አዲስ አበባ፡- የተማሪዎች ግንኙነት ማጠናከርና ሰላም ማስፈን የሚያስችል አገር አቀፍ የሰላም ጥሪና የምክክር ጉባዔ ተካሄደ።
የሃይማኖት አባቶች፣ የሀገር ሽማግሌዎች፣ አባ ገዳዎችና ታዋቂ ግለሰቦች በተገኙበት ትናንት በአዲስ አበባ በተካሄደ ሀገር አቀፍ የሰላም ጥሪና የምክክር ጉባዔ ላይ በተላለፈው መልዕክት፤ ተማሪዎች ከሁከትና ከብጥብጥ ራሳቸውን በማራቅ ለሰላም መስፈን አስተዋጽኦ እንዲያደርጉ ጥሪ ቀርቧል።
በጉባዔው ላይ ንግግር ያደረጉት የኢትዮጵያ ኦርቶዶክስ ተዋህዶ ቤተክርስቲያን የውጭ ግንኙነት ኃላፊ ብፁዕ አቡነ አረጋዊ (ዶክተር) ተማሪዎች አላስፈላጊ ከሆነ ግጭት በመራቅ ለትምህርታቸው ትኩረት እንዲሰጡ ጥሪ አቅርበዋል።
የከፍተኛ ትምህርት ተቋማት የአብሮነት መስተጋብር ማጠናከሪያ መድረክ ናቸው ያሉት ሃላፊው፤ አሁን እየታየ ያለው የእርስ በርስ ግጭት የሚወገዝ ተግባር መሆኑን ገልፀዋል። “ከብጥብጥ ይልቅ ተርቦ ያስተማራችሁን ቤተሰብና በድህነት ያስተማራችሁን ወገን አስቡ!።” በማለት ተማሪዎች ቤተሰባዊና ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን በአግባቡ እንዲወጡም ተማፅኖዓዊ ጥሪ አስተላልፈዋል።
የኢትዮጵያ እስልምና ጉዳዮች ከፍተኛ ምክር ቤት ምክትል ፕሬዚዳንት ሼህ ጄላን ከድር (ዶክተር) የከፍተኛ ትምህርት ተማሪዎች ከሁከትና ግርግር ራሳቸውን በማራቅ ለትምህርታቸው ቅድሚያ ሰጥተው ሀገራዊ ሃላፊነታቸውን መወጣት እንደሚጠበቅባቸው ገልፀዋል።
ቤተሰብ ልጆቹን በመምከር የሰላም ማስከበር ሚናውን ሊወጣ እንደሚገባ የተናገሩት ሼህ ጄላን፤ የሃይማኖት አባቶች ለተማሪዎችና ለህብረተሰቡ ሰላምን በመስበክና አንድነትን የሚያጠናክሩ ትምህርቶችን በመስጠት ሃላፊነታቸውን እንዲወጡም መልዕክት አስተላልፈዋል።
በሰላም ጥሪና የምክክር ጉባዔው ላይ የተገኙት አባገዳ አልዬ ሙሐመድ ተማሪዎች በዩኒቨርሲቲ ውስጥ በሚኖራቸው ቆይታ የመማር ማስተማር ሂደቱን ከሚያውኩ ተግባራት እንዲታቀቡና ከትምህርት ገበታቸው የራቁ ተማሪዎችም ወደ ትምህርት እንዲመለሱ ጥሪ አስተላልፈዋል። በመማር ማስተማር ሂደት ላይ ችግር የሚፈጥሩ አካላት ከድርጊታቸው መቆጠብ ይገባቸዋል ያሉት አባ ገዳ አልዬ ተማሪዎችም ለብጥብጥ ከሚጋብዙዋቸው አካላት እራሳቸውን እንዲጠብቁ ምክር ለግሰዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2012
ተገኝ ብሩ