ኢትዮጵያውያን የዕለት ተዕለት ማህበራዊ ግንኙነታቸውን፣ ኢኮኖሚያዊ እንቅስቃሴያቸውን፣ በአጠቃላይ ሕይወታቸውን ሲመሩ ከባህላዊ እሴታቸው አይርቁም።በራሳቸው ባህላዊ እሴትና ሥርዓት ችግርን ያስወግዳሉ፤ በጋራ ሥራዎቻቸውን ያከናውናሉ።ደስታቸውን ይካፈላሉ። በዚህም የባህል እሴቶቻቸውን ለትናንት፣ ለዛሬ እና ለነገ የአኗኗር ሥርዓታቸው ይጠቀሙበታል።
ድንቅ የባህላዊ እሴቶች ባለቤት ከሆኑት መካከል ወደ ውቢቷ የቤንሻንጉል ጉሙዝ ክልል እናቅና።በክልሉ አምስት ብሔረሰቦች አሉ።የአምስቱንም ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴ ማሳየት በዚህች አጭር አምዳችን ከባድ ነውና ለዛሬ የሺናሻ ብሄረሰብን ባህላዊ የግጭት አፈታት ዘዴን እናስነብባለን።
የሺናሻ ብሄረሰብ የባህላዊውን ህግ (ሽምግልና) ግጭትን በመፍታት ዘመናትን የተሻገረ እንደሆነ የብሔረሰቡ ሽማግሌዎች ይናገራሉ።በባህሉ የማያምንና ተቀብሎ የማይተገብር ወይም አባቶችን የማያዳምጥ ችግር ይደርስበታል ተብሎ ይታመናል። ስለዚህ ማንም የብሄረሰቡ አባል ከአባቶች ቃል ፈቀቅ አይልም። አያሌ ዘመናትንም እየተዳደሩበት የኖሩትና ችግሮቻቸው በመልካም መፍትሄ የቋጩት በዚህ እምነታቸው ነው ።
በብሄረሰቡ ዘንድ ባህላዊ የዳኝነት ስርዓት ሶስት ደረጃዎች ተሰጥተውት ይሰራበታል።እነሱም የመጀመሪያ ደረጃ ፍርድ ‘’ቡራ’’ ተብሎ
ይጠራል፤ ሁለተኛው ደረጃ ደግሞ ‘’ኔማ’’ሲባል ሶስተኛው ደረጃ ፍርድ ‘’ፄራ’’ ይባላል።እያንዳንዱ የዳኝነት ደረጃ የራሱ የሆነ አተገባበርና መመሪያ አለው።ይኼም ቡራ የመጀመሪያ ደረጃ ዳኝነት “ቡራ” አንድ ሽማግሌ ብቻውን ሆኖ የሚፈርድበት የቤተሰብ ባህላዊ ችሎት ነው።
የ”ቡራ” ፈራጆች ወይም ሽማግሌዎች የሚመረጡት ከሟችና ከገዳይ ቤተሰብ ውጭ የሆኑና ከገለልተኛ አካል (ወገን) የተወጣጡ ናቸው። በሁለቱም ቡድኖች (ከሟች ወገንና ከገዳይ ወገን) ምስጢር ይጠብቃሉ ተብሎ የታመነባቸው ሊሆኑም ይገባል።ምክንያቱም ከአንድ ወገን የሆነ ነገር ካፈተለከ ወይም ምስጢር ከወጣ ግጭቱ አይበርድም።እርቅ ሊፈጸም የሚችልበትም ሁኔታ ይዳከማል።
“ቡራ” መጀመሪያ ደረጃ ግጭት መፍቻ እንደመሆኑ መጠን የቅርብ ጊዜ ወይም ትኩስ የሆነ አለመግባባቶችና የግድያ ግጭቶችን የሚያይ ችሎት ነው። በመሆኑም የግጭቱ አፈታት ዘዴ እንደየ አስፈላጊነቱ ሊታይ የሚችል እንጂ ቋሚነት የለውም። ስለዚህም በ ‘’ቡራ” ደረጃ ፍርድ ላይ ፈራጅ ሆኖ የሚሾመው ወይም የሚመረጠው ግለሰብ የብሄረሰቡን ባህላዊ ጉዳዮችን በደንብ ጠንቅቆ ያወቀና የተረዳ መሆን አለበት።ግጭቶችን በመፍታት ዙሪያ በማህበረሰቡ ዘንድ ተቀባይነት ያለው፣ ለእውነት ሲባል የሚፈርድ መሆንም ይጠበቅበታል። ‹‹ቡራ›› ፍርድ ላይ ፈራጅ የመጀመሪያ እንደመሆኑ መጠን የበዳይን ጥፋት ተመልክቶ በራሱ አቅም የማይፈታ ከሆነ ወደ ሁለተኛ ደረጃ ፍርድ” ኔማ” እንዲሄድ የሚደረግበት ሂደት ነው።
ኔማ
‹‹ኔማ›› ሁለተኛው ደረጃ ዳኝነት ሲሆን፤ ሶስት ሽማግሌዎች በጋራ ሆነው የሚፈርዱበት ባህላዊ ችሎት ነው። እነዚህ ፈራጆች ከማህበረሰቡ ጋር የጠበቀ ቁርኝት ያላቸው፣ ለገዳይ ወይም ለሟች ወገን የማያዳሉ፣ በማህበረሰቡ የሚታመኑና ተቀባይነት ያላቸው እንዲሁም የማህበረሰቡን ባህል ጠንቅቀው የሚረዱ ሽማግሌዎች መሆን አለባቸው።በተለይም በባህሉ መሰረት በተለያዩ ምክንያቶች በሰዎች መካከል የሚፈጠሩ ግጭቶችን በመፍታት ልምድ ያላቸው መሆን ይጠበቅባቸዋል።ስለዚህም ከበድ ያለ ችግር ሲመጣ ማህበረሰቡ ወደ እነርሱ ዘንድ ይሄድና ችግሩን ያስረዳል።ሽማግሌዎቹም በማስታረቅ ከፍተኛውን ድርሻ የያዙ ናቸውና ማህበረሰቡ የጣለባቸውን ሀላፊነት ይወጣሉ።
‹‹ኔማ›› በዘመናዊው ህግ ይግባኝ እንደ ማለት ነው። በቡራ ፍርድ አንድ ሰው ቅር ከተሰኘ የተፈረደው ፍርድ ሚዛናዊነትን የያዘ አይደለም በማለት ወደ ሁለተኛው ፍርድ ይግባኝ የሚሉበት ነው።ስለዚህም ተበዳዩ ‘’ኔማ” በማለት ፈራጅ ይግባኙን ሰምቶ እንዲዳኘው ይጠይቃል።
ጼራ
ሦስተኛ ደረጀ የግጭት መፍቻ ዘዴ ወይም ዳኝነት ደግሞ ‹‹ፄራ›› የተሰኘው ነው። ይህ ባህላዊ ችሎት እንደ ቡራ ሁሉ በአንድ ሰው የሚመራ የዳኝነት ችሎት ነው።የመጨረሻው የይግባኝ ደረጃ በዘመናዊው ዳኝነት “ሰበር” እንደማለት ነው።ከዚህ በኋላ ይግባኝ የማይጠየቅበት የዳኝነት የመጨረሻው ስርዓት ነው። ይህ ችሎት በይግባኝ ሰሚ ችሎት ‹‹ኔማ›› የአንድን ሰው ጥፋት ለመፍታት የማይቻለውና ጥፋቱ ካቅማቸው በላይ በሚሆንበት ጊዜ የሚመጡበት ሲሆን፤ ‘’ፄራ” የፍርድ ችሎት ተቀብሎ ያስተናግዳቸዋል።
በፄራ የፍርድ ችሎት ፈራጅ እንደሌሎቹ ሁሉ በስነ ምግባር የታነፁ፣ ታማኝና ቅቡልነት ያላቸው፣ ፍርዱ እውነትን መሠረት ያደረገ፣ የብሔረሰቡን ባህል ጠንቅቆ የሚያውቁ መሆን መቻል አለባቸው። በአብዛኛው ጊዜ ባህላዊ ግጭት የሚያስወግዱ ወይም የሚፈቱ ሽማግሌዎቸ ፍርድ የሚሰጡት በማህበረሰቡ በተመረጡ ሽማግሌዎች አማካይነት ነውና እዚህ ላይ ሲደርስ ያለውን መቀበል ግድ ይሆናል።ምክንያቱም የበቁና ያወቁ ናቸው ተብሎ ስለሚታመን ከዚህ ቃል ፈቀቅ ማለት አይቻልም።
ስለዚህም ሺናሻዎች በዳይ (ገዳይ) እና ተበዳይ (የሟች ወገን) ፄራ ለመምረጥ ነፃ ናቸው። በዚህም መሰረት የፄራ ሽማግሌ ሲመረጡ መሟላት የሚገባቸው ጉዳዮች ከአባት፣ ከአያት፣ ከቅድመ አያት ያገኙት የግጭት አፈታት፣ የምርቃት እውቀት ያላቸው፣ ወንጀል ነክ ጉዳዮችን በማየት ከፍተኛ ልምድ ያካበቱ፣ ምክንያታዊ የሆነ፣ ሃሳቡን በነፃነት መግለፅ የሚችልና የማሰብ ችሎታ ያለው መሆን አለበት። ከዚህ ተመራጭ ጋር ማንም መከራከርም ሆነ መቃረን አይችልም።ግን አሳምኖ የመላኩ ሁኔታ ከፈራጁ ይጠበቃል።ምክንያቱም ይህ ካልሆነ ችግሩ ሊቀጥል ይችላል።እናም በጼራ ላይ የሚሳተፍ ፈራጅ ብዙ ብቃት የሚለኩ ፈተናዎችን አልፎ የቆመ መሆን አለበት።የሚያደርገውም ከእውነት የራቀ መሆን የለበትም።
በአጠቃላይ ሺናሻዎች በባህላዊ የዳኝነት ስርዓታቸው ተጠቅመው ችግር ወግድልኝ ብለው በሰላምና በፍቅር ይኖራሉ። ባህላቸውንም ጠብቀው ለትውልድ ያስተላልፋሉ። ባህላዊ እሴቶቻችን በርካታ መልካም ገጽታዎች አሏቸውና ልንጠብቃቸውና ልንጠቀምባቸው ይገባል። ሰላም!
አዲስ ዘመን ኅዳር 21/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው