አዲስ አበባ፡- የምሥራቅ አፍሪካ የልማት በይነ መንግሥታት /ኢጋድ/ አባል ሀገራት ለቀጣናው ሰላም መስፈን ሚናቸው የጎላ መሆኑን የኢፌዴሪ ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አህመድ ገለጹ፡፡
13 ኛው የኢጋድ የመሪዎች ጉባኤ ትናንት በአዲስ አበባ በተካሄደበት ወቅት የመክፈቻ ንግግር ያደረጉት ጠቅላይ ሚኒስትር ዶክተር አቢይ አሕመድ አባል ሀገራቱ በተለይም ከቅርብ ጊዜ ወዲህ በቀውስ አያያዝና ግጭቶችን በማስቀረት ያስገኟቸው ለውጦች ውጤታማ እንደሆኑ ተናግረዋል፡፡
ሶማሊያ ከከባድ የፀጥታ ችግር ወጥታ አሁን ባለችበት ሁኔታ ለህዝቦቿ ምቹ ሆና መመልከት መቻሉን ያነሱት ሊቀመንበሩ፣ በሶማሊያ የአፍሪካ ህብረት ተልእኮ/ አሚሶም/ በቀጣናው ሰላም ማስከበር የተጫወተውን ሚና አድንቀዋል።
ኢጋድ በደቡብ ሱዳን እና በሱዳን የተከሰቱ ግጭቶችን ለማረጋጋት የሰራው ሥራ እንዲሁም ኢትዮጵያና ኤርትራ የቀደመ ግንኙነታቸውን በመለሱበት ወቅት አባል አገራቱ ያሳዩት ድጋፍ የሚበረ ታታና የጋራ ችግሮችን በጋራ ለመፍታት የሚደረግ ጥረት ማሳያ እንደሆነ ዶክተር አቢይ በንግግራቸው ጠቅሰዋል።
አባል ሀገራቱ በቀጣናው ሰላም መስፈንና ልማት እንዲጠናከር የሚያደ ርጉትን ጥረት በስኬትነት ያነሱት ጠቅላይ ሚኒስትር አቢይ፣ ኢትዮጵያ ኢጋድን ለበርካታ ዓመታት እንድትመራ አመኔታ በማሳደራቸውም አድናቆታቸውን ገልፀዋል።
በጉባኤው ላይ ኢጋድን በዋና ፀሐ ፊነት ለ 11 ዓመታት ያገለገሉት የቀድሞው የኢጋድ ዋና ፀሐፊ አምባሳደር ማህቡብ ማሊም ከአዲሱ ዋና ፀሐፊ ዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ ጋር የሎጎ ርክክብ ያደረጉ ሲሆን፣ አምባሳደሩ ለዶክተር ወርቅነህ ገበየሁ መልካም የሥራ ጊዜን ተመኝተዋል።
ኢጋድ በ13ኛው የመሪዎች ጉባኤው ሱዳንን ሊቀመንበር አድርጎ የመረጠ ሲሆን የሀገሪቱ ጠቅላይ ሚኒስትር አብደላ ሀምዶክም የወቅቱ የኢጋድ ሊቀመንበር ሆነዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012
ድልነሳ ምንውየለት
ፎቶ፡- ዳኜ አበራ