ለሶስት አስርት አመታት ሀገሪቱን በፕሬዚዳንትነት መርተዋል። ወደዚህ የስልጣን እርከን ብቅ ያሉትም እኤአ በ1989 በመፍንቅለ መንግስት ነበር፡፡ የስልጣን ዘመናቸው በጭቆና፣በዘር ማጥፋትና በሰብአዊ መብት ረገጣ የተጨማለቀ በመባል ይታወቃል፡፡
በፕሬዚዳንትነት የስልጣን ዘመናቸው በተመድ መረጃ መሰረት ከ200 እስከ 400 የሀገሪቱ ዜጎች በግጭት ሳቢያ አልቀዋል። ሁለት ነጥብ ሰባት ሚሊዮን ሰዎች ደግሞ ተፈናቅለዋል። እርሳቸው የመሰረቱት ሚሊሺያ ለእዚህ ቀውስ በቀጥታም ይሁን በተዘዋዋሪ ተጠያቂ መሆኑን በቅርቡ ለንባብ የበቃ የዘ ጋርዲያን ጋዜጣ ይዞት የወጣ መረጃ ያመለክታል። ሙስና ሌላው ተዘፍቀውበታል የሚባለው ወንጀል ነው፡፡ የቀድሞው የሱዳን ፕሬዚዳንት ኦማር ሀሰን አህመድ አልበሽር፡፡
እኚህ ሰው ታዲያ በሰፈሩት ቁና… እንዲሉ እኤአ ከታህሳስ ወር 2018 አንስቶ በቅድሚያ ከኑሮ ውድነት ጋር በተያያዘ በኋላም ፓለቲካዊ ጥያቄዎችን መሰረት በማድረግ በተቀሰቀሰባቸው ህዝባዊ ተቃውሞ ለ30 አመታት ፈላጭ ቆራጭ ሆነው ከቆዩበት የፕሬዚዳንትነት ስልጣን ባለፈው ሚያዝያ 2019 ተነስተዋል፤በተለያዩ ወንጀሎችም ተርጥረው ወህኒ ወርደው ጉዳያቸው በህግ እየታየ ይገኛል። ሀገሪቱም በአሁኑ ወቅት በጦር ሀይሉና ሲቪሎች የጋራ ምክር ቤትና በሲቪል በሚመራ ካቢኔ እየተዳደረች ትገኛለች።
ሰሞኑን ደግሞ ‹‹እባብ ግደል ከነበትሩ ገደል›› ሆነና ነገሩ እኤአ በ1992 የተመሰረተው ፓርቲያቸውም ህልውናውን እንዲያጣ የሚያደርግ ህግ አዲሱ የሀገሪቱ መንግስት ይፋ አድርጓል። ህጉ ሱዳንን ለበርካታ አመታት ሲመራ የቆየውን የአልበሽርን ብሄራዊ ኮንግረስ ፓርቲ አፍርሶታል። በተጨማሪም ህጉ በህገወጥ መንገድ የተመዘበረ የህዝብ ገንዘብ ያለውን የፓርቲውን ሀብትና ንብረት ጭምር እንዲወረስም የሚያደርግ ነው። ለእዚህም ኮሚቴ እንደሚቋቁም መንግስት አስታውቋል። የለውጡ አቀንቃኞች የአልበሽር ዘመን ባለስልጣናት ለህግ እንዲቀርቡ የሚያደርግ ድንጋጌ በሀገሪቱ አዲሱ ህገመንግስታዊ ቻርተር ውስጥ እንዲካተት ሲጠይቁ መቆየታቸውን ዘገባዎች አስታውሰዋል፡፡
የአልበሽር ፓርቲ ግን የመንግስትን እርምጃ አጣጥሎታል።ፓርቲው በስልጣን ላይ ያለውን መንግስት ህገወጥ በማለት እርምጃውንም የሞራል ዝቅጠት የተሞላበትና የውድቀቱ አንድ ማሳያ ሲልም ነው ያስገነዘበው። ፓርቲው በየትኛውም ህግና ውሳኔ እንደማይደናገጥም በመግለጽ፣ፓርቲው ጠንካራና ሀሳቡ ሁሉ መቼም ቢሆን መሬት ጠብ የማይሉ ናቸው ሲል በማህበራዊ ትስስር ገጹ ማስነበቡን ቢቢሲ በዘገባው አመልክቷል፡፡ፓርቲው ይህን ይበል እንጂ የሀገሪቱ ዜጎች፣ አክቲቪስቶችና ተንታኞች ለህጉ ከፍተኛ ስፍራ ሰጥተውታል፡፡
ህጉ የጸደቀው የሱዳን የላእላይ ምክር ቤትና ካቢኔው 14 ሰአታት የወሰደ ውይይት ካደረጉበት በኋላ መሆኑን አለምአቀፍ መገናኛ ብዙሃን በየዘገባዎቻቸው አስነብበዋል። አዲሱ ህግ በእዚሁ እለት የአልበሽር መንግስት ሴቶች መልበስ ባለባቸው ላይና በሌሎች መብቶቻቸው ላይ ክልከላ ጥሎ የነበረ ሌላ ህግንም ሽሯል፡፡ ህጉ በአልበሽር የስልጣን ዘመን በዋና ዋና የሃላፊነት ቦታዎች ላይ የሰሩ ባለስልጣናትም ለሚቀጥሉት 10 አመታት በሀገሪቱ የፓለቲካ እንቅስቃሴዎች እንዳይሳተፉ የሚያግድ አንቀጽ የተካተተበት ሲሆን፣ብዙ ማነጋገሩን ውይይቱን የተከታተሉ ምንጮችን ጠቅሶ ዘ ጋርዲያን ዘግቧል።
ህጉን ይፋ ያደረጉት የሐገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር በትዊተር ገጻቸው‹‹ፓርቲው በህግ እንዲፈርስ የተደረገው በበቀል በመነሳሳት ሳይሆን የሱዳናውያንን ክብር ለመጠበቅ ሲባል ነው፡፡ ››ሲሉ ገልጸዋል፡፡ የሀገሪቱ ፍትህ ሚኒስትር በሀገሪቱ ብሄራዊ ቴሌቪዥን በሰጡት ማብራሪያ እንዳስታወቁት፤የፓርቲው ሀብትና ንብረት እንዲወረስ ጭምር የሚደነግገው ይህ ህግ፣የአልበሽር የስልጣን ዘመን ማብቃቱን ለማረጋገጥ ሲባል የተወሰደ እርምጃ ነው፡፡የሀገሪቱ የማስታወቂያ ሚኒስትር ፋይሳል ሞሀመድ ሳሌህ በበኩላቸው፤ህጉ በሱዳን አዲስ ዘመን ለማምጣት ታስቦ የወጣ መሆኑን አስታውቀዋል፡፡
መንግስት ህጉን ይፋ ማድረጉን ተከትሎ የካርቱም ነዋሪዎች ያለፈውን ሀሙስ ምሽት በሙሉ ደስታቸውን ገልጸዋል፡፡ በመዲናዋ ካርቱም አሽከርካሪዎችም ጡሩምባዎችን ከፍ አርገው ሲያሰሙ አምሽተዋል፡፡
የአልጀዚራ የዜና ወኪል ሂባ ሞርጋን ከካርቱም እንደዘገበው፤አዲሱ ህግ በሀገሪቱ የመልካም አስተዳደር ለውጥ እንዲመጣ ለወራት ሲጠይቁ የነበሩ ሱዳናውያንን ፍላጎት በተወሰነ መልኩ እንደሚመልስ አስታውቋል፡፡ፊልም ሰሪውና አክቲቪስቱ ሆጆጅ ኩካ፣‹‹ይህ ለውጥ ይመጣል ብለን ስንጠበቅ የነበረው ከአንድ ወር በፊት ነበር።እርምጃው ሁላችንም በአንድነት እንድንቀጥል የሚያደርግ ነው። ››ብሏል ።‹‹የአልበሽር ስርአት ግብአተ መሬት መፈጸሙን የሚያመለክት ነው።››ሲል ገልጾታል፡፡ህጉ አዲሱ መንግስት ከአልበሽር አገዛዝ ሃላፊዎች የሐገሪቱን የገንዘብ ነክ አስተዳደር የሚቆጣጠርበት አቅም ያገኘበት ነው፤እነዚህ ሃላፊዎች ሁሉንም ነገር ይዘውት ነበር። ››ሲል ገልጾ፣ይህን በእርግጥ መቆጣጠር ተችሎ ይሆን?››ሲልም ጠይቋል።
በሱዳን ለውጥ እንዲመጣ በጽኑ ሲንቀሳቀሱ የቆዩ አክቲቪስቶችም ይህን የመንግስት ውሳኔ በአድናቆት ተቀብለውታል፡፡ እርምጃውን ይህ ለውጥ እንዲመጣ አጥብቀው ሲንቀሳቀሱ ለነበሩ ወገኖች ጥያቄዎች የተሰጡ ቁልፍ ምላሾች ሲሉ መግለጻቸውን የዘ ጋርዲያን ዘገባ አመልክቷል።
በተቃውሞ እንቅስቃሴ ጉልህ ስፍራ ከነበራቸው አንዱ የሱዳን ሙያተኞች ማህበር ቃል አቀባይ ሳምሂር ሙባራክ ‹‹ፓርቲውን የሚያፈርሰው ህግ መውጣት ለሱዳን ታሪካዊ ወቅት ነው።››ሲል ለቢቢሲ ገልጸዋል፡፡ ህጉ ለሱዳናውያን እፎይታን ያገናጸፈ ነው፤ምክንያቱም በአልበሽር አገዛዝ በአንድም ይሁን በሌላ እያንዳንዱ ሱዳናዊ ክፉኛ ተሰቃይቶ ነበር፡፡››በማለትም ተናግሯል፡፡
ለውጡ እንዲመጣ በተቃውሞ እንቅስቃሴ ውስጥ በሰፊው የተሳተፉት የሀገሪቱ ሴቶች በተለይም የሴቶች መብት አክቲቪስቶች ፓርቲው እንዲፈርስ ሀብትና ንብረቱም እንዲወረስ የሚያስችለው ህግ መውጣቱን እንዲሁም የሴቶችን መብት ይጨፈልቅ የነበረው ህግ ከስራ ውጪ መደረጉን በደስታ ተቀብለውታል፤ ህጎቹ ሱዳንን ወደተሻለ ምዕራፍ ለማሸጋገር የተደረገው ትግል የመጀመሪያ ውጤት ሲሉም መገልጻቸው ተመልክቷል።
በበርሚንግሃም ዩኒቨርሲቲ የአፍሪካ ፓለቲካ ባለሙያው ኒክ ቼሴማን በሱዳን የመጣውን ለውጥ አስመልክቶ ያለው ጥያቄ ለውጡ ኮስሞቲክ ወይም የላይ ላይ ነው? የአልበሽር አገዛዝ አስኳሉ አይነካ ይሆን? የሚል እንደነበር አስታውቀዋል። ተንታኞች የህጎቹ መውጣት የሽግግር ወቅቱ ባለስልጣናት የአልበሽርን ጨካኝ አገዛዝ አሽቀንጥሮ ለመጣል ምን ያህል ፈቃደኛ መሆናቸውን ወይም አቅሙ እንዳላቸው ያመለካተ ትልቅ እርምጃ ሲሉ ገልጸውታል።
አዲስ ዘመን ኅዳር 23/2012
ኃይሉ ሣህለድንግል