* ኬሚካሉን ለማስወገድ እስከ 5 ነጥብ 6 ሚሊዮን ዶላር ወጪ ያስወጣል
* በዓመት 20 ሚሊዮን ዶላር ኬሚካል ለማስወገድ ወጪ ይደረጋል
* የመጠቀሚያ ጊዜያቸው ያለፈባቸው ኬሚካሎችን የሚያስወግድ ህጋዊ ተቋም የለም
አዲስ አበባ፡- 1ሺህ 400 ቶን ዲዲቲ እና 20 ቶን ነባር የትራንስፎርመር ዘይት ከአገር ውጭ ለማስወገድ እየሰራ መሆኑን የአካባቢ ደንና የአየር ንብረት ለውጥ ኮሚሽን አስታወቀ፡፡ በሀገር ውስጥ ተከማችቶ የሚገኘውንና የመጠቀሚያ ጊዜው
ያለፈበትን ኬሚካል ለማስወገድ እስከ አምስት ነጥብ ስድስት ሚሊዮን ዶላር ወጪ እንደሚያስወጣ ገልጿል።
በኮሚሽኑ የደረቅና አደገኛ ቆሻሻ ህግ ተከባሪነት ዳይሬክቶሬት ዳይሬክተር አቶ ግርማ ገመቹ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ አገር ውስጥ የሚገቡትም ሆኑ አገር ውስጥ የሚመረቱ ኬሚካሎች በብዛት ተከማችተውና የመጠቀሚያ ጊዜያቸው አልፎ ህጋዊ አስወጋጅ ተቋም ባለመኖሩ ሳይወገዱ ቆይተዋል፡፡ የተከማቸው ኬሚካል አደጋው የከፋ ስለሆነ ተቋሙ የማስወገድ ኃላፊነት ባይሰጠውም ጥናት አድርጎ የለያቸውን 1ሺህ 400 ቶን ዲዲቲና 20 ቶን ነባር የትራንስፎርመር ዘይት ለማስወገድ እየሰራ ይገኛል፡፡
ኬሚካሉ ከ20 ዓመት በፊት የገባ ሲሆን፤ በስድስት ወር ጊዜ ውስጥ የእሸጋና የመጓጓዝ ሥራው ተጠናቆ እንደሚወገድ ገልጸዋል፡፡ አሁን ባለው ደረጃ ሁለቱን ኬሚካሎች ከአገር ውጪ ለማስወገድ ግምታዊ ወጪው ከ4ነጥብ 9 እስከ 5 ነጥብ6 ሚሊዮን ዶላር መሆኑን አስታውቀዋል።
ሀገሪቱ አገልግሎት ላይ ያልዋለ ኬሚካልን ለማስወገድ በዓመት 20 ሚሊዮን ዶላር እንደምታወጣም ያስታወቁት አቶ ግርማ፤ የማስወገድ ተግባሩን ለመከወን በአገር ደረጃ የተቋቋመ ህጋዊ ተቋም ባለመኖሩ አገሪቱ ለከፍተኛ ወጪ እየተዳረገች መሆኑን ተናግረዋል፡፡ አወጋገዳቸውም ቀጣይነት ያለውና በፍጥነት የሚከናወን ባለመሆኑም ወጪው ከጊዜ ወደ ጊዜ እየጨመረ ነው ብለዋል፡፡
የመጠቀሚያ ጊዜው ያለፈበት ኬሚካል በአገር ውስጥ ተከማችቶ መቆየቱ ተቋሙ ለማምከን፣ ለማከምና ለመጠቀም የሚያስችልበትን መንገድ እንዳይፈጥር አድርጎታል ያሉት አቶ ግርማ፤ በህክምናው ዘርፍ ያሉ አነስተኛ ኬሚካሎችን ማምከን የሚቻልበት ሁኔታ ቢፈጠርም ግብርና እና ኢንዱስትሪ ዘርፍ ላይ ያሉት ግን አሁንም ፈታኝ እንደሆኑ አንስተዋል፡፡
እንደ አቶ ግርማ ገለጻ፤ የኮሚሽኑ የሥራ ኃላፊነት የትኛውም ኬሚካል በአካባቢና በሰው ላይ ጉዳት አለማድረሱን ማረጋገጥና ቁጥጥር ማድረግ ብቻ ነው፡፡ ይሁንና ማረጋገጥ የሚቻለው ችግሩ ሲጠፋ በመሆኑ አመንጪውን አካል ለማገዝ ወደማስወገዱ ሥራ ተገብቷል፡፡ በመሆኑም በአገር ውስጥ የማስወገድ ሥራ የሚሰራ አካል ማዋቀር እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል፡፡
ኮሚሽኑ በጉዳዩ ዙሪያ ከሚሰሩ አካላት ጋር በመተባበር የግል አስወጋጅ ድርጅቶችን ለመፍጠር እየተሰራ መሆኑን ተናግረዋል፡፡ ይሁን እንጂ እስካሁን እውቅና ተሰጥቶት በአገር ደረጃ እየሰራ ያለ አካል እንደሌለ አስረድተዋል፡፡
አሁንም ብዙ ያልተለዩ አደገኛ ቆሻሻዎች በየተቋማት ሊኖሩ እንደሚችሉ የጠቀሱት አቶ ግርማ፤ ይህንን ቶሎ ማጥራትና ችግር እንዳይፈጥሩ ማድረግ ይገባል ብለዋል፡፡ የአደጋ መጠኑ ከፍ ካለ የሚወጣው ወጪም በዚያው ልክ ያይላል፡፡ ስለሆነም አገር ለከፍተኛ ወጪ እንዳትዳረግ አገር አቀፍ የኬሚካል ልየታና ቆጠራ በማድረግ ቁጥጥርና እገዛ ማድረጉ ላይ የተጠናከረ ሥራ መስራት ያስፈልጋል፡፡ በተለይ ወጪን መቀነስ ላይ፣ ቴክኖሎጂ ማምጣትና ብቃት ያለው ባለሙያ መፍጠር ላይ በትኩረት መስራት ይገባል ሲሉ አሳስበዋል፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው