አዲስ አበባ፡- የቅዱስ ጳውሎስ ሆስፒታል ሚሌኒየም ሜዲካል ኮሌጅ የኩላሊት ንቅለተከላ ህክምና ማዕከል በቀድሞ ጠቅላይ ሚኒስትር አቶ ኃይለማርያም ደሳለኝ የማረሚያ ቤቶች ንብረት የሆነው ህንጻና ቦታ የተሰጠው ቢሆንም የስም ዝውውር ሳይደረግለት ሁለት ዓመታት ማስቆጠሩ ተገለጸ፡፡ይህም ሊያስፋፋ ላሰበው ሥራው እንቅፋት ፈጥሮበታል።
የማዕከሉ ሜዲካል ዳይሬክተር ዶክተር ሞሚና አህመድ በተለይ ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደተናገሩት፤ የስም ዝውውሩ አለመደረጉ ተቋሙ ባለበት ሁኔታ ብቻ አገልግሎት እንዲሰጥ ገድቦታል፡፡ ብዙ የማስፋፊያ ሥራዎችም እንዳይሰሩ አድርጓል፡፡ ይህ ደግሞ ተጠቃሚን ከማብዛትም ሆነ በጥራት አገልግሎት ከመስጠት አኳያ የተዋጣለት ሥራ ለመስራት እንዳይቻል እንቅፋት ሆኗል ብለዋል፡፡
ማዕከሉ የሚሰፋበትንና መስተካከል ያለባቸውን ነገሮች አቅዶ ወደተግባር የሚገባበትን ሁኔታዎች ለማመቻቸት እንዳላስቻለው የሚናገሩት ሜዲካል ዳይሬክተሯ፤ በአገር አቀፍ ደረጃ ብቸኛ የንቅለተከላ ማዕከል በመሆኑና በርካታ ህሙማንን በወቅቱ ለማከም የማስፋፊያ ቦታ ያስፈልገዋል፡፡
ሆኖም በእያንዳንዱ ሥራ ላይ ቀድሞ እቅድና በጀት ማስበጀት ያስፈልጋል፡፡ ለዚህ ደግሞ መጀመሪያ ማዕከሉ ባለቤትነቱን ማረጋገጫ ህጋዊ ማስረጃ ሊኖረው ያስፈልጋል፡፡ ነገርግን የራስ ባልሆነ ንብረት ላይ ማዘዝና እቅድ ማስያዝ ስለማይቻል የስም ዝውውሩ መዘግየት ቀጣይ ሥራዎችን ለመስራት እንዳይቻል ማድረጉን ገልጸዋል፡፡
የሆስፒታሉ የአስተዳደርና ልማት ምክትል ፕሮቮክስ አቶ ተመስገን መኮንን በበኩላቸው፤ የስም ዝውውሩ ባለመደረጉ ተቋሙን ላልተፈለገ ወጪና ምልልስ መዳረጉን አስታውቀዋል፡፡ በተለይም ጉዳዩ ያለአግባብ በተደጋጋሚ እንዲታይ የሚጠየቅበት ሁኔታ ሌላ ሥራ የሚሰራበትንም ጊዜ እያባከነ መምጣቱን ጠቅሰው ባለንብረቱ የነበረውም ተቋም በተዘጋ ጉዳይ እንደ አዲስ የቤት ኪራይ እንዲጠይቁና እንዲከሱ እያደረጋቸው መሆኑን አስረድተዋል፡፡
እንደ አቶ ተመስገን ገለጻ፤ ማዕከሉ ለኩላሊት ንቅለተከላው ተብሎ ቀደም ሲል ባለመሰራቱ አሁን ባለው ደረጃ ለአገልግሎት ምቹ አይደለም። ሆኖም ግን አገልግሎት በመስጠት ላይ ይገኛል። ነገር ግን ባለችው ጠባብ ቦታ ሰፊ ማስፋፊያ ለማድረግ ባለመታቀዱ የተነሳ የስም ዝውውሩ ብቸኛ ምክንያት ነው ብሎ መውሰድ እንደማይቻል ገልጸዋል፡፡ የባለቤትነት መብት አለመረጋገጡ ግን እንግልትን ከመፍጠር ባለፈ ሌላ ተጨማሪ ሥራ እየሰጠ መሆኑን አንስተዋል፡፡
ስም ዝውውሩ በታቀደለት ጊዜ አለመከናወኑ የማይገባ ሁኔታ ውስጥ እንደከተታቸው የሚናገሩት አቶ ተመስገን፤ ያልታቀዱና በጀት ያልተያዘላቸው ሥራዎች እየተሰሩ መሆናቸውን ጠቅሰዋል። አሁንም ስም ዝውውሩ በአፋጣኝ እንዲከናወንላቸው ይጠይቃሉ፡፡
አዲስ ዘመን ህዳር 21/2012
ጽጌረዳ ጫንያለው