ፍቼ፡- የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ለሆስፒታሎች እና ጤና ተቋማት 30 ሚሊዮን ብር የሚያወጣ መድሃኒት እና ለትምህርት ተቋማት 40ሺ መጽሃፍትን ማከፋፈሉን አስታወቀ።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ የምርምርና ማህበረሰብ አገልግሎት ምክትል ፕሬዚዳንት ዶክተር እሸቱ ወንድሙ ለዝግጅት ክፍላችን እንደገለፁት፤ ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ድረስ ከበርካታ የጤናና የትምህርት ተቋማት ጋር ግንኙነት በመፍጠር የተለያዩ ድጋፎችን እያደረገ ሲሆን በተለይም ደግሞ በአውሮፓ እና አሜሪካ ስታንዳድ የተዘጋጁ መጽሐፍትን ከውጭ አገር ዩኒቨርሲቲዎች ጋር በመፃፃፍ ወደ ሀገር ውስጥ እንዲገቡ በማድረግ እጥረት ላለባቸው የጤናና ትምህርት ተቋማት እያበረከተ ይገኛል።
በተመሳሳይ መንገድ ከተለያዩ አካላት ያገኛቸውንና ግምታቸው 30 ሚሊዮን ብር የሚሆን መድሃኒቶችን ለሆስፒታሎች ማከፋፈሉን አስረድተዋል። በቀጣይም በማህበረሰብ አገልግሎት ዘርፍ በሰፊው የመስራት ውጥን እንዳለው አብራርተዋል።
የሰላሌ ዩኒቨርሲቲ ማህበረሰብ አገልግሎት ዳይሬክተር ዶክተር ታደሰ ብርሃኑ በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው በአራቱም አቅጣጫዎች እስከ 100 ኪሎ ሜትር ድረስ በመንቀሳቀስ የአርሶአደሩንና ከተሜ ነዋሪዎችን ህይወት የሚያቃልሉ ሥራዎችን እያከናወነ መሆኑን ጠቁመዋል። በምርምር ሥራው በርካታ ጉዳዮችን እየዳሰሰ መሆኑን ተናግረው ለአብነትም ከአማራ፣ ደቡብ ብሄር ብሄረሰቦች እና ኦሮሚያ ክልል የተለያዩ አካባቢዎች በተገኙ የድንች ዝርያዎች ላይ ምርምር አድርጎ በአሁኑ ወቅት ለአካባቢው እጅግ ተስማሚ የሆኑ አምስት ምርጥ የድንች ዝርያዎች ወደ አርሶ አደሩ ተሰራጭተው ውጤታማ ምርት እያሳዩ መሆኑን አብራርተዋል።
በአካባቢው ከፍተኛ የሆነ የወተትና የእንስሳት ሃብት በመኖሩ በዚህ ላይ ምርምር እየተደረገ መሆኑን ጠቁመው በዚህም የተለያዩ የእንስሳት ዝርያዎች ላይ ምርምር እየተደረገ መሆኑን አብራርተዋል። ከዚህም በተጨማሪ በጤና እና የትምህርት ተቋማት መሻሻል ላይ ድጋፍ እያደረገ መሆኑን አረጋግጠዋል። በዚህም በአጎራባች ወረዳዎችና የትምህርት ተቋማት ላይ ያላሰለሰ ድጋፍ እያደረገ ሲሆን ለሆስፒታሎች መድሃኒት፣ ለትምህርት ተቋማት ደግሞ መጻሕፍት በማከፋፈል ላይ መሆኑን አብራርተዋል።
የሙከጡሪ ሆስፒታል ሥራ አስኪያጅ አቶ ላስቻለው ሃይማኖት በበኩላቸው፤ ዩኒቨርሲቲው እስካሁን ድረስ 40 ፍራሾችን ጨምሮ የተለያዩ የህክምና መገልገያ ቁሳቁሶችንና የመድሃኒት ድጋፎችን አድርጓል። በተለይም ደግሞ በቀላሉ ለመግዛት አስቸጋሪ የሆኑና ለታካሚዎችም ፍቱን የሆኑ መድሃኒቶችን በአጭር ጊዜ ከዩኒቨርሲቲው መገኘቱን ጠቁመዋል። ዩኒቨርሲቲው ያደረ ገው ድጋፍ የሆስፒታሉን ችግር በከፍተኛ ሁኔታ ማቃለሉን ጠቁመዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012
ክፍለዮሐንስ አንበርብር