አዲስ አበባ፡- በኢትዮጵያ እዚህም እዚያም የሚስተዋሉትን ግጭቶች በዘላቂነት ለመፍታት ሃይማኖታዊ አስተምህሮቶችን በማስረጽና የጋራ ማህበራዊ እሴቶችን በመጠበቅ ረገድ ትኩረት ሰጥቶ መስራት እንደሚገባ ተገለፀ፡፡
የኢትዮጵያን ወንጌላውያን አቢያተ ክርስቲያናት ህብረት አመራር የቦርድ ሰብሳቢና በጀስትስ ፎር ኦል የሰላምና ደህንነት አማካሪ መጋቤ ዘርሁን ደጉ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፣ ሰላማዊነት፣ እውነተኛነትና ይቅርታ መስጠትና መቀበል የሃይማኖቶች አስተምህሮት መሰረት ቢሆኑም ሃይማኖታዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ መጥተዋል፡፡ ምዕመናን ወደ ሃይማኖት ተቋማት ይሄዳሉ እንጂ የሃይማኖት አስተምህሮቶቹን ተግባር ላይ በማዋል ረገድ ችግሮች ይታያሉ፡፡
ኢትዮጵያ ሃይማኖት ያላቸው ሕዝቦች አገር እንደሆነች ቢታወቅም ሃይማኖት የላቸውም በሚባሉ አገራት ያልተደረጉ ድርጊቶች ሲፈፀሙ ይስተዋላሉ የሚሉት መጋቤ ዘሪሁን የግለሰቦች ጸብ ጭምር ብሔርና የሃይማኖት መልክ እየያዘ መጥቷል ብለዋል፡፡ መስጅድና ቤተክርስቲያን ሲቃጠሉ ባቃጠሉት አካላት ላይ የሃይማኖት ተቋማት በጋራ ሆነው ከሃይማኖቱ እስከማገድ የሚያደርስ እርምጃ መውሰድ አለባቸው፤ የሃይማኖት ተቋማት ተከታዮቻቸውን ሲያስተምሩና ሲገስጹ ራሳቸውም ጭምር ምሳሌ መሆን እንዳለባቸው ገልጸዋል፡፡
እንደ አገር የነበሩን አብሮ የመኖር ማህበራዊ እሴቶች እየተሸረሸሩ መምጣታቸው፣ በሚያስተሳስሩን የጋራ ጉዳዮች ላይ ትኩረት ሰጥተን አለመስራታችን፣ሥራ ፈላጊው የወጣት ቁጥር እየተበራከተ መሄድ፣ ፍትሀዊ የሀብት ክፍፍል አለመኖርና መሰረታዊ በሚባሉ ችግሮቻችን ዙሪያ እውነተኛ መድኃኒት እየተሰጣቸው አለመሄዳቸው ለግጭቶቹ መባባስ አስተዋጽኦ ማድረጋቸውንም ተናግረዋል፡፡
በአሁኑ ጊዜ የሚከሰቱ የብሔርና የሃይማኖት መልክ የያዙ ግጭቶች የተፈጠሩት የተለያየ ፍላጎት ባላቸው ፖለቲከኞች መሆኑን ገልጸው እነዚህ ፖለቲከኞች የተወለዱበትን ብሔረሰብና የሚናገሩትን ቋንቋ ሽፋን አድርገው አንዱን ብሔር ከሌላው ጋር የማጋጨት ሰፊ ዘመቻና ሥራ እየሰሩ በመሆኑ እንጂ በታሪካችን የኢትዮጵያ ሕዝብ እርስ በርሱ በብሔር፣ በሃይማኖትና በቋንቋ መነሻ ምክንያት ሆኖ የተጋጨበት ዘመን የለም ሲሉ ገልጸዋል፡፡
የግጭቶቹን መንስኤ ለመፍታትም ሁሉም ወገን የበኩሉን ድርሻ መወጣት እንደሚጠበቅበት አመልክተው የግጭቶቹ መነሻ ምክንያቶች ላይ ትኩረት ሰጥተን ከሰራንና በሰለጠነ መንገድ በውይይት መፍታት ከቻልን ተጨባጭ ለውጥ እንደሚመጣ አመልክተዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 22/2012
ጌትነት ምህረቴ