አዲስ አበባ፡- ዘንድሮ ለ14ኛ ግዜ የሚከበረው የብሄሮች፣ ብሄረሰቦችና ህዝቦች ቀን ብዝሀነትና አንድነት ተጣጥመውበት እንደሚከበር የፌዴሬሽን ምክር ቤት አስታወቀ።
የፌዴሬሽን ምክር ቤት የህዝብ ግንኙነትና ኮሙኒኬሽን ዳይሬክተር አቶ ገብሩ ገብረስላሴ ለአዲስ ዘመን እንደገለጹት፣ ‹‹ ህገ መንግስታዊ ቃል ኪዳናችን ለዘላቂ ሰላም›› በሚል መልዕክት በኦሮሚያ ክልላዊ መንግስት አዘጋጅነት የሚከበረው ይህ በዓል የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦችና ህዝቦች የጋራ ቃል ኪዳን ያሠሩበት መታሰቢያ ነው። ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን ለማክበር ቃልኪዳናቸውን ያድሳሉ። ብዝሀነትና አንድነትም ይጣጣሙበታል።
ብሄር ብሄረሰቦች ከሁሉ አስቀድመው ሰላማቸውን ማረጋገጥ እንደሚገባቸው የተናገሩት አቶ ገብሩ፣ አሁን በሀገሪቱ የሚታየውን ችግር ለመፍታትም ተቀራርቦ የመነጋገርና አብሮ የመኖር ቃላቸውን የሚያድሱበት እንደሆነ ገልጸዋል። ህዳር 29 ከሚከበረው የብሄር ብሄረሰቦች ቀን አስቀድሞ የህዝብ ለህዝብ ግንኙነቶችን የሚያጠናክሩ የተለያዩ መድረኮች ሲካሄዱ መቆየታቸውን ተናግረዋል። በዚህም በተጎራባች ዞኖች፣ ወረዳዎችና ቀበሌዎች ውይይት ሲካሄድ እንደነበር አስታውሰዋል።
የዘንድሮው በዓል አከባበር በሀገራችን ሰላም ላይ የሚያጠነጥን ሆኖ ችግሮቻችንን በውይይት የመፍታት አቅማችንን የምናጎለብትበት እንደሆነ እና የህገ መንግስቱን መርሆዎችና እሴቶችን አጉልተን የምንመለከትበት እንደሆነም ጠቅሰዋል። መሪ መልዕክቱም ይህንኑ የሚያንጸባርቅ መሆኑን አመልክተዋል።
በዓሉን ለየት የሚያድርገው ሌላው ጉዳይ ህገ መንግስቱ የጸደቀበት 25ኛ ዓመት የብር እዮቤልዩ የሚከበርበት ዕለት መሆኑንም ዳይሬክተሩ ጠቅሰው፣ እስከዛሬ የነበሩት ችግሮቻችን፣ ስኬቶቻችን ፣ ህገ መንግስታዊ ሥርዓቱን እየተገዳደሩ ያሉ ነገሮች ምንድናቸው? በአጠቃላይ የ25 ዓመታት ጉዟችን ምን ይመስላል? በሚሉት ላይ ውይይት ሲደረግ እንደነበርም አስታውሰዋል።
ኢትዮጵያ የተለያዩ ብዝሃነቶች የሚታዩባት ሀገር እንደመሆኗ የህገ መንግስቱ የመጨረሻ ግብም በብዝሀነት ላይ የተመሰረተ አንድነትን በማጎልበት ጠንካራ ሀገር መገንባት እንደሆነ አቶ ገብሩ ገልጸዋል። ብዝሃነቱ የተለያዩ ቋንቋዎች፣ ባህሎች፣ ሃይማኖቶች የሚገለጹበት እንደመሆኑ በዓሉ የኢትዮጵያ ብሄር ብሄረሰቦች ከጫፍ እስከጫፍ ተገናኝተው አንዱ ስለሌላው የሚያውቅበት መድረክ መሆኑንም ተናግረዋል።
በዓሉ የኢትዮጵያን አንድነት የሚሸረሽር ነው የሚል አመለካከት ያላቸው አካላት እንዳሉም አቶ ገብሩ ጠቅሰው፣ የአስራ አንድ ዓመት የብሄር ብሄረሰቦች ቀን በዓል አከባበር ጉዞ ምን እንደሚመሥል በተደረገ ጥናት የተገኘው ውጤት 85 በመቶ በዓሉ ተጠናክሮ መቀጠል እንዳለበት ያመላከተና ህብረ ብሄራዊ አንድነትን ለመመስረት ትልቅ አቅም ነው ሲሉም ገልጸዋል። በመሆኑም በብዝሀነት ላይ የተመሰረተ አንድነት መጪዋን ኢትዮጵያ ለመገንባት ትልቅ አስተዋጽኦ እንዳለው አስረድተዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 25/2012
ኢያሱ መሰለ