በኢፌዴሪ መከላከያ ሚኒስትር አቶ ለማ መገርሳ የተመራ ከፍተኛ የወታደራዊ አመራሮች ልዑካን ቡድን ከአሜሪካ ወታደራዊ አመራሮች ጋር ስኬታማ ውይይት ማድረጋቸው ተገለጸ፡፡ ውይይቱ የኢትዮጵያ እና የአሜሪካን የሁለትዮሽ የመከላከያ ትብብር ለማጠናከር ያለመ መሆኑንም በአሜሪካ የኢትዮጵያ አምባሳደር ፍጹም አረጋ በማህበራዊ ገጻቸው አስታውቀዋል።
አሜሪካን በተካሄደው የሁለቱ አገራት ውይይትም የመከላከያ ሚኒስትሩን ጨምሮ የጦር ኃይሎች ጠቅላይ ኢታማጆር ሹም ጀነራል አደም ሙሀመድና ከፍተኛ የጦር መኮንኖች ተሳትፈውበታል፡፡ ኢትዮጵያና አሜሪካ ወታደራዊ ትብብር የጀመሩት ቀደም ባሉ ዓመታት ሲሆን በተለይ ሽብርተኝነትን በመከላከል ረገድ ተጠቃሽ ትብብር አላቸው፡፡
መረጃዎች እንደሚያሳዩት 1903 የኢትዮጵያና አሜሪካ ዲፕሎማሲያዊ ግንኙነት መጀመራቸው ይታወሳል፡፡ እ.ኤአ በ1993 የንግድ ልውውጥ 85 ነጥብ ሦስት ሚሊዮን ዶላር የነበረ ሲሆን በየዓመቱ እያደገ መጥቶ እኤአ በ2017 አሜሪካና ኢትዮጵያ ከአንድ ነጥብ 144 ሚሊዮን ዶላር በላይ የንግድ ልውውጥ አድርገዋል።
በዚህም ኢትዮጵያ ወደ አሜሪካ የተለያዩ ምርቶችን ልካ 292 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር ስታገኝ ከአሜሪካ ደግሞ 852 ነጥብ አራት ሚሊዮን ዶላር የሚያወጡ ዕቃዎችን በተለይ ደግሞ ቦይንግ አውሮፕላኖችን አስገብታለች።
የኢትዮጵያንና የአሜሪካን የሁለትዮሽ የመከላከያ ትብብር በርካታ ዓመታትን ያስቆጠረ ሲሆን ባለፈው ዓመት በአዲስ አበባ ተመሳሳይ ውይይት ማድረጋቸው ይታወሳል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2012
በጋዜጣው ሪፖርተር