከራተቱ የአካባቢው ወጣቶች እንዲሠሩበት ሊደረግ፤ ካልሆነም ሌላ ባለሀብት ገብቶ ለወጣቱም፣ ለአካባቢውም ለአገርም የሚጠቅም ሥራ እንዲያከናውንበት በመንግሥት በኩል እንዲሠራ እና ቦታው በአስቸኳይ ወደልማት እንዲገባ ሲሉ ጥሪያቸውን አስተላልፈዋል።
በወረዳው ለኢንቨስትመንት ተሰጥተው ያለሥራ ባክነው ከቀሩ ቦታዎች አንዱ ገንደ ሀሮ በሚባለው አካባቢ የተጀመረውና ሞቢል ላንድ የተባለ የፈርኒቸር የተሰኘ ኢንቨስትመንት ፕሮጀክት ደግሞ በ2007 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ውል ገብቶ በ3 ነጥብ 34 ሄክታር መሬት ወስዶ ወደ ግንባታ ሥራ የገባ ቢሆንም፤ ይሄ የውጭ ባለሀብት ግንባታውን ወደማጠናቀቅ በደረሰበትና ለአካባቢው ህዝብም ሆነ ወጣት የተስፋ ጭላንጭል በማሳደር ላይ እያለ ከአንድ ዓመት በፊት ግንባታውን ባልታወቀ ምክንያት አቋርጦ ወጥቷል። በዚህም ከአንድ ዓመት በላይ የፕሮጀክቱ ጥበቃዎች ያለደመወዝ እንዲሠሩ፤ የአካባቢው ህብረተሰብም የመልካም አስተዳደር ጥያቄ እንዲያነሳ ሆኗል።
ጎልደን ሮዝ የተባለው የአበባ እርሻ ኢንቨስትመንትም በ1990 ዓ.ም የኢንቨስትመንት ፈቃድ ወስዶ በ20 ሄክታር መሬት ላይ ሥራ የጀመረ ሲሆን፤ በ1994 ዓ.ም ደግሞ ለማስፋፊያ ሥራ የሚሆን 13 ነጥብ 26 ሄክታር መሬት ወስዶ በጥቅሉ በ33 ነጥብ 26 ሄክታር መሬት ላይ ሥራውን ሲሠራ ቆይቷል።
በዚህም ከአንድ ሺህ በላይ ለሚሆኑ ሰዎች የሥራ ዕድል ፈጥሮ ሲያሠራ፤ ለአገርም የውጭ ምንዛሬ ሲያስገኝ ቆይቷል። ይሁን እንጂ ከሰባት ዓመት በፊት ምክንያቱ ሳይታወቅ ሥራውን ትቶ ወጥቷል።
ወረዳውም ጉዳዩን ለማወቅ በተደጋጋሚ ደብዳቤ እየጻፈ ባለሀብቱ ለምን ሥራውን አቋርጦ እንደወጣ እንዲታወቅና ተመልሶም ልማቱን እንዲያከናውን ለዞንም ለክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ጥያቄ ቢያቀርቡም ዞኑ ጉዳዩን ተመልክቶ ከእሱ አቅም በላይ መሆኑን በመግለጽ ለክልል ማሳለፉን አሳውቋል።
የክልሉ ኢንቨስትመንት ኮሚሽን ግን እስከአሁን ምላሽ መስጠት እንዳልቻለ ጠቁመዋል። በመሆኑም የሚመለከተው አካል በጉዳዩ ላይ ምላሽ ሊሰጠው ይገባል ሲሉ አስተያየታቸውን ሰጥተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2012
ወንድወሰን ሽመልስ