እኤአ ህዳር 17 ቀን 2010 በቱኒዚያ አንድ አስገራሚ ድርጊት ተፈጸመ። ይህም ቱኒዚያዊው የ27 ዓመት ወጣት ራሱን በእሳት አቃጥሎ የገደለበት ታሪክ ነው። በጎዳና ላይ ንግድ ህይወቱን ይመራ የነበረው ወጣቱ ሞሀመድ ቦአዚዝ፣ ራሱን በአሰቃቂ ሁኔታ በመግደሉ ምክንያት በቱኒዚያ ከባድ ህዝባዊ አብዮት መቀጣጠሉ ይታወሳል።
በፕሬዚዳንት ቤን አሊ አምባገነናዊ አገዛዝ ለዘመናት ሲቀበለው የኖረውን አፈናና የኢኮኖሚ ድቀት ለሌላ ተጨማሪ ዘመን ሊሸከም ፈቃደኛ ያልሆነው ወጣቱ፣ እርምጃውን የወሰደው ከዚህ አበሳና አፈና እስከወዲያኛው ለመገላገል፣ እንዲሁም ለአገዛዙ ያለውን ከፍተኛ ጥላቻ ለማሳየት ሲል ነበር።
የወጣቱ ድርጊት የብዙዎችን ቀልብ በመሳብ ለቱኒዚያውያን የለውጥ ማስጀመሪያ ደውል ሆነ። ቱኒዚያውያንን ከሁለት አስር ዓመታት በላይ ኢ ዴሞክራሲያዊ ሆኖ የቆየው አስተዳደር ወደ ዴሞክራሲያዊ ምዕራፍ እንዲሸጋገር አንደረደራቸው። የወጣቱ እርምጃ ታሪክና ጊዜ በአንድ ላይ በመገጣጠማቸው ከፍተኛ የለውጥ አንቀሳቃሽ ኃይል ለመሆን በቃ፡፡
የወጣቱ ድርጊት በቱኒዚያ ህዝብ ልብ ውስጥ ከፍተኛ ቁጭት ፈጠረ። ለረጅም ዘመናት በከፍተኛ ጭቆናና አሰቃቂ የኢኮኖሚ ድቀት ውስጥ ሲማቅቁ የነበሩት ቱኒዚያውያን፣ ሞሀመድ ቦአዚዝ በአሰቃቂ ሁኔታ ራሱን በራሱ እንዲገድል የተገደደባቸውን ዋና ዋና ምክንያቶች አነሷቸው። ሁሉም እንደ አንድ፣ አንዱም እንደ ሁሉም በመነሳት በአምባገነኑና በጨቋኙ መሪያቸው ቤን አሊ አገዛዝ ላይ ህዝባዊ ተቋውሞ አሰሙ። ወጣቱ በአደባባይ ራሱን በእሳት በማቃጠል የጀመረውን አብዮት ህዝቡ ተቀብሎ በማቀጣጠል በአመጽና በተቃውሞ የቤን አሊን አገዛዝ ተገረሰሰ።
ሲኤን ኤን እንደዘገበው በቱኒዚያ ይህ ከሆነ እነሆ አሁን ሰባት ዓመታት ተቆጥረዋል። ወጣቱ በአደባባይ የፈጸመው የቱኒዚያ አብዮት መነሻ ታሪክ ዓመታትን ቆጥሮ ሰሞኑን ራሱን ደግሟል። በ2010 ወጣቱ ሞሀመድ ቦአዚዝ ራሱን በማቃጠል በመንግሥት ላይ ያሳየውን ተቃውሞ አብዱራዛቅ ዞርጉኢ በተመሳሳይ ራሱን አቃጥሎ በመግደል ሰሞኑን ደግሞታል።
ጋዜጠኛው አብዱራዛቅ ድርጊቱን ከመፈጸሙ አስቀድሞ በቪዲዮ በካሳኢሪኒ የሚኖሩ ወጣቶች ቆመው ለመሄድ የሚያስችል ገቢ የሌላቸው መሆኑን በመጥቀስ፤ የእኔንም ሆነ የእነሱን አሰቃቂ ኑሮ ከማይ እስከወዲያኛው ለመገላገል ወስኛለሁ የሚል መልዕክት አስተላልፏል፡፡
ጋዜጠኛው በቱኒዚያ ከስምንት ዓመት በፊት በሞሀመድ ቦአዚዝ ላይ የተቀጣጠለው ህዝባዊ አብዮት ውጤታማ አለመሆኑንም በመግለጽ፤ ህዝባዊ ተቃውሞው ዳግም እንዲፋፋም ራሴን አሳልፌ ሰጥቻለሁ ሲል መግለጹን ዘገባው ጠቁሟል ።
የአብዱራዛቅን ተግባር ተከትሎ የቱኒዚያ ጎዳናዎች በህዝባዊ ተቃውሞና አመጽ መጨናነቃቸውን በዘገባው ተመልክቷል። ፖሊስ በካሳኢሪኒ ጎዳናዎች ለተቃውሞ የወጣውን ሕዝብ ለመበተን አስለቃሽ ጭስ መጠቀሙን አስታውሷል። በካሳኢሪኒ ከተማ መነሻውን ያደረገው ይህ ተቃውሞ ወደ ሌሎች የሀገሪቱ አካባቢዎች እየተዛመተ ይገኛል ።
መንግሥት አመጹን በእንጭጩ ለመቅጨት እርምጃ እየወሰደም መሆኑን ዘገባዎች ያመለክታሉ፤ ፖሊስ አስለቃሽ ጋዝ በመጠቀም ተቃውሞውን ለመበተን እርምጃ በመውሰድ ጉዳት እንዳይደርስ መከላከሉን የቀጠለ ሲሆን፣ በካሳኢሪኒ በድርጊቱ የተሳተፉ 18 ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር እንደዋሉ መግለጹን ዘገባዎች ያመለክታሉ።
ተጠርጣሪዎች በቁጥጥር ስር የዋሉት ጎማ በማቃጠል፤ ድንጋይ በመወርወር፤ በርካታ መንገዶችን በመዝጋት በጸጥታ አካላታ ላይ ጥቃት መፈጸማቸው መሆኑን ፖሊስ የገለጸ ሲሆን፣ በአመጹ ላይ ያልተገባ ድርጊት የፈጸሙትን አካላት ለህግ በማቅረብ እንዲጠየቁ የማድረጉ ሂደት ተጠናክሮ እንደሚቀጥልም ጠቁሟል።
የጀርመን ፕሬስ ድርጅት በበኩሉ የቱኒዚያ ጋዜጠኞች ኅብረት በወጣቶች የሚታየው ከፍተኛ መጠን ያለው ሥራ አጥነት፤ የመንግሥት አካላት በዜጎች ላይ የሚያደርሱት ፈተና ጋዜጠኛው ራሱን እንዲያጠፋ ምክንያት መሆናቸውን ዘግቧል። «ዛሬ የሀገሪቱ መሪዎች በሙሉ በወጣቶች ላይ ለሚደርስባቸው መከራ ተጠያቂዎች ናቸው፤ ኃላፊነት ሊሰማቸው ይገባል» ሲልም ማህበሩ አስገንዝቧል። በቱኒዚያ አሁን ያለውን ችግር ለመፍታት እንቅስቃሴ መደረጉን እንደሚቀጥል ያስታውቃል። በቱኒዚያ የተፈጠረውን አብዮት ስምንተኛ ዓመት ለማክበር እና በሀገሪቱ በመገናኛ ብዙኃን ላይ የሚደርሰውን አስከፊ ችግር ለመቃወም በመጪው ጥር 14ቀን 2019 አጠቃላይ እንቅስቃሴ ለማድረግ ጥሪ መቅረቡንም ዘገባው አስነብቧል።
ኤ ኤፍ ፒ በበኩሉ በቱኒዚያ የተቀሰቀሰው ህዝባዊ ተቃውሞ ከዕለት ወደ ዕለት እየተባባሰ እንደሚገኝ እንዲሁም የተቃ ውሞው መበርታት አገሪቱ አደገኛ ቀውስ ውስጥ እንድትገባ ሊያደርጋት እንደሚችል ዘግቧል። ተቃውሞው በካሳኢሪኒ ከተማ መጀመሩን የጠቀሰው ዘገባው፤ በአሁኑ ወቅት በሦስት የተለያዩ ከተሞች መዛመቱን አመልክቷል።
የአገሪቱ ደህንነት ቃል አቀባይ ዋሊድ ሀኪማ ንግግርን ዋቢ በማድረግ በቱኒዚያ ምስራቃዊ ክፍል የምትገኘው ጀቢኒያን እንዲሁም በሰሜናዊ ቴቦርባአ የተቃውሞ እንቅስቃሴዎች መዛመታቸውን ዘግቧል። መንግሥት በተቃውሞ የወጡ ዜጎቹን በአስለቃሽ ጋዝ ለመበተን ከሚያደርገው እርምጃ ባለፈ በዚህ አካባቢ ብቻ አምስት ሰዎችን በቁጥጥር ስር እንዳዋለ ዘገባው አስታውቋል።
በፈረንጆቹ አዲስ ዓመት የመጀመሪያው ወር ላይ በቱኒዚያ የተቀውሞ ሰልፍ ማድረግ የተለመደ እየሆነ መጥቷል የሚለው ዘገባው፣ እኤአ 2018 እንዲሁም በ2011 በቱኒዚያ የተካሄደው እንቅስቃሴም አስታውሷል። ሰሞኑን የተቀሰቀሰው እንቅሰቃሴም ከዚሁ ጋር የሚመሳሰል እንደሆነ አመልክቷል፡፡ እንቅስቃሴውን ከወዲሁ መግታት ካልተቻለ የዛሬ ስምንት ዓመት የተቀሰቀሰው የዓረብ አብዮት ዳግም መቀስቀሱ አይቀርም ሲሉም አትቷል።
ዘገባው ከስምንት ዓመት በፊት በህዝባዊ ተቃውሞ ለ23 ዓመት አገሪቱን ሲመሩ የነበሩትን ፕሬዚዳንት ቤን አሊን በማሰናበት በዴሞክራሲያዊ የሽግግር ሂደት አዲስ መሪ ማምጣት መቻሉን አስታውሷል። የሰሞኑ ተቃውሞም በአገሪቱ የሽግግር መንግሥት ከተደረገ በኋላም ችግሮች መፍትሄ አለማግኘታቸውን ተከትሎ የተቀሰቀሰ ነው ሲል ዘግቧል። የዋጋ ግሽበት ከቁጥጥር ውጪ መሆን እንዲሁም ሥራ አጥነት በከፍተኛ መጠን መጨመር በድህነት ወለል ስር የሚገኙትን ዜጎች ኑሮ ማሻሻል እንዳይቻል ማድረጋቸውን ዘገባው ጠቁሟል።
ፍራንስ 24 በበኩሉ፤ የቱኒዚያ ኢኮኖሚያዊ ማህበራዊ መብቶች ፎረም ፕሬዚዳንት ሜልዱ ሮምሀን ዋቢ በማድረግ እንደገለጸው፤ በፖለቲካ ውስጥ የመደብ መከፋፈል እየተንጸባረቀ መምጣት በተለይ ወጣቶች የኑሮ ዋስትና ማጣት ተስፋ እንዳይሰንቁ አድርጓቸዋል፡፡ ህዝባዊ ተቃውሞው ወደ አስቸጋሪ ደረጃ ማምራቱ የማይቀር ስለመሆኑም ጠቋሚ ሁኔታዎች ይስተዋላሉ ።
ዘገባው ፕሬዚዳንት «የቱኒዚያዊያን ችግር ተአማኒነት ያለው የፖለቲካ ሥርዓት እጥረት ነው፤ ይህን በትክክል ተደራሽ ማድረግ ይገባል፤ ስለዚህ የተጀመረው ተቃውሞ ወደ ሌሎች አካባቢዎች እንደሚዛመት እጠብቃለው። በቅርብ ወራት ውስጥ በቱኒዚያ የፖለቲካ ህይወት ወደሽባነት ተቀይሮ በ2019 የፕሬዚዳንሻል ምርጫ በህዝብ ድጋፍ የተደረገለት አካል እንደሚቀመጥ ተስፋ አደርጋለው።» ሲሉ መናገራቸውን አመልክቷል፡፡ የተቃውሞው መጠን ወደ ሌሎች ከተሞች በፍጥነት በመዛመት ከስምንት ዓመት በፊት የነበረውን ታሪክ ሊደግም ይችላል ሲል ስጋቱን አስፍሯል።
በሞሀመድ ቦአዚዝ የህይወት መስዋእትነት አሀዱ ያለው የያኔው አብዮት በቱኒዚያ ላይ ብቻ እንዳላበቃ ይታወሳል፡፡ መላው ዓለም ሳይቀር ይሆናል ብሎ ያልገመተውና ያልጠበቀው ክስተት በሰሜን አፍሪካና በመካከለኛው ምስራቅ ሀገራት ውስጥ እንዲታይ አድርጓል፡፡ በርካታ ወገኖች የአብዮት አብዮት የሚል የቁልምጫ ስም ያወጡለት ድንገተኛ ህዝባዊ አብዮት በእነዚህ ሀገራት ውስጥ ተቀጣጥሎ ለውጦችን አስከትሏል፡፡
የጋዜጠኛ አብዱራዛቅ ድርጊትን ተከትሎ በቱኒዚያ የተቀሰቀሰው ከባድ ህዝባዊ ተቃውሞ፤ አዝማሚያው በአገሪቱ መንግሥት ላይ ብቻ እንደማይወሰን እየተገለጸ ይገኛል፡፡ ወደ ሌሎች አገራት ላለመዛመቱ ማስተማመኛ እንደሌለም እየተነገረ ነው። ከስምንት ዓመት በፊት በሞሃመድ ቦአዚዝ የተቀጣጠለው አብዮት ከቱኒዚያ ተሻግሮ በርካታ የአረብ አገራትን እንዳዳረሰው ሁሉ፣ በጋዜጠኛው አብዱራዛቅ እርምጃ የተጀመረው ይህ አመጽ የት ያደርስ ይሆን? የሚለው በቀጣይ የሚመልስ ይሆናል።
አዲስ ዘመን ታህሳስ 23/2011
ዳንኤል ዘነበ