አዲስ አበባ:- የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ካቢኔ የቀላል ባቡር ሥራ ከጀመረበት 2008 ዓ.ም እስክ ጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም ያለውን ከአምስት ቢሊዮን ብር በላይ የድጎማ ማካካሻ ክፍያ ለፌዴራል መንግሥት እንደማይከፍል ውሳኔ አሳለፈ።
የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ከንቲባ ጽህፈት ቤት ህዳር 3 ቀን 2012 ዓ.ም ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድ ትራንስፖርት ቢሮ በጻፈው ደብዳቤ ከጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በፊት ለቀላል ባቡር አገልግሎት የቀረበውን የድጎማ ማካካሻ እንደማይከፈል ካቢኔው በዘጠነኛው መደበኛ ስብሰባው ውሳኔ ማሳለፉን አሳውቋል።
ለካቢኔው ውሳኔ መነሻ የሆነው የቀድሞው የገንዘብና ኢኮኖሚ ትብብር ሚኒስቴር የአሁኑ የገንዘብ ሚኒስቴር በታህሳስ 10 ቀን 2010 ለከተማው የመንገድና ትራንስፖርት ቢሮ የድጎማ ማካካሻ ገንዘብ እንዲከፍል መጠየቁ ነው። ሚኒስቴሩ በጻፈው ደብዳቤ የቀላል ባቡር ፕሮጀክት ወጪን ከተሳፋሪዎች የሚገኘው ገቢ ስለማይሸፍን የድጎማ ማካካሻ በከተማ አስተዳደር በኩል እንዲሸፈን ጠይቋል።
ከሚኒስቴሩ የመጣውን ጥያቄ ተከትሎ ቢሮው፤ የኪሳራ ማካካሻ ድጋፍ የሚደረግበትን ሁኔታ አጥንቶ እንዲያቀርብ ተጠይቋል። ቢሮውም የቀላል ባቡሩ አገልግሎት መሰጠት ከጀመረበት 2008 እስከ 2010 ዓ.ም አጋማሽ ከድርጅቱ መረጃ በመውሰድ ጥናት አድርጓል።
በጥናቱም በሦስት ዓመታት በድምሩ 265 ሚሊየን 524 ሺህ 261 ብር ከተሳፋሪዎች ገቢ ተሰብስቧል። በአንፃሩ 5 ቢሊዮን 338 ሚሊየን 234 ሺህ 688 ብር ወጪ የተደረገ ሲሆን 5 ቢሊዮን 72 ሚሊየን 710 ሺህ 427 ኪሳራ መድረሱንም ጥናቱ ያመላክታል።
ቢሮው ለካቢኔው በላከው ደብዳቤ ባቀረበው የውሳኔ ሐሳብ በፌዴራል መንግሥት ከተጠየቀው የሦስት ዓመታት 5 ቢሊዮን 72 ሚሊየን 710 ሚሊየን 427 ብር የማካካሻ ድጎማ ውስጥ 2 ቢሊዮን 821 ሚሊየን 207 ሺህ 338 እንዲደጎም የውሳኔ ሐሳብ አቅርቦ ነበረ።
ቀሪው ገንዘብ ግን የግንባታ ወጪ ወለድ ምጣኔ በመሆኑ ይህም በአገልግሎት ሰጪው ድርጅት ምክንያት የደረሰ ኪሳራ አይደለም። ሚኒስቴሩ በጻፈው ደብዳቤ ይህ ወጪ በፌዴራል መንግሥት የሚሸፈን መሆኑ በመገለፁ የከተማ አስተዳደሩ ቀሪውን ኪሰራ መክፈል እንደሌለበትም በደብዳቤው አብራርቶ ነበር።
የከተማ አስተዳደሩ ግን ከጥር 18 ቀን 2011 ዓ.ም በፊት ያለውን ውድቅ ያደረገ ሲሆን፣ ከዚህ በኋላ ለሚደረገው የድጎማ ማካካሻ ግን፤ የመንገድ ትራንስፖርት ቢሮ ጥናት አድርጎ እንዲያቀርብለትም ወስኗል።
የኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽን ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ስንታየሁ ወልደሚካኤል “የገንዘብና ኢኮኖሚ ሚኒስቴር ለቀላል ባቡር አገልግሎት አንድነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር በየዓመቱ የድጎማ ማካካሻ እንዲያደርጉ ለአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር ደብዳቤ ጽፏል። ክፍያውን አንከፍልም ካሉም የማይከፍሉበትን ምክንያት መልስ መስጠት አለባቸው። እኛ ግን ከመንግሥት ጋር እየተነጋገርን ነው። ያም ሆኖ ግን ችግሩ በጣም አሳሰቢ አይደለም፤ በቀጣይ በመነጋገር የሚፈታ ነው” ብለዋል።
“የፕሮጀክቱ ባለቤት የከተማ አስተዳደሩ ነው። ግንባታው እንዲካሄድም የተወሰነው በከተማው ነው። ኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክቱን የቴክኒክና የአስተዳደር ሥራ ነው ያከናወነው። አገልግሎት እየሰጠ ያለው ለከተማው ነው” ሲሉም ገልፀዋል።
በኢትዮጵያ ምድር ባቡር ኮርፖሬሽኑ ምክትል ዋና ሥራ አስፈፃሚ አቶ የኋላሸት ጀመረ ቀደም ሲል ከአዲስ ዘመን ጋዜጣ ጋር ባደረጉት ቃለ ምልልስ ፕሮጀክቱ ባለቤት የከተማ አስተዳደሩ ሲሆን ግንባታው እንዲካሄድም የተወሰነው በከተማው ነው። ኮርፖሬሽኑ የፕሮጀክቱን የቴክኒክና አስተዳደር ሥራ ሲሆን አገልግሎት እየሰጠ ያለውም ለከተማው አስተዳደሩ መሆኑም ገልፀዋል።
የብዙሐን ትራንስፖርት አገልግሎት የሚሠራው በትርፍ ሳይሆን በድጎማ ነው አቶ የኋላሸት የአዲስ አበባ ቀላል ባቡር አገልግሎት እየሰጠ ያለው በድጎማ ነው። እስካሁን የደጎመው የበባቡር ኮርፖሬሽን ነው።
ኮርፖሬሽኑ የፌዴራል መንግሥት እንደመሆኑ የአንድን ከተማ ትራንስፖርት መደጎም ትክክል አይደለም። ምክንያቱም ድጎማው ከሁሉም የኢትዮጵያ ህዝብ የተሰበሰበን ገንዘብ ለአንድ ከተማ አስተዳደር መደጎም ተገቢ አይደለም። በመሆኑም አስተዳደሩ በየዓመቱ አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር እንዲደጉም ለሚመለከተው አቅርበናል ብለዋል።
በምክትል ከንቲባ ማዕረግ የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር መንገድና ትራንስፖርት ቢሮ ሃላፊ ዶክተር ኢንጂነር ሰለሞን ኪዳኔ እንደገለፁት አስተዳደሩ ከዲዛይን እስከ አገልግሎት ዋጋ ትመና አለመሳተፉን ጠቁመው በዚህም የከተማ አስተዳደሩ ቅሬታ ነበረው ብለዋል፡፡
“ቀደም ሲል ቢያንስ ድጎማ ለማድረግ የዋጋ ትመና ሲወጣ ያዋጣል አያዋጣም የሚለው ውይይት ማድረግ ነበረብን፤ የኮርፖሬሽኑ ኪሳራ ትክክል ነው ወይስ አይደለም የሚለውንም ለማጥራትም የተደረገ ነገር የለም። በአጠቃላይ ከኮርፖሬሽኑ ጋር አስተዳደሩ ምንም አይነት ስምምነት የለንም። ዝም ተብሎ ተመጥቶ ነው አዲስ አበባ ከፋይ የተባለው” ሲሉም አብሮ የመሥራት ሁኔታ እንዳልነበር ተናግረዋል፡፡
“የአዲስ አበባ ከተማ አስተዳደር በጀት የሚተዳደረው በከተማው ምክር ቤት በሚያወጣው አዋጅ መሰረት ነው። ኪሳራ ለማካካስ የዋጋ ትመና ሲወጣ ኪሳራውን ለመክፈል አቅም እንዳለው መጠየቅ ነበረበት። አስተዳደሩ መደጎም ካልቻለ በአዋጩ ዋጋ ማስከፍል ነው ያለበት። ክፈሉም ከተባለ መክፈል ያለብን ኮርፖሬሽኑ ለገጠመው ኪሰራ ሳይሆን እያንዳንዱ ተሳፋሪ ሂሳብ ተሰልቶ ነው። ይህን ባላወቅንበት ሁኔታ መደጎም አንችልም።
ምክንያቱም ኪሳራው በአሠራር፣ ከሥራው በላይ ሰው በመቅጠር፣ በአሠራር ክፍተትና በመሳሰሉት ሊመጣ ይችላል። የከተማ አስተዳደሩ ይህን መደጎም የለበትም። ከደጎመም ስህተት ነው። ኪሳራ ስላለብን በዓመት አንድ ነጥብ አምስት ቢሊዮን ብር አምጡ ማለትም ተገቢ አይደለም” ብለዋል ዶክተር ኢንጂነር ኪዳኔ።
ፕሮጀክቱ የፌዴራል መንግሥት ያመጣው ኢንቨስትመንት ነው። እንዲያም ሆኖ ለከተማው ህዝብ አገልግሎት እስከሰጠ ድረስ የከተማ አስተዳደሩ መደጎም እንዳለበት ያምናል። አሁን ግን በርካታ ፕሮጀክቶች ስላሉን አቅም ስለሚያንሰን ከጠቅላይ ሚኒስትሩ ጋር በመነጋገር የፌዴራል መንግሥት እንዲሸፍንልን በካቢኔ ወስነናል። በቅርብ ጊዜ ባይሆንም በቀጣይ ከፌዴራል መንግሥት ጋር በመነጋገር የተሳፋሪዎችን ኪሳራ ግን ሊደጉሙ እንደሚችሉ ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2012
አጎናፍር ገዛኸኝ