ሻሸመኔ፡- በኦሮሚያ ክልል ምዕራብ አርሲ ዞን ሻሸመኔ ወረዳ በ2012 በጀት አመት 15 ሺ አርሶአደሮችን በችግኝ ማፍላት ስራ በማሳተፍ ተጠቃሚ ለማድረግ መታቀዱን የወረዳው ግብርናና ተፈጥሮ ሀብት ፅህፈት ቤት አስታወቀ።
በፅህፈት ቤቱ የአፈርና ውሃ ከፍተኛ ባለሙያ አቶ ዘሪሁን ባህሩ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ በበጀት አመቱ በመንግስት፣ በአርሶአደሮች፣ በግለሰቦችና መንግስታዊ ባልሆኑ ድርጅቶች እጅ ባሉ 257 የችግኝ ማፍያ ጣቢያዎች 14 ነጥብ 2 ሚሊዮን ችግኞችን ለማፍላት የታቀደ ሲሆን በዚህም 15 ሺ አርሶአደሮች ተጠቃሚ ይሆናሉ ተብሏል።
እንደ አቶ ዘሩሁን ገለፃ ከሚፈሉት ችግኞች ውስጥ 11 ነጥብ 1 ሚሊዮን ያህሉን በ 1 ሺ 100 ሄክታር መሬት ላይ ለመትከል የቅድመ ዝግጅት ስራዎች እየተከናወኑ ነው።
የዚህ ስነህይወታዊ ስራ አንዱ አካል የሆነውና ከመጪው ጥር 1/2012 ዓ.ም ጀምሮ በወረዳው ለሚከናወነው ስነ አካላዊ የአፈርና ውሃ ጥበቃ ስራ 7 ሺ ሄክታር መሬት መዘጋጀቱንም አቶ ዘሪሁን ጨምረው ገልፀዋል።
በሻሸመኔ ወረዳ ባለፈው የ2011 ዓ.ም በጀት አመት በመደበኛና የአረንጓዴ አሻራ ሀገር አቀፍ የችግኝ ተከላ መርሀ ግብር 27 ሺ 700 አርሶ አደሮችን በማሳተፍ 9 ነጥብ 8 ሚሊዮን ችግኝ ማፍላት የተቻለ ሲሆን ከዚህ ውስጥ 6 ነጥብ 3 ሚሊዮን ያህሉ ተተክሏል ተብሏል።
የግብርና ሚኒስቴር በሁለቱም መርሀግብሮች የተተከሉ ችግኞች አሁን ያሉበትን ሁኔታ ለሚዲያ አካላት ባስጎበኘበት ወቅት አቶ ዘሪሁን እንዳስረዱት፤ በወረዳው የተተከሉ ችግኞች የፅድቀት ምጣኔ በመጀመሪያ ዙር በተደረገ ቆጠራ መሰረት በአማካይ 95 በመቶ የደረሰ ሲሆን ለዚህም የተሻለ የዝናብ ስርጭት መኖርና ችግኞችን በባለቤትነት ተረክቦ መንከባከብ መቻሉ በምክንያትነት እንደሚያዝ ተናግረዋል።
ችግኞችን በዚህ ሁኔታ መንከባከብ መቻሉና ከእንስሳትና ከሰው ንክኪ ነፃ እንዲሆኑ በጥበቃ ሰራተኛም ጭምር የታገዘ ስራ መሰራቱ በተለይም ቆላማ አካባቢዎች የተሻለ የደን ሽፋን እንዲያገኙ ከማስቻሉም ባሻገር ከዚህ በፊት ከየአካባቢዎቹ ሸሽተው የነበሩ የዱር እንስሳትን ማየት መቻሉም በጉብኝቱ ወቅት ተገልጿል።
በተለይም በወረዳው ዳለቲ ጨለለቃ ቀበሌ ሮባ ተራራ በአረንጓዴ አሻራ ቀን የተተከለው ችግኝ የቦታውን ገፅታ በመቀየር እና የአካባቢውን ስነምህዳር በማስተካከሉ ከዚህ በፊት ያልነበሩ ጅብ እና ከርከሮ መሰል የዱር እንስሳትን የተመለከትን ሲሆን ቦታው ሙሉ በሙሉ ከሰዎችና እንስሳት ንክኪ ነፃ ሆኖ ችግኞችም በጥሩ የእድገት ደረጃ ላይ መሆናቸውን በምልከታችን አስተውለናል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2012
ድልነሳ ምንውየለት