አዲስ አበባ፡- የኢትዮጵያ ህዝቦች አብዮታዊ ዴሞክራሲ ግንባር (ኢህአዴግ) ከአራቱ ግንባር ድርጅቶች ወደ ውህድነት በመምጣቱ ስኬታማ ከሆነ ለሌሎች ፓርቲ ዎችም አርዓያ እንደሚሆን የፓርቲ አመ ራሮችና ፖለቲከኞች ገለጹ። ስኬቱ የሚለካው ከውህደት በኋላ በሚያሳየው ለውጥ መሆኑን የተናገሩት አስተያየት ሰጪ ዎች፤ በአገሪቱ ውስጥ የተከሰቱ ችግሮችን በመቅረፍ መልካም አስተዳደር የሚያሰፍን ከሆነ ለሌሎች ተፎካካሪ ፓርቲዎችም አርዓያ እንደሚሆን ተናግረዋል።
የመድረክ እና የኦሮሞ ፌዴራላዊ ኮንግረስ (ኦፌኮ) ሊቀመንበር ፕሮፌሰር መረራ ጉዲና ለአዲስ ዘመን ጋዜጣ እንደገለጹት፤ ዋናው ጉዳይ የፓርቲው መዋሃድ ሳይሆን የሚያመጣው ለውጥ ነው። ፓርቲው ለውጥ ካመጣ አርዓያ የማይሆንበት ምክንያት የለም። ካልተሳካለት ግን መጥፎ ምሳሌ ነው የሚሆነው። ‹‹ውህደት በራሱ መፍትሔ አይደለም›› የሚሉት ፕሮፌሰር መረራ፤ ዋናው ጉዳይ የተዋሃደው ምን ለመሥራት ነው የሚለው እንደሆነ ተናግረዋል። ማንም ፓርቲ ቢሆን መጥፎ ፓርቲ መሆን አይፈልግም፤ ውጤታም ፓርቲ ለመሆን ግን ችሎታ ነው የሚወስነው።
ውህድ ፓርቲ መሆኑ በራሱ ህብረ ብሄራዊነትን ያመጣል ማለት እንደማያስችል የአፍሪካ ተሞክሮም እንደሌለ ይናገራሉ ፕሮፌሰር መረራ። በንጉሳዊ ሥርዓቱም፣ በወታደራዊ የደርግ ሥርዓትም የነበረው ተሞክሮ አገሪቱን የጎዳ ነበር። ለ27 ዓመታት የቆየው ኢህአዴግም የፌዴራሊዝም ሥርዓትን አሰፍናለሁ ብሎ አገሪቱን ሲያምስ የነበረ ነው። አዲሱ ውህድ ፓርቲ ሀገሪቱ የተጋረጡባትን ፈተናዎች ማለፍ የሚችል ከሆነና ሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት የሚዘረጋ ከሆነ ነው መዋሃዱ ለውጥ አምጥቷል የሚባለው። ሀቀኛ የፌዴራሊዝም ሥርዓት ካልዘረጋ ስሙን ስለቀየረ ብቻ ለውጥ ነው ማለት አይቻልም።
የሕብር ኢትዮጵያ ዴሞክራሲያዊ ፓርቲ ሊቀመንበር እና የኢትዮጵያ ፖለቲካ ፓርቲዎች የጋራ ምክር ቤት ምክትል ሰብሳቢ አቶ ግርማ በቀለ እንደሚሉት፤ ኢህአዴግ ያደረገው የፕሮግራም ለውጥ አልታየም፤ የነበረውን ኢህአዴግ ፕሮግራም የሚያስቀጥል ሆኖ አደረጃጀቱን ነው አገራዊ ሆንኩኝ ያለው። የመዋቅር ለውጥም አላመጣም፤ መተዳደሪያ ደንቡ ላይ ባለው የየክልሉ ፓርቲዎች ኮታ ያው የነበረው አይነት ነው። የሚጠበቀውን የዴሞክራሲያዊ አደረጃጀት ለውጥ የለውም። ስሙን መቀየር ሳይሆን መሰረታዊ ለውጥ ነው ማምጣት ያለበት።
‹‹መዋሃዱ እንደ አገር ምን ያስገኝልናል ተብሎ ነው መታየት ያለበት›› የሚሉት አቶ ግርማ፤ የውህደት ሂደቱና አሰራሩ የሌሎች ፓርቲዎች ጉዳይ እንዳልሆነ ይናገራሉ። ይሄ የራሱ የድርጅቱ አሰራር ነው። መዋቅሩን በትብብር፣ በግንባርም ሆነ በውህድ የማዋቀር ህገ መንግሥታዊ ሥርዓቱም የድርጅቱ ደንብም የሚፈቅድለት ነው።
‹‹ውህደቱ አዳዲስ ፓርቲዎች እንዲቀ ላቀሉ ያደርጋል›› የሚሉት ደግሞ አቶ ሙሼ ሰሙ ናቸው። እንደ አቶ ሙሼ አስተያየት፤ በአገራቸው ጉዳይ ላይ ዕድል አጥተው ለነበሩ ፓርቲዎች በአገሪቱ ፖለቲካ ውስጥ የመሳተፍ ዕድል እንዲኖራቸው ያደርጋል። አንድ የፖለቲካ ፓርቲ ዕድሜ ልኩን አራትና አምስት ብቻ ሆኖ መቀጠል የለበትም። በአንድ አይነት ማዕቀፍ ውስጥ ሌሎችንም ማካተት አለበት። በፊት የነበሩበትን የብሄር ፖለቲካ ይዞ ከማራገብ ይልቅ አገራዊ ራዕይ ይዘው እንዲሰሩ ያደርጋል።
አዲሱ ውህድ ፓርቲ ከባህሪው ተነስቶ ዴሞክራሲያዊ ይሆናል አይሆንም የሚለውን አሁን ላይ ማወቅ ባይቻልም እስካሁን ኢህአዴግ በመጣበት አካሄድ ግን መቀጠል እንደማይችሉ ግልጽ የሆነላቸው ይመስለኛል›› ይላሉ አቶ ሙሼ። ህዝቡ የሚያነሳው ጥያቄ ኢህአዴግ ቀደም ሲል ከፈጠረው አደረጃጀትና ርዕዮተ ዓለም የራቀ ነው። ከዚህ በፊት ችግር የነበረው በአገሪቱ ውስጥ የጋራ ጉዳይና ራዕይ አለመኖር ነው። ነገ ምን ሊሆን እንደሚችል ባይታወቅም የውህደት አደረጃጀቱ ግን ለዚህ መፍትሔ የሚሆን ይመስላል ይላሉ አቶ ሙሼ ሰሙ።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012
ዋለልኝ አየለ