– ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ስጋት ደቅኗል
አዲስ አበባ፡- ከሰኔ ወር አጋማሽ ጀምሮ ባልተቋረጠ ሁኔታ በየመን እና ሶማሌ ላንድ በኩል ወደ ኢትዮጵያ የገባው የአንበጣ መንጋና በአፋርና ሸዋሮቢት አካባቢ ተከስቶ የነበረውን የግሪሳ ወፍ በሰብል ላይ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል መቆጣጠር መቻሉን የግብርና ሚኒስቴር አስታወቀ።
በግብርና ሚኒስቴር የግብርና ልማት ዘርፍ ሚኒስትር ዴኤታ አቶ ሳኒ ረዲ ለዝግጅት ክፍሉ እንደገለጹት፤ የዝናቡ ስርጭትና የሙቀቱ ሁኔታ ለእርሻ ሥራው አመቺ የሆነውን ያህል በዚያው መጠን ለልዩ ልዩ ተባዮችና የሠብል በሽታዎች መራባት ምቹ ሁኔታን ፈጥሯል።
በቀን እስከ 160 ሚሊዮን መጠን ያለው የበረሃ አንበጣ ከየመንና ከሶማሊ ላንድ ወደ ኢትዮጵያ እንደሚገባ የገለጹት ሚኒስትር ዴኤታው፤ መንግስት የጉዳዩን አሳሳቢነት በመረዳት ቀደም ብሎ ከ96 ሺ ሊትር በላይ የኬሚካል ግዢ በማከናወንና ሁለት አውሮፕላኖችን በራስ አቅም በመመደብና ብሎም ከምስራቅ አፍሪካ አንበጣ መከላከያ ተቋም ሁለት አውሮፕላኖችን በመከራየት ባደረገው ሰፊ የኬሚካል ርጭት የአንበጣውን ዝውውር መግታት ተችሏል።
በአሁኑ ወቅት የአንበጣው መንጋ ከአፋር፣ ከምስራቅ አማራ እና ከደቡብ ምስራቅ ትግራይ ማባረርና ነፃ ማውጣት መቻሉን የገለፁት አቶ ሳኒ፤ ሰብል አምራች ወደሆኑት አማራ፣ ኦሮሚያና ደቡብ ብሄርብሄረሰቦችና ህዝቦች ክልል እንዳይዛመት የመግታት ሥራዎች ውጤታማ መሆናቸውን አብራርተዋል። የአንበጣው መንጋ ወደ ኢትዮጵያ መግባት ከጀመረበት ከሰኔ አጋማሽ ጀምሮ በ39 ሺ 574 ሄክታር መሬት ላይ ማረፉን አስታውሰው ከዚህ ውስጥ 34 ሺ 500 ሄክታር የሚሆነውን መሬት ከጥፋት መከላከል ተችሏል።
አንበጣ በባህሪው እርጥበታማ አየር ጠባይ ስለሚመርጥ በቀጣይ እርጥበታማ የአየር ጠባይ ወደሚኖራቸው ወደ ኬኒያና ታችኛው ሶማሌ ክፍል እንዲሁም ወደ ቦረና አካባቢ እንደሚሄድ ይጠበቃል ያሉት አቶ ሳኒ፤ እንቅስቃሴውን መሰረት በማድረግም የማዳከም ስራዎችን ለማከናወን ከወዲሁ ሁለት አውሮፕላኖች ዝግጁ መሆናቸውን አስረድተዋል።
ትግራይ ክልል ገብቶ የነበረው የአንበጣ መንጋ ወደ ኤርትራ መሻገሩን እና በሚኖረው የአየር ጸባይ ምክንያትም ኢትዮጵያ ውስጥ የሚቆይበት ጊዜ ውስን መሆኑን ያብራሩት ሚኒስትር ዴኤታው፣ አፋርና ሸዋ ሮቢት አካባቢ ተከስቶ የነበረውን የግሪሳ ወፍም ተደጋጋሚ እርምጃ በመውሰድ የከፋ ጉዳት ሳያስከትል በቁጥጥር ስር ማዋል ተችሏል። ሆኖም ግን በሶማሌ ላንድ በኩል በየቀኑ በመቶ ሚሊዮኖች የሚገባው የአንበጣ መንጋ እስካሁንም አልተቋረጠም። ይሁንና የመንጋው እንቅስቃሴ በቁጥጥር ስር በመሆኑ የከፋ ጉዳት የማስከተል አቅም አይኖረውም።
አንበጣ መንጋንና የግሪሳ ወፍን በተደረገው ርብርብ የከፋ ጉዳት ሳያስከትሉ መቆጣጠር ቢቻልም ወቅቱን ያልጠበቀ ዝናብ ግን አሁንም ከባድ ስጋት መሆኑን ያስረዱት ሚኒስትር ዴኤታው እስካሁንም መሰብሰብ ካለበት የደረሰ ሰብል ውስጥ የተሰበሰበው 48 በመቶ ብቻ ነው። በመሆኑም ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል በማስተባበር ሰብሎችን ማሰባሰብ ካልተቻለ በመጠንም ሆነ በጥራት ከፍተኛ መጠን ያለው ሰብል ሊታጣ እንደሚችል አስጠንቅቀዋል። ሁሉም የህብረተሰብ ክፍል ዝናቡ የሚያደርሰውን ሥጋት ከግምት ውስጥ በማስገባት የደረሱ ሰብሎችን በማጨድና ወደ ጎተራ በማስገባት ሀገራዊ ግዴታውን እንዲወጣ አቶ ሳኒ አሳስበዋል።
አዲስ ዘመን ህዳር 20/2012
እስማኤል አረቦ