
ካለፉት አስርት አመታት ወዲህ በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በተፈጠሩ ችግሮች ከ20 ሚሊዮን በላይ ሰዎች ከመኖሪያ ቀዬአያቸው ተፈናቅለዋል። በሚሊዮኖች የሚቆጠሩ የድሃ ሀገራት ዜጎች የአየር ንብረት ቀውስን ሲሸሹ ከፍተኛ ዋጋ ከፍለዋል፡፡ ዛሬም እየከፈሉ ይገኛሉ፡፡
በዓለም አቀፍ ደረጃ ድህነትንና ኢ ፍትሃዊነትን ለመቅረፍ የሚሰራው ኦክስፋም ባለፈው ሰኞ ይፋ ያደረገው ጥናት እንዳመለከተው ከባድ አውሎ ንፋሶች፣ ጎርፍና የዱር እሳት አደጋ ድግግሞሽ ከሚታሰበው በላይ እየሆነ መጥቷል፡፡ ሆኖም አደጋዎቹ በሰዎች ላይ ከፍተኛ ጉዳት ከማስከተላቸው በፊት አስቀድሞ የነፍስ አድን ስራ በመሰራቱ ብዙዎቹ የችግሩን ስፋት መረዳት አልቻሉም፡፡
የኦክስፋም የአየር ንብረት ፖሊሲ መሪ ቲም ጎሬ ለሮይተርስ እንደገለፁት ኩባ፣ ዶሚኒካና ቱቫሉ የተባሉ የደሴት አገሮች በየአመቱ በአማካኝ ወደ 5% የሚሆኑት ሕዝቦቻቸው በአየር ንብረት ጫና ምክንያት አብዛኛውን ጊዜያቸውን ከቤታቸው ውጪ ለማሳለፍ እየተገደዱ መሆናቸውን አስረድተዋል፡፡ “ይህ ለረጅም ጊዜ ሲያስጠነቅቀን የነበረው የዓለም ሙቀት መጨመር ውጤት ነው። አሁን በዐይናችን ፊት ሲጫወት እያየን ነው”ሲሉ ገልፀዋል፡፡
የተራድኦ ድርጅቱ በመንግስትና በዓለም አቀፍ ኤጀንሲዎች መረጃዎች እንዲሁም በመገናኛ ብዙሃን ዘገባዎች ላይ በመመርኮዝ እ.ኤ.አ ከ2008 እስከ 2018 በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት በየሀገሩ የተፈናቀሉ ሰዎችን መረጃ አሰባስቧል፡፡ በመረጃዎቹ መሰረት ከግጭቶች ይልቅ የአየር ንብረት ለውጡ ውጤት በሆኑት በረሃማነት፣ በጎርፍና በእሳት አደጋዎች የተፈናቀሉ ሰዎች ቁጥር ከፍ ያለ ነው፡፡ የአየር ንብረት ለውጥ ያፈናቀላቸው በግጭት ከተፈናቀሉት በሶስት እጥፍ ይበልጣሉ፡፡
በጦርነት ውስጥ የቆዩት እንደ ሶማሊያና የመን ያሉ አንዳንድ ሀገራት ከግጭቶች ጎን ለጎን የአየር ንብረት ለውጥ ሰለባ ሆነዋል የሚሉት ቲም ጎሬ፤ አንዳንዴም በተመሳሳይ ዓመት ሁለቱንም ለማስተናገድ መገደዳቸውን ያነሳሉ፡፡ ሁለቱ አደጋዎች በተመሳሳይ ወቅት ሲከሰቱ ደግሞ ከአንዱ ቀውስ ለማገገም ሲታገሉ ሌላኛው ቀውስ እያጋጠማቸው በእንቅርት ላይ ጆሮ ደግፍ ሲሆንባቸው እንደነበር አንስተዋል፡፡ አንዳንዶች በድርቅና በጎርፍ ለተጎዱ አካባቢዎች በተመሳሳይ ጊዜ የእርዳታ ጥሪ አቅርበዋል ብለዋል፡፡
“በአሁኑ ወቅት በአለም ላይ እየተከሰቱ ያሉት ክስተቶች ያልተለመዱ ናቸው” የሚሉት የቡድኑ መሪ እየሆኑ ያሉት ነገሮች የአየር ንብረት የሚያስከትለው መዘዝ ምን እንደሚመስል ፍንትው አድርገው የሚያሳዩ ናቸው ይላሉ፡፡ የኦክስፋም ሪፖርት እንደሚያመላክተው፤ ካላቸው የሕዝብ ቁጥር አንጻር ከፍተኛ መፈናቀል ከሚከሰትባቸው 10 የዓለም ሀገራት ሰባቱ በፓስፊክና በካሪቢያን ደሴቶች ውስጥ የሚገኙ ድሃ ሀገራት ናቸው፡፡
ነገር ግን ካለፉት አስርት ዓመታት ወዲህ በአየር ንብረት ቀውስ አደጋዎች ከቤት ንብረታቸው ከተፈናቀሉት ከአጠቃላይ ሰዎች መካከል 80 በመቶው የሚሆኑት ከፊሊፒንስ እስከ ስሪላንካ ባሉት ሀገሮች በተከሰተው ከባድ አውሎ ነፋስ ወይም በጎርፍ በተጥለቀለቁ አካባቢዎች ውስጥ የሚኖሩ ናቸው፡፡
እንደ ኦክስፋም ሪፖርት ባለፈው ግንቦት ወር የተከሰተው ፋኒ የሚል ስያሜ የተሰጠው አውሎ ነፋስ በባንግላዴሽና በህንድ ብቻ 3 ነጥብ 5 ሚሊዮን ሰዎች እንዲፈናቀሉ አድርጓል፡፡ ከነዚህ ተፈናቃዮች ውስጥ አብዛኞቹ አውሎ ነፋሱ ከመከሰቱ ቀደም ብለው ህይወታቸውን ለማትረፍ አካባቢያቸውን የለቀቁ ናቸው፡፡ በአጠቃላይ፣ ባለፉት አስርት ዓመታት እጅግ ከባድ እንደሆኑ የሚታሰቡ የአየር ንብረት አደጋዎች ቁጥር በአምስት እጥፍ አድጓል፡፡
ባለፈው ሰኞ የህጻናት አድን ድርጅት ያወጣው ሌላኛው ትንተና እንደሚያሳየው በዚህ ዓመት በምስራቅና በደቡብ አፍሪካ በጣም ሞቃታማ የአየር ሁኔታ፣ ዚምባዌንና ማላዊን የመታው ሁለት አውሎ ነፋሶችን ጨምሮ እስከ ሰኔ ወር ድረስ ብዙ ሰዎችን ከቤታቸው አፈናቅሏል፡፡
እ.ኤ.አ. በ2018 ኦክስፋም ባካሄደው ግመታ መሰረት በዓመቱ በከባድ የአየር ንብረት አደጋዎች ምክንያት ከተፈናቀሉት ዜጎች ውስጥ ከ10 እስከ 20 በመቶ የሚሆኑት እስከ ዓመቱ መጨረሻ ድረስ ወደ ቤታቸው አልተመለሱም፡፡
በአየር ንብረት አደጋዎች ምክንያት በርካታ ዜጎች ከቀኤያቸው በተፈናቀሉ ቁጥር እነዚህን ዜጎች መልሶ ለማቋቋም የሚያስፈልገው ገንዘብና የሚያስከትለው ማህበራዊ ቀውስ እየጨመረ ይሄዳል የሚለው ኦክስፋም፤ ድሃ ሀገራት ችግሩን ለመቋቋም የሚያደርጉትን ጥረት እጅግ አዳጋች እንደሚያደርገው አትቷል፡፡
የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ውይይቶች የአካባቢና የልማት ቡድኖች በአየር ንብረት ለውጥ ምክንያት ለችግር እየተጋለጡ ያሉ ሀገራትን ለመደገፍ የገንዘብ ድጋፍ ሊሰባሰብ እንደሚገባ በማሳሰብ ጫና እየፈጠሩ ይገኛሉ፡፡ እ.ኤ.አ በ2013 በተደረገው የተባበሩት መንግስታት ድርጅት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ ላይ የዋርሶ ዓለም አቀፍ ኪሳራና ጉዳት መቋቋሚያ ዘዴ የተቀየሰ ሲሆን ዋናው ዓላማው ለአየር ንብረት ለውጥ ይህ ነው የሚባል አስተዋጽኦ ሳያበረክቱ የአየር ንብረት ለውጥ ዳፋ ሰለባ የሆኑትን ሀገራት መርዳትን መሰረት ያደረገ ነው፡፡
ሆኖም ተቺዎች እንደሚሉት ከሆነ የአየር ንብረት ለውጥ አደጋዎች ተጠቂ የሆኑ ድሃ ሀገራት የኢንሹራንስ ፖሊሲዎችን እንዲጠቀሙ ድጋፍ ከማድረግ በዘለለ የተቀየሰው ዘዴ ተጎጂ ሀገራትን በሚፈለገው ልክ ለመርዳት ተጨባጭ አስተዋጽኦ አላበረከተም፡፡ የኦክስፋም ቡድን መሪ ጉሬ እንደገለጹት ኢንሹራንስ ብቻውን የተጎጂ ሀገራትን ችግር መፍታት አይችልም፡፡
ሰሞኑን በስፔን ማድሪድ እየተካሄደ ባለው 25ኛው የተባበሩት መንግስታት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤ አጀንዳዎች አንዱ ያደጉት ሀገራት ከዚህ ቀደም በነበሩት የአየር ንብረት ለውጥ ጉባኤዎች በማደግ ላይ ላሉ ሀገራት የአየር ንብረት ለውጥን መቋቋም እንዲችሉ ድጋፍ ለማድረግ የገቡትን ቃል እንዲተገብሩ ጫና ማሳደር አንዱ ይሆናል ተብሎ ይጠበቃል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2012
መላኩ ኤሮሴ