አዲስ አበባ:- በሀገር ውስጥ ብዙ ችግሮች ቢኖሩም በግልጽ ውይይት ላይ ተመስርቶ ለመፍታት ያለመቻል ልምዱ ከሁሉም የላቀ ችግር መሆኑ ተገለጸ።
የኦሮሚያ እና የአማራ ምሁራን ውይይት ትናንትና በኢሊሌ ሆቴል በተካሄደበት ወቅት የብልጽግና ፓርቲ ማዕከላዊ ኮሚቴ አባል አቶ ታዬ ደንዳ እንደገለጹት፣ አሁን ላይ እንደሀገር ብዙ ችግሮች አሉብን፣ ከሁሉም በላይ ግን በግልጽ መወያየት ያለመቻል ልምዱ ትልቅ ፈተና ሆኗል። በመሆኑም ምሁራን ዕውነቱን ሳይሸፋፍኑ ግልጽ ውይይት በማድረግ ለቀጣዩ ትውልድ የበለጸገች ሀገር ስለማስተላለፍ ሊሰሩና ሊመክሩ ይገባል።
<<ምንም አይነት ትርክት ቢኖር የኦሮሞ እና የአማራ ህዝቦች ኢትዮጵያን በመገንባት ረገድ የጋራ ታሪክ አላቸው>> ያሉት አቶ ታዬ፤ ይሁንና አንዱ ወገን “የቀድሞው ሁሉ ዕውነተኛ ነው” ሲል ሌላው ደግሞ “የቀደመውን ሁሉ መጥፎ ነው” በማለት ማዶ ለማዶ ተራርቀው መቆማቸውን ተናግረዋል። በመሆኑም የሀገረ መንግሥት ግንባታው የተጀመረ እንጂ ያላለቀ በመሆኑ የተሳሳተውን አስተካክሎ መልካሙን ስለማስቀጠል በማሰብ ትብብር የሚያጠናክሩ ሰፊ ውይይቶች ማድረግ እንደሚያስፈልግ ገልጸዋል።
የምጣኔ ሃብት ባለሙያው ዶክተር ጉቱ ቴሶ <<ውይይት፣ ድርድር እና ትብብር ህብረብሔራዊነት እና ተቃርኖ ባሉበት ሀገር>> በተሰኘ ጽሁፋቸው እንደገለጹት ፤ አለመግባባትና ጸብ ያለው በምሁራኑ ውስጥ እንጂ አርሶአደሩ ጋር አይደለም። የፖለቲካ ፓርቲዎችም በሚያለያያቸው ጉዳይ ተመስርተው ስለተቋቋሙ አለመግባባቶቹ እየሰፉ የመጡት በምሁራኑ በኩል ነው። በመሆኑም “እናንተ እና እኛ” ከሚል ጣት መቀሳሰር ወጥቶ ግልጽ እና ገንቢ ውይይቶችን በማድረግ ምሁሩ ሊከሰት የሚችለውን ችግር መቀነስ አለበት ብለዋል።
<<ቅኝ ባንገዛም በየጊዜው ጦርነት መኖሩ፣ ሰፊ ሃብት ቢኖረንም ልዩነቶቻችን እየበዙ በመምጣታቸው የተነሳ ለተቀረው ዓለም ግርምት እየፈጠርን ነው>> ያሉት ዶክተር ጉቱ፤ ለዚህ ችግር ዋነኛ ተጠያቂ የሆነው ምሁሩ በመሆኑ በመተማመን ላይ የተመሰረተ፣ ግልጽ ውይይትን በማካሄድ ትብብርን ማጠናከር እንዳለበት ገልጸዋል። የዩኒቨርሲቲው መምህራኖችም አላስፈላጊ ጽሁፎችን ማህበራዊ ድረገጽ ላይ ከማሰራጨት ይልቅ ለሰለጠነ ውይይት መንገድ ሊጠርጉ እንደሚገባ አስረድተዋል።
ውይይት ያስፈልጋል ሲባል ውይይቱን ለጊዜ መግዣነት ሊጠቀሙ የሚችሉ ሰዎች መኖራቸውን የጠቀሱት ዶክተር ጉቱ፤ ውይይት ለጊዜ መግዣነት ከዋለ አለመተማመንን በማስፈን ወደባሰ ችግር ሊወስድ ስለሚችል ጥንቃቄ ማድረግ ያስፈልጋል። ውይይቱንም በኦሮሞ እና በአማራ ህዝቦች መካከል ሳይሆን በጠብ አጫሪዎች መካከል ጭምር በማድረግ አካታችነት ያለው ውጤት ስለማምጣት መታሰብ እንዳለበት ገልጸዋል።
የህግ ባለሙያው ዶክተር ዮናስ ተስፋ በበኩላቸው፤ እንወያይ ሲባል ነገን አሻግሮ ስለልጆቻችን እጣ ፈንታ መልካምነት በሚያስብ መልኩ መሆን እንዳለበት ተናግረዋል። እንደሩዋንዳ እና ደቡብ ሱዳን እልቂት ከመከሰቱ በፊት በመነጋገር መፍትሄ ማምጣትና ትብብሩን ማጠናከር ይገባል ብለዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2012
ጌትነት ተስፋማርያም