ወጣት ብርቱካን ገበየሁ በሰው አገር መሰቃየት አንገፍግፏት የእናቷም ናፍቆት ስለበረታባት ወደ አገሯ መመለስን አሰበች። እንዳሰበችም አልቀረችም ጓዟን ጠቅልላ አገሯ በሰላም ገባች። ቤተሰቦቿን ለማየት እግረ መንገዷንም ናፍቆቷን ለመወጣት ወደ ቀዬዋ እየሄደች ነው። አሽከርካሪውም ቶሎ ለመድረስ በማሰብ በከፍተኛ ፍጥነት እያሽከረከረ ጉዞውን ቀጥሏል። በድንገት በጉዟቸው ላይ እያሉ አንድ ያልታሰበ ነገር ተከሰተ። በመንገድ ላይ አንድ በሬ መንገዱን ቀይሮ ወደ ተሽከርካሪው መስመር እየሮጠ ገባ።
አሽከርካሪውም ከፍተኛ ፍጥነት ላይ ስለነበር ፍሬን መያዝና መኪናውን መቆጣጠር አልቻለም። በሬውን ደርቤ አልፋለሁ ሲል የተሽከርካሪውን መንገድ ስቶ በመውጣት ተገልብጦ ወደቀ።
የወደቀውም ይህች ወጣት ባለችበት በኩል ነበር። ወድቆ እየተንሸራተተ ሲሄድ የራስ ቅሏና የተቀረው የሰውነት ክፍሏ ላይ ከፍተኛ ጉዳት አደረሰባት። ጤነኛ የነበረ አካል በአንዴ እንዳይሆኑ ሆነ። ‹‹ሩቅ አሳቢ ቅርብ አዳሪ›› እንደሚባለው ወጣትዋ በአሽከርካሪው የጥንቃቄ ጉድለት የናፈቋትን እናቷን ሳታይ፣ ህልሟንም እውን ሳታደርግ ለህክምና እርዳታ በአቤት ሆስፒታል ለመተኛት ተገደደች።
በጫንጮ ከተማ ነዋሪ የሆነው ሌላኛው የትራፊክ አደጋ ተጎጂ ወጣት ታምራት ዓለሙ የእርሱንና የሁለት ታናናሽ ወንድሞቹን ጉሮሮ ለመድፈን ማልዶ በመነሳት ይተዳደርበት የነበረውን የእንጨት ሥራ ለመጀመር ፈጣሪውን ሰላም አውለኝ ብሎ ጓዙን ጠቅልሎ ከቤት ይወጣል።
ሰላም መዋል የሚቻለው በአንድ ወገን ፍላጎት ብቻ ባለመሆኑ ከቤቱ ከወጣ ከሦስት ደቂቃዎች በኋላ መንገዱን ሲሻገር ከፊት ለፊቱ የነበረው ተሽከርካሪ እንደምንም ብሎ ፍሬኑን ያዘለት። ከድንጋጤ ያልነቃው ወጣት ታምራትም ነፍሱ በመትረፏ አሁንም ምስጋናውን እያቀረበ ሊሻገር ሲል ሌላ አይሱዚ የቆመውን መኪና ደርቦ በመምጣት ከመንገዱ ዳር በሚገኝ ቱቦ ውስጥ ከትቶት አመለጠ። ተሽከርካሪውን ለመያዝ ለጊዜው ሙከራ ቢደረግም ሳይቻል ቀርቷል። ወጣት ታምራትም አሁን ላይ በመንግሥት ዕርዳታ በአቤት ሆስፒታል ህክምና እየተደረገለት ይገኛል።
በ2108 የዓለም ጤና ድርጅት ባወጣው ሪፖርት መሠረት በዓለማችን ላይ 1 ነጥብ 3 ሚሊየን ሰዎች በመንገድ ላይ ሆነው አሊያም በትራንስፖርት ከቦታ ወደ ቦታ በሚንቀሳቀሱበት ወቅት ባላሰቡትና ባልጠበቁት ሁኔታ በመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት ህይወታቸውን ያጣሉ። 50 ሚሊየን ሰዎች ላይ ከባድና ቀላል የአካል ጉዳት ደርሶባቸዋል። በአገራችን ባለፈው ዓመት 5 ሺ 100 ዜጎች ህይወታቸው አልፏል። እንዲሁም 600 ቢሊዮን ዶላር የሚገመት ንብረት ወድሟል።
በመንገድ ትራፊክ አደጋ ምክንያት በሰዎች ላይ እየደረሰ ያለው የሞትና የአካል ጉዳት ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ በሥነ ልቦና እንዲሁም በኢኮኖሚ ላይ ጫና በመፍጠር የዓለም ሥጋት እየሆነ መምጣቱን ተከትሎ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት በዓመት አንድ ቀን ‹‹የዓለም የመንገድ ትራፊክ አደጋ ተጎጂዎች ማስታወሻ ቀን›› በማለት በዓለም አቀፍ ደረጃ እንዲከበር ወስኗል። በዚህም መሠረት ዘንድሮ በዓለም ለ14ኛ ጊዜ በአገራችን ደግሞ ለ12ኛ ጊዜ ‹‹ህይወት ተሽከርካሪ አካል አይደለም መለዋወጫ የለውም›› በሚል መሪ ቃል የጤና ጥበቃ ሚኒስቴር፣ መንገድና ትራንስፖርት ባለስልጣን ከአቤት ሆስፒታል ጋር በመተባበር አክብረዋል።
የአቤት ሆስፒታል ዋና ሥራ አስኪያጅ ዶክተር ገሊላ መንግሥቱ እንደሚናገሩት፤ በየጊዜው በርካታ ኢትዮጵያውያን በትራፊክ አደጋ ለአካል ጉዳተኝነት እየተዳረጉ ነው። ህይወታቸውን የሚነጠቁም በርካቶች ናቸው።
የቅዱስ ጳውሎስ አካል የሆነው ሆስፒታልም አደጋውን ለመከላከል ተጎጂዎችን ከማከም ባሻገር ሌሎች የግንዛቤ ማስጨበጫ መድረኮችን በማመቻቸት ህብረተሰቡን አሳታፊ የሆነ አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። አደጋውን በዘላቂነት በተሻለ ለመቆጣጠር ከእግረኛው ጀምሮ ሁሉም ዜጋ ኃላፊነት ሊሰማው ይገባል።
የኢትዮጵያ መንገድ ትራፊክ ደኅንነት ዘርፍ ምክትል ዳይሬክተር አቶ ምትኩ አማረ በበኩላቸው፤ በዓለም ላይ አደጋው ከሚደርስባቸው ዜጎች 90 በመቶ የሚሆኑት አፍሪካውያን መሆናቸውን በመጠቆም ከዚህም ውስጥ ኢትዮጵያውያን በአደጋው የመጠቃታቸው ሁኔታ አሳሳቢ ደረጃ ላይ መሆኑን ጠቁመዋል።
የመንገድ ደኅንነትን ጨምሮ የእግረኞች እንቅስቃሴና የአሽከርካሪዎች ቸልተኝነት አደጋውን ማባባሱን አስረድተው፤ በቀጣይ ችግሩን ለመቀነስ የመንገድ ደኅንነት ጉዳይ የጤና ኢንስፔክሽን ዘርፍ ውስጥ ተካትቶ እንደሚሠራበት ገልፀዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 26/2012
አዲሱ ገረመው